ኦቲዝም - ክፍል ፩

ኦቲዝም - ክፍል ፩
Photo by Hiki App / Unsplash

የኦቲዝም ቁጥር መጨመር

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም. መጀመሪያ ከአንድ መቶ ሃምሳ ልጆች መሀከል አንድ (150፡1) ኦቲስቲክ ልጅ ይገኝ እንደነበረና ከሃያ ዓመታት በኋላ ይህ ቁጥር በሶስት እጥፍ ያህል ጨምሮ በ2020 ዓ.ም. ከሰላሳ ስድስት ልጆች መሀል አንድ (36፡1) ኦቲስቲክ ልጅ መገኘቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኦቲዝም ቁጥር መጨመር ምክንያቱ ምን እንደሆነ ከመመልከታችን በፊት ኦቲዝምን አስመልክቶ ያሉትን ግንዛቤዎች በጥቂቱ እንዳስስ።

(ስለ ኦቲዝም ብዙ የምንነጋገርባቸው ነጥቦች እንዳሉ በመገንዘብ ወደፊት ሌሎች አርዕስቶችን ይዘን እንደምንመለስ አስቀድመን እናሳውቃለን።)


ኦቲዝም - ከየት ወዴት

ከ1940 - 1960 ዎቹ ዓመታት (እ.አ.አ.)

የኦቲዝም ምልክቶች አልፎ አልፎ የሚታዩ ስለነበሩና ከሃያ አምስት ሺህ ልጆች መሃል አንድ ሁኔታውን የሚያሳይ ልጅ ይገኝ ስለነበረ የአዕምሮ በሽታ እንዳለበት ሆኖ ተቆጥሮ ሁኔታው ከስኪዞፍሬንያ ጋር ተደምሮ ይታይ ነበረ።

በ1980 ዎቹ (እ.አ.አ)

የኦቲዝም ምልክቶች ከስኪዞፍሬንያ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ስለተገመገመ በነጠላ ፈርጅ ኦቲዝም ዲዞርደር (autim disorder) ተብለው እንዲጠቃለሉ ተወሰነ።

በ1990 ዎቹ (እ.አ.አ)

  • ኦቲዝም በዘር ሊወረስ የሚችል ኒውሮሎጂያዊ ልዩነት ወይም የነርቮች አወጣጠር ልዩነት (neurological difference) እንደሆነ ጥናታዊ መረጃዎች አረጋገጡ። አንዳንድ የኦቲዝም ዲዞርድር ምልክቶች የሚገኝባቸው ሰዎችም ጤናማ የአዕምሮ ብስለት እንደሚያሳዩ፣ ከዚያም አልፎ የረቀቀ አስተሳሰብና ልዩ ችሎታ ወይም ተሰጥዖ ሊኖራቸው እንደሚችል እየታወቀ በመምጣቱ አስፐርጋርስ ሲንድረም (Asperger's syndrome) በሚል ስያሜ እንዲሌዩ ሆነ።
  • የኦቲዝም ምልክቶች በተለያየ መልክ ሊገለጹ እንደሚችሉና ኦቲስቲክ ሰዎች ደግሞ ዋሕድ ዘር/ጋነገብ ወይም አንድዓይነት አለመሆናቸው ሲታወቅ ልዩነታቸው አንዳለ ሆኖ ሁሉም በኦቲዝም ስፔክትረም ዲዞርደር - ኤ.ኤስ.ዲ. (autism spectrum disorder - ASD) አንድ የጃንጥላ ጽንሰ-ሀሳብ ሥር እንዲካተቱ ተደረገ።

በ2000 ዎቹ (እ.አ.አ.)

ኦቲዝም በሰዎች መሀከል የሚገኝ የነርቮች ድር አወጣጠር ልዩነት ነው የሚል አስተሳሰብ እየገነነ መጥቷል። የዚህ አመለካከት አርአያ ኒውሮዳይቨርሲቲ ፓረዳይም (neurodiversity paradigm) ሲሆን ኦቲዝም - እንደ ግራኝነት - በሰዎች መሀከል ከሚገኙ በርካታ ልዩነቶች ረድፍ ሊደመር ይገባል በሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረት ነው።

የኒውሮዳይቨርዚቲ ፓረዳይም አቋም

  • ሰዎች ስንባል ትክክለኛ ወይም ኖርማል በሚባል መመዘኛ አንለካም - ሁላችንም የተለያየን ነን።
  • አንጎል ወይም የነርቮች ድር አወጣጠር ከሰው-ሰው ይለያያል - አንዱ ከሌላኛው የተሻለ ወይም ያነሰ አይደለም።
  • ኦቲዝም የተፈጥሮ ብዝሃ-ሕይወት (ባዮዳይቨሲቲ - biodiversity) አንዱ አካል ነው፣ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ኦቲዝም የማንነት አንዱ ገጽታ ነው።
  • ሰውን አቅመ-ውሱን የሚያደርገው (disability) ተፈጥሮውና ማንነቱ ሳይሆን በዚያ ሰውና በአካባቢው መሀከል የሚኖረው አለመጣጣም ወይም አለመስማማት ነው - አካባቢን ለኦቲስቲክ ሰዎች ማመቻቸት የሕክምና ዕርዳታ አንዱ ዋና ተግባር ሊሆን ይገባል።
  • በሰዎች መሀከል ልዩነቶች እንዳሉ ሁሉ ጥንካሬዎችም ይገኛሉ።
  • የኒውሮዳይቨርሲቲ ዓላማና ግብ ኦቲስቲክ ሰዎች ሙሉ-በሙሉ እራሳቸውን መሆን እንዲችሉ ማገዝና ሕይወታቸውን እነርሱ በሚመርጡት መንገድ እንዲመሩ ሁኔታዎችንና አካባቢያቸውን ማመቻቸት ነው።
  • ኦቲዝም እንደበሽታ መታየቱ እንዲቆም ሕዝብን ማስተማርና ማንቃት ያስፈለጋል።

ኦቲስቲክ ሰዎች የአካባቢያቸው ሁኔታ የሚያስከትልባቸው ውጥረት ከአቅማቸው በላይ ሲሆን ስሜታቸውን ለመግራት ተስኗቸው ኦቲስቲክ ባልሆኑት የኅብረተስብ አባላት አመለካከት ተቀባይነት የሌላቸውን ባህርያት ሊያሳዩ ይችላሉ።

ትኩረታችንን በእነዚህ ባህርያት ላይ ስናደርግና በኦቲስቲክ ሰዎች ላይ አካባቢያቸው ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ሳናስገባ ስንቀር ለኦቲስቲክ ሰዎች የባህርይ ለውጥ ምክንያቱ ኦቲዝሙ ነው የሚል የተሳሳተ ውሳኔ ላይ ልንደርስ እንችላለን።

የኒውሮዳይቨርሲቲ ፓረዳይም አርአያነት አጉልቶ የሚያሳየን ዓለም ኦቲስቲክ ባልሆኑ (non-autistics) ሰዎች የተቀረጸች ስለሆነች ለኦቲዝም ሰዎች የምትመች አለመሆኗን፣ ኦቲስቲክ ሰዎች ከአካባቢያቸው ሁኔታ ጋር የማይስማማ የነርቭ ድር አወቃቀር እንዳላቸው፣ እንዲሁም አካባቢያቸውን ወይም ኦቲስቲክ ያልሆኑ ሰዎችን ለመምሰል በሚያደርጉት ጥረት ከባድ የመንፈስ ውጥረት (stress) ሊያድርባቸው እንደሚችል ነው።

ኦቲዝም ምን ይመስላል?

"እኔ ኦቲዝም ያለብኝ ሰው አይደለሁም። ኦቲዝም ከእኔነቴ ጋር የተዋሃደ ማንነቴ ነው እንጂ። ስለሆነም ኦቲዝም በእያንዳንዷ የሕይወቴ ቅጽበት ውስጥ በሚኖረኝ አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ግንዛቤ ላይ ተጽዕኖ አለው።" (ስለ ኦቲዝም መብት ተሟጋች የሆኑ አንድ ሰው ከተናገሩት የተቀነጠበ)

ብዙ ሰዎች (በርካታ የጤና ባለሞያዎችን ጨምሮ) ስለኦቲዝም ያረጀና ጊዜው ያለፈበት አመለካከት አላቸው። ማለትም - የሌላን ሰው ዓይኖች በቀጥታ የማይመለከቱ፣ ለየት ያለ ባህርይ የሚያሳዩ፣ የአዕምሮ ብስለት የሌላቸው፣ መናግር የማይችሉና ሙሉ ሰዓት የሌላ ሰው እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ድኩማን ናቸው ብለው የሚያምኑ ብዙኃን ናቸው።

የተሳሳቱ አመለካከቶችን እንመርምር

  • ኦቲዝም ልጆች ሲያድጉ የሚጠፋ ሁኔታ ነው። (አይደለም!)
  • ኦቲዝም የበለጠ በወንዶች ዘንድ የሚከሰት ሁኔታ ነው። (በብዙ የሚቆጠሩ ኦቲስቲክ ሴቶች ሳይታወቅላቸው ይቀራሉ፣ አለዚያም ኦቲስቲክ መሆናቸው የሚታወቀው ዘግይቶ ነው።)
  • ኦቲስቲክ ሰዎች ለሰዎች ርኅራሔ (empathy) የላቸውም። (በርካታ ኦቲስቲክ ሰዎች የላቀ ስሜታዊነት ሊያሳዩ ይችላሉ።)

የሚከተሉትን ማስተዋል ይገባል፦

  • በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት ያለው የኦቲዝም ትክክለኛው አጠራር ኦቲዝም ስፔክትረም ዲዞርደር (autism spectrum disorder) ነው። ከኦቲዝም ጋር ሊከሰቱ በሚችሉ ጉዳቶችና ለመፍትሔዎቻቸው ትኩረት እንዲሰጥ በመሻት ኦቲዝም ስፔክትረም ዲዛቢሊቲ (autism spectrum disability) የሚለውን አጠራር የሚመርጡ አሉ።
  • የኦቲዝም መከሰት ምክንያት ይህ ነው ተብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ይሁንና ልጅ የሚያድግበት የአካባቢ ሁኔታ እንዲሁም የዘር ጂኖች በመተባበር በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ኦቲዝም ሊከሰት ይችላል ተብሎ ይታመናል።
  • ኦቲስቲክ ሰዎች የተለያዩ ባህርዮችን ሊያሳዩ ይችላሉ። ለምሳሌ፦
    • ከሰዎች ጋር መስተጋብር ሊያዳግታቸው ይችላል
    • ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላ ሁኔታ መሸጋገር ወይም ለውጥ ሊከብዳቸው ይችላል
    • ለጥቃቅን ሁኔታዎች ትኩረት የመስጠት ባህርይ ሊያሳዩ ይችላሉ
    • ወዘተ
  • የኦቲስቲክ ሰዎች ችሎታ፣ ፍላጎትና ሁኔታ የአንዳቸው ከሌላኛቸው ሊለያይ ይችላል።
    • አንዳንዶቹ እራሳቸውን ችለው በብቃት መኖር ሲችሉ ሌሎች ደግሞ የዕድሜ ልክ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሊሆኑ ይችላሉ
    • በትምህርትና በሥራ ዓለም ላይ ተጽዕኖ ሊያጋጥማቸው ይችላል
    • ብዙ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ኦቲስቲክ ሰዎች መንከባከብ በቤተሰብ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል
  • የኦቲዝም ምልክቶች የሚታዩት በልጅነት ዕድሜ ነው። ይሁን እንጂ ኦቲዝም እንዳላቸው ሳያውቁ ቆይተው አድገው በዐዋቂ ዕድሜያቸው ሁኔታው የሚታወቅላቸው ሰዎች ቁጥራቸው እየበረከተ መጥቷል።
  • የኦቲስቲክ ሰዎች የአዕምሮ ብስለት ከዝቅተኛ እስከ እጅግ የላቀ ደረጃ የተለያየ ሊሆን ይችላል።
  • ኦቲስቲክ ሰዎች የተለያዩ የአዕምሮ ጤና ሁኔታዎች በተደራቢነት ሊኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ፦ ጭንቀት፣ ድባቴ፣ የማስተዋል ብቃት መዛባት (ADHD)፣ ወዘተ

ከኦቲዝም ጋር የሚታዩ ሁኔታዎች

  • የአካባቢያቸው ሁኔታዎች በስሜቶቻቸው ላይ ከባድ ተጽዕኖ ሲያሳድሩባቸው ኦቲስቲክ ሰዎች የመረበሽ ወይም እራሳቸውን የማግለል ባህርይ ሊያሳዩ ይችላሉ። (ለምሳሌ፦ ድምፅ፣ ብርሐን፣ ወ.ዘ.ተ. ሊያውካቸው/ሊረብሻቸው ይችላል።)
  • የኦቲስቲክ ሰዎች ለጥቃቅን ነገሮች/ሁኔታዎች ትኩረት የመስጠት ባህርይ ኦቲስቲክ ካልሆኑ ሰዎች አመለካከት ጋር ላይጣጣም ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ትኩረታቸው ጥራት ያለውና ስኬታማ ውጤት ስለሚያስገኝላቸው በአንዳንድ የሥራ መስኮች ተፈላጊ ያደርጋቸዋል ።
  • ንግግራቸው ቀጥተኛና ፊትለፊት ሊሆን ይችላል፣ ሰዎች የሚሉትንም በቀጥታ የመተርጎም ዝንባሌ ሊያሳዩ ይችላሉ። ስለዚህ ቀልድ ወይም ተረብን ያካተቱ አነጋገሮችን መገንዘብ ሊያዳግታቸው ይችላል።ይህም አለመግባባትን ሊያስከትልና የኦቲስቲክ ሰዎችን ውጥረት (stress) ሊያባብስ ይችላል።
  • በአንድ ነገር ላይ ከመጠን ያለፈ የማተኮርና የላቀ የማወቅ ፍላጎት/ዝንባሌ ሊኖራቸው ይችላል። ያም ከአንድ ሀሳብ ወደ ሌላ በቀላሉ መሸጋገር እንዲሁም ለውጥን መቀበል እንዲያዳግታቸው ሊያደርግ ይችላል።

የኦቲዝም ቁጥር መጨመር

በአለፉት ሃያ ዓመታት የኦቲስቲክ ልጆች ቁጥር በየሁለት ዓምቱ ከ10 እስከ 20 በመቶ እያደገ የመጣበትን ምክንያት በሜሪላንድ የኤፒዴሚዮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት Christine Ladd-Acosta እንደሚከተለው ያብራራሉ ።

  • ኦቲዝምን ለመለየት የምንጠቀምበት መስፈርት ሰፋ እንዲል በመወሰኑ በመስፈርቱ የሚታቀፉ ሰዎች ቁጥራቸው እንዲጨምር ምክያት ሆኗል።
  • የጤና ባለሞያዎች ከ18 እስከ 24 ወር ዕድሜ ያላቸውን ሕፃናት ኦቲዝም ይኖራቸው እንደሆነ ለማጣራት ስለሚመረምሯቸው ኦቲዝም የመከኘት ዕድሉ ከፍ እንዲል ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።
  • የጤና ትምህርት በመጠናክሩና ሰዎች ስላኦቲዝም ያላቸው ግንዛቤ እየተሻሻለ በመምጣቱ ወላጆች የኦቲዝምን ምልክቶች ለይተው ማወቅ ችለዋል። ስለዚህም ልጆቻቸው ኦቲዝም ሊኖራቸው ይችል ይሆን ብለው ከጠረጠሩ ቶሎ ሐኪም ዘንድ ወስደው ያሳይዋቸዋል። ይህ ሁኔታ የኦቲዝም ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽዖ አድርጓል።
  • ኦቲዝም በብዙ ማህበረሰቦች ውስጥ ተቀባይነት እየኖረው መጥቷል። ስለሆነም ሰዎች ኦቲዝምን አስመልክቶ የጤና ባለሞያዎችን ዕርዳታ የመጠየቅ ድፍረት አግኝተዋል።
  • በተጨማሪም ሥውር ወይም በዓይናችን የማናያቸውን የኦቲዝም ምልክቶች ለማግኘት የተሻለ ዕውቀት፣ የመመርመሪያ ዘዴና ብቃት እየኖረን ስለመጣ ወትሮ በቀላሉ ልንስታቸው የምንችላቸውን የኦቲዝም ምልክቶች መለየት መቻላችን ለኦቲዝም ቁጥር ማደግ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።

መረጃዎች

https://publichealth.jhu.edu/2025/is-there-an-autism-epidemic

What is Autism, Really? | Understanding Autism
A comprehensive guide to autism, ADHD, and neurodivergence - Brain science, coping strategies, and pathways to thriving

የአንድ የኦቲዝም ወላጅ ተሞክሮ

Read more

አዎን! ወንዶችም ያርጣሉ!

አዎን! ወንዶችም ያርጣሉ!

የሴቶች እርጣት (menopause - ሜኖፖዝ) በእያንዳንዷ ሴት የሕይወት ሂደት ውስጥ በድንገት የሚከሰት ከኤስትሮጀንና ፕሮጀስትሮን የሴቶች ሆርሞኖች መጠን ማሽቆልቆል ሲሆን ከወር-አበባ ማብቃትና የሴቶች የመውለድ ችሎታ ፍጻሜ ጋር የተቆራኘ ሁኔታ ነው። በአንጻሩ ግን የወንዶች እርጣት (andropause - አንድሮፖዝ) በአንዳንድ ወንዶች ዘንድ ብቻ የሚከሰትና ከቴስቶስትሮን የወንዶች ሆርሞን መጠን መቀነስ ጋር የተጣመረ፣ አመጣጡ ደግሞ

By TW
የኮንሸስ ፓረንቲንግ  ፍልስፍና                                              - አስተዳደግ ክፍል ፫

የኮንሸስ ፓረንቲንግ ፍልስፍና - አስተዳደግ ክፍል ፫

ኮንሸስ ፓረንቲንግ (conscious parenting = የንቁ-ሕሊና የአስተዳደግ ዘዴ) በአስተውሎት ወይም በmindfulness ላይ የተመሠረተ የልጆች አስተዳደግ ፍልስፍና ሲሆን የሚከተሉትን ዋና-ዋና ባህርያት ያካትታል። * ወላጆች ስለእራሳቸው የተሻለ ግንዛቤ (self-awareness) እንዲኖራቸው እንዲሁም 'እውነተኛ ማንነታቸውን' (authentic self) በበለጠ ለመረዳት ሲሉ ለስሜቶቻቸው ትኩረት እየሰጡ እራሳቸውን ይመረምራሉ (self-reflection) * የልጆችን አስግተዳደግ አስመልክቶ ያሏቸውን ቅድመ-ግንዛቤዎች በመመርመር አመለካከቶቻቸውንና ተግባሮቻቸውን

By TW
የአንጀት ደህንነት-ለጠቅላላ ጤንነት

የአንጀት ደህንነት-ለጠቅላላ ጤንነት

በአዕላፋት የሚቆጠሩ የተፈላጊ ረቂቃን ነፍሳት ሕብረተሰብ ወይም ማይክሮባዮም (microbiome) በቆዳችን ላይና በሰውነታችን ውስጥ ይገኛል። ከሌሎቹ የሰውነታችን ክፍሎች ጋር ሲነጻጸር በአንጀታችን ውስጥ የሚገኘው የማይክሮባዮም መጠን ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። የአንጀት ውስጥ ማይክሮባዮም ማይክሮባዮም እንደ ባክቴሪያ (የbacteria ነጠላ ስም ባክቴሪየም- bacterium ነው)፣ ቫይረሶች (virus/ viruses)፣ ፈንገሶችና (fungus/fungi) ጥገኛ ነፍሳት (parasites) ያሉ ተህዋሳትን

By TW
"ሆዴ ነግሮኝ ነበረ!"

"ሆዴ ነግሮኝ ነበረ!"

"እኔኮ ታውቆኝ ነበረ፣ ሆዴ ነግሮኝ ነበረ፤ ..." ስንል ምን ማለታችን ነው? * ለመረዳትና ለማብራራት በሚያዳግት ሁኔታ አንዳንድ አጋጣሚዎች ወይም ቦታዎች በውስጣችን ያለመመቸት ስሜት የሚቀሰቅሱብን ለምን ይሆን? * ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅነውን ሰው፣ ስለማንነቱ ብዙም ሳንውቅ ሆዳችን እንድንርቀው የሚገፋፋንስ ለምንድን ነው? * ደግሞስ ሆዳችን ነግሮን በእርግጠኝነትና በፍጥነት ትክክለኛ ውሳኔ የምንወስነው እንዴት ሆኖ ነው? የሆድ

By TW