አስተዳደግ - ክፍል ፩

አስተዳደግ - ክፍል ፩
Photo by Anna Kharkivska / Unsplash

የአስተዳደግ ዓይነቶች

የወላጆችና የአሳዳጊዎች ኀላፊነት ልጆች አድገው እራሳቸውን እንዲችሉ እንዲሁም የኑሮ ውጣውረዶችን ለመቋቋም ብቃት እንዲኖራቸው ኮትኩቶ ማሳደግ ነው።

ከስህተታቸው ትምህርት እንዲያገኙ ድጋፍ በመሆን ዕድሜያቸው በሚፈቅደው መጠን ለልጆች ኀላፊነትን መስጠትና ለሚገጥሟቸው ችግሮች መፍትሔዎችን ፈልገው እንዲያገኙ ዕድል መክፈት ከመልካም አሳዳጊዎች የሚጠበቁ ዋና ተግባሮች ናቸው።

ይሁንና የወላጆችና የአሳዳጊዎች ብቃት፣ በወቅቱ የሚገኙበት ሁኔታ፣ እንዲሁም እራሳቸው በዕድገታቸው ያጋጠሟቸው ልምዶችና የሚያሳድጉት ልጅ ባህርይ ጭምር በልጅ አስተዳደግ ዘዴ ምርጫቸው ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል።

Diana Baumrind የተባሉ የሥነልቦና ባለሞያ በልጆች አስተዳደግ ላይ ሰፊ ጥናት አድርገው ሦስት ዓይነት የአስተዳደግ መንገዶች እንዳሉ በ1960'ዎቹ (እ.ኤ.አ.) ሲያሳውቁ ዘግየት ብለው ደግሞ በ1980'ዎቹ (እ.ኤ.አ.) Eleanor Maccoby እና John Martin የተባሉት ባልደረቦቻቸው አራተኛ መንገድ እንዲታከል አድርገዋል። እንደሚከተለው እንዘረዝራቸዋለን፦

የሚገራ የአስተዳደግ ዘዴ

(Authoritative parenting style)

  • ይህ የአስተዳደግ ዘዴ ከሚያሳድጉት ልጅ ጋር በመቀራረብ በጉዳዮች ላይ አብሮ የመነጋገር ልምድን እንዲሁም መታደግን የሚያበረታታ ነው።
  • አሳዳጊዎች ግልጽ መመሪያ ይሰጣሉ። ደንብና ሥርዓትን መጠበቅ ምን እንድሚመስል እንዲሁም እነዚህን አለመጠበቅ ምንን እንደሚያስከትል በማስረዳት ልጆች የሚጠበቅባቸውን አውቀው እንዲያድጉ የሚያግዝ የአስተዳደግ ዘዴ ነው።
  • ለልጆች ስሜቶችና (emotional well-being) አመለካከቶች ቦታ በመስጠት ልጆቻቸውን ተግተው ያዳምጣሉ፤ ለመግባባት ጥረት ያደርጋሉ። ችግሮችን አብረው ከልጆቻቸው ጋር በመነጋገር ይፈታሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ ነገሮችን የመቋጨትና ውሳኔ የመስጠት ሀላፊነት ግን ምንጊዜም ቢሆን የአሳዳጊዎች መሆኑን ግልጽ አድርገው ያስረዳሉ።

በሚገራ የአስተዳደግ ዘዴ ተደግፈው ያደጉ ልጆች በእራሳቸው የሚተማመኑ፤ ኀላፊነትን ከመውሰድ ወደኋላ የማይሉ፣ የተመዛዘነ አመለካከት ኖሯቸው በመግባባት ከሰዎች ጋር ስኬታዊ ወዳጅነትና ግንኙነቶችን ሊያበጁ የሚችሉ፣ ዕውቀታቸውን ለማስፋት ጉጉት ያላቸውና በተሰማሩባቸው መስኮች ሁሉ መልካም ውጤትን ለማስገኘት የሚጥሩ ዜጎች ይሆናሉ።

የረገበ/የላላ የአስተዳደግ ዘዴ

(Permissive parenting style)

  • አሳዳጊዎች ከልጆቻቸው ጋር 'እንደጓደኝነት' ጥሩ ቅርበት ኖሯቸው በውይይት የሚያምኑ ሲሆን ለልጆቻቸው ስሜታዊ ደህንነት (emotional well-being) ትጋት ያሳያሉ።
  • ለልጆቻቸው አልፎ አልፎ ብቻ መመሪያ ይሰጡ እንደሆን ነው እንጂ እምብዛም አይቆጣጠሯቸውም።
  • አሳዳጊዎች ጭቅጭቅን ፍራቻ በልጆቻቸው ፍላጎት እየተመሩ ሁሉን እሺ ይላሉ፣ ልጆቻቸው በነፃነት ደስ ያላቸውን ውሳኔ እንዲወስኑ ይፈቅዳሉ።
  • ልጆቻቸው ችግር ካጋጠማቸው በፍጥነት ለልጆቻቸው በመድረስ መፍትሔ ይሰጧቸዋል/ ከችግር ያወጧቸዋል።

በረገበ ወይም ላላ ባለ አስተዳደግ የሚያድጉ ልጆች የተለያዩ ጉዳዮችን አስመልክቶ (የምግብ ምርጫቸውን፣ የመኝታ ሰዓታቸውን፣ የቤት ሥራ መሥራት አለመሥራታቸውን ወዘተ) እንደፈለጋቸው መወሰን እንዲችሉ ሆነው ስለሚያድጉ በራሳቸው የመተማመን ባህርይ ያሳያሉ። አድገው የዳበረ የማሕበራዊ ኑሮ ግንኙነት ችሎታ (social skills) የሚኖራቸው ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ እራሳቸውን የመቆጣጠር ችሎታቸው ዝቅተኛ ስለሚሆን የማይበጇቸውን ውሳኔዎች በመወሰን እራሳቸውን ለችግርና ለአደጋ ይዳርጋሉ ።

በተጨማሪም የረገበ/ላላ ያለ አስተዳደግ የሚመርጡ አሳዳጊዎች አካባቢዎችንና ሁኔታዎችን ለልጆቻቸው እንደሚመቹ አድርገው በማረቅ ልጆቻቸው ከጥፋት/ከውድቀት/ከስህተት ተጠብቀውና ተጋርደው ስለሚያሳድጉ ለሕይወት ገጠመኞችና ውጣ-ውረዶች ዝግጁ ያልሆኑ ዜጎች ሆነው ያድጋሉ ።

አምባገነን የአስተዳደግ ዘዴ

(Authoritarian parenting style)

  • የአሳዳጊዎችን ፍላጎትና አመለካከት ብቻ ስለሚያካትት ግትርነታቸው የልጆችን ስሜትና ፍላጎት ይጫናል/ያፍናል
  • የአሳዳጊዎችን መመሪያዎችና ደንቦች ያለ ምንም መፈናፈኛ እንዲከተሉ ሆኖ ልጆች በጥብቅ ቁጥጥርና ቅጣት ያድጋሉ
  • ወላጆችና አሳዳጊዎች ከልጆቻቸው ፍጹምነትን ይጠብቃሉ
  • ብዙውን ጊዜ ልጆቹ ምን ጥፋት እንዳጠፉ ሳይገባቸው ቅጣት ይደርስባቸዋል

በአምባገነን ያስተዳደግ ዘዴ ያደጉ ልጆች መመሪያ፣ ደንብንና ሥነ-ሥራዓትን ያለ ምንም ጥያቄ የሚከተሉ ሰዎች ይሆናሉ። ቅጣትን ፍራቻ ውሳኔዎችን ለመወሰንት የሚያመነቱና በእራሳቸው መተማመን የማይኖራቸው ስለሚሆኑ፣ እንዲሁም ቁጡና ተጻራኒ ባህርይ ስለሚያሳዩ ከሰዎች ጋር በቀላሉ የሚጋጩ ይሆናሉ።

ቸልተኛ የአስተዳደግ ዘዴ

(Neglectful parenting style)

  • አሳዳጊዎች የልጆቻቸውን መሠረታዊ ፍላጎቶች በተገቢው መንገድ ባለማሟላታቸው ልጆቻቸው በቂ እንከብካቤ ሳያገኙ ያድጋሉ
  • አሳዳጊዎች በተለያዩ ምክንያቶች በቅርባቸው ስለማይገኙ የሚገራቸው ሰው አጥተው ልጆች እንዳሻቸው ሆነው ያድጋሉ

በቸልተኛ አስተዳደግ ዘዴ ያደጉ ልጆች የዕድገታቸው ሁኔታዎች አስገድደዋቸው ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ ስለሚኖራቸው ፈጥነው እራሳቸውን ለመቻል ይበቃሉ። ይሁንና ስሜቶቻቸውን ለመግራት ስለሚሳናቸው ከሰዎች ጋር ለመግባባት ይቸገራሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ በእራሳቸው የመተማመን ችሎታቸው ዝቅተኛ ስለሚሆን ከማይበጇቸው ሰዎች ጋር ይገጥማሉ/ ይወዳጃሉ።

የትኛው የአስተዳደግ ዘዴ ይመረጣል?

አንዱን የልጆች አስተዳደግ ዘዴ መርጦ መከተል ያስፈልጋል የሚል አመለካከት ባይኖርም ከፍ ብለው ከተዘረዘሩት አራት መንገዶች መሃል የሚገራ የአስተዳደግ ዘዴ የተሻለና የሚመረጥ እንደሆነ ይታመናል። ይህ ዘዴ የልጆችን የዕድሜ ብስለት ተከትሎ የሚደነገግ ደንብና ሥርዓት ላይ በመመርኮዝ የሚደረግ ግልጽ ውይይትንና መግባባትን ስለሚያበረታታ ልጆች ሚዛናዊ ስሜትና አመለካከት ኖሯቸው እንዲያድጉ ያግዛል ።

አሳዳጊዎች ከአራቱ የአሳዳጊነት ዘዴዎች በአንዱ ላይ የበለጠ ለማተኮር ቢመርጡም ይተለያዩ አጋጣሚዎችና ሁኔታዎች ለየት ያለ የአስተዳደግ ዘዴ እንዲተገበሩ ሊያስገድዷቸው ይችላሉ።

ከላይ ከተዘረዘሩት አራት ዋና የልጆች አስተዳደግ ዓይነቶች በተጨማሪ አልፎ አልፎ የሚጠቀሱ ዘዴዎችን ቀጥለን እንመልከት።

ልዝብ የአስተዳደግ ዘዴ

(Gentle parenting)

  • የዚህ የአስተዳደግ ዘዴ ዋና ዓላማ አሳዳጊና ልጅ ጠንካራ ትስስር (bond) እና የእርስ በእርስ መተማመን (trust) በመሀከላቸው እንዲዳብር ነው
  • ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የተባባሪነት እንጂ የበላይነት (authority figure) ባህርይ አያሳዩም
  • የልጆችን ስሜት ለመገንዘብ የአሳዳጊዎችን ሀዘኔታና (empathy) ትዕግስት በሰፊው ስለሚጠይቅ በጣም አድካሚ የአስተዳደግ ዘዴ ነው

ነፃነት-ሰጪ የአስተዳደግ ዘዴ

(Free-range parenting)

  • የአሳዳጊዎችን ቁጥጥር ለዘብ በማድረግ ልጆች በነፃነት እንዲያድጉ ይፈቅዳል
  • ከቸልተኛ የልጆች አስተዳደግ ዘዴ ለየት የሚያደርገው ልጆች ደንብና ሥራዓትን እንዲከተሉ ስለሚጠበቅባቸው ነው
  • አካባቢዎቻቸውን በነፃነት እንዲቃኙና ልጆች ለእራሳቸው ገደብ ማበጀትን እንዲለምዱ ዕድል ይሰጣቸዋል

ፓንዳ የአስተዳደግ ዘዴ

(Panda parenting)

ከየሚገራ እና ከነፃነት-ሰጪ የልጆች አስተዳደግ ዘዴዎች ጋር ይመሳሰላል

  • በትዕዛዝና በጥብቅ ደንብና ሥርዓት ከመግራት ይልቅ ልጆች እራሳቸው አስበውና አመዛዝነው ምርጫቸውን አስተካክለው እንዲወስኑ ያስተምራል
  • ወላጆችና አሳዳጊዎች እንደየአስፈላጊነቱ ለልጆች ድጋፍ እንዲሰጡ ይመክራል
  • በወላጆችና በልጆቻቸው መሀል መቀራረብን፣ መከባበርንና እርስበእርስ መተማመንን (trust) ያበረታታል

ሄሊኮፕተር/ አንዣባቢ እና የሣር-ማጨጃ/ደልዳይ የአስተዳደግ ዘዴ

(Helicopter & Lawnmower parenting)

  • ወላጆችና አሳዳጊዎች ከመጠን ያለፈ እንክብካቤ ለልጆች ይሰጣሉ
  • ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆቻቸው ማንኛውም ዓይነት መሰናክል እንዳይገጥማቸው አስቀድመው 'ሁኔታዎችን በመደልደልና በማለስለስ እያመቻቹ' ይንከባከቧቸዋል
  • ልጆቻቸው እንከን ወይም ዕክል ሲያጋጥማቸው ወላጆቻቸው 'በማንዣበብ' ፈጥነው ያድኗቸዋል

እነዚህ የአስተዳደግ መንገዶች ልጆች ከልምዳቸው ወይም ከስህተታቸው የሚማሩበትን ዕድል ስለሚነፍጉ አድገው በእራሳቸው እንዳይተማመኑ ከማድረጉም በላይ ልጆቹ ለችግሮች መፍትሄ ፈልገው የማግኘት ልምዱ ስለማይኖሯቸው ሲያድጉም ይሁን አድገው የእራሳቸውን ሕይወት ሲኖሩ ፍራቻና ጭንቀት (anxiety) እንዲያድርባቸው ይሆናል።

አሳዳጊዎች የሚከተሉትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይመከራል፦

  • ለልጆች መብትና ግዴታቸው ምን እንደሚመስሉ አስቀድሞ በግልጽ ማሳወቅ
  • ለልጆች ምርጫ በመስጠትና አብሮ በመወያየት ተገቢ የሆኑና ያልሆኑ ሁኔታዎችን መለየት
  • ልጆችን በማዳመጥ ስሜታቸውን እንዲገልጹ ማበረታታት -
  • ጥያቄ ከማብዛት ይልቅ "እሺ ሌላስ ምን ሆነ፤ እናስ ምን ተሰማሽ/ህ?" እያሉ ማዳመጥ
  • በተቻለ አጋጣሚ ሁሉ ከልጆች ጋር (ስልክ ሳይኖር - ሙሉ ልብ ሰጥቶ) ጊዜ አብሮ ማሳለፍ
  • ልጆች ሲረበሹ/ሲናደዱ/ ሲቆጡ እራስን በመቆጠብና በዕርጋታ ለመረዳት በመሞከር ልጆቻቸው እራሳቸውን ማረጋጋት እንዲለምዱ ማገዝ
  • አዘውቶሮ ፍቅርን ለልጆች ማሳየትና መግለጽ
  • ልጆችን ለማበረታታት መትጋት - መልካም ነገር ሲያደርጉ፣ ሲሠሩ፣ ሲናገሩ ... ማስተዋልና እንደሰማን/እንዳይየን በኩራት መግለጽ
  • ጉዳት የማያደርስ ሁኔታ ከሆነ ልጆች አጉል ጸባይ ሲያሳዩ ችላ በማለት ማሳለፍ ወይም ትኩረት አለመስጠት
  • በልጆች ፊት ስለሌሎች ሰዎች አሉታዊ አስተያየትን ከመስጠት/ ከመናገር መቆጠብ

ለምሳሌ፦ "የቤትሥራ ካልጨረስሽ ታብሌትሽ አይሰጥሽም!" በማለት ከመቅጣት ወይም ከማስፈራራት ይልቅ "የቤትሥራ ሠርተህ ስትጨርስ ታብሌትህን እሰጥሃለሁ፡፡" ብሎ አስቀድሞ ማስረዳት ልጆችን የሚያበረታታ ስለሆነ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ጥናቶች ያሳያሉ።

ብዙ አሳዳጊዎች ልጆቻቸው አድገው ሕይወታቸው መሳካቱ ወይም አለመሳካቱ የማንነታቸውና የአሳዳጊነት ብቃታቸው ነጸብራቅ እንደሆነ አድርገው በመገመት እንዲሁም "ሰው ምን ይለኛል" በሚል አመለካከት በመገፋፋት ለልጆቻቸው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ሲጥሩና ከአቅማቸው በላይ ሲደክሙ ይታያሉ።

ይሁንና ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው የአሳዳጊዎች ኀላፊነት በተለያዩ አጋጣሚዎች ልጆቻቸው አዳዲስ ነገሮች እንዲሞክሩ ማበረታት፣ ከልምዳቸውና ከስህተቶቻቸው እንዲማሩ ዕድል መስጠት፣ እንዲሁም አድገው የእራሳቸውን ሕይወት ሲቀጥሉ የኑሮን ውጣ ውረድ የመቋቋም ብቃት ኖሯቸው እንደገና ለማንሰራራት የሚያስችል ጥንካሬና ችሎታ እንዲኖራቸው ማዘጋጀት ነው።

ደንብና ሥራዓትን ለልጆች አስቀድሞ ማሳወቅ እጅጉን አስፈላጊ ነው።አሳዳጊዎች አስቀድመው እርስ በእርሳቸው በመወያየት ከልጆቻቸው ምን እንደሚጠብቁና አስተዳደጋቸው ምን መልክ ቢኖረው እንደሚመርጡ ሊስማሙ ይገባል። ደንቦችን በዘፈቀደ የምናወጣና የምንቀይር ከዚያም አጠፋችሁ ብለን የምንቀጣ ከሆነ ልጆች ግራ ይጋባሉ።

ወላጆች ተለያይተው ከሆነስ?

በሁለቱም ቤቶች ቆይታቸው ልጆች ተመሳሳይ ደንብና ሥርዓትን እንዲከተሉ ሁለቱም ወላጆች በቅድሚያ ተስማምተው በግልጽ ለልጆቻቸው ማስረዳታቸውና በቋሚነት ተግባራዊ ማድረጋቸው እጅጉን ወሳኝ ነገር ነው። ልጆች ሁኔታዎች ግልጽ ካልሆኑላቸው ግራ ተጋብተው ይጨነቃሉ፣ ስለራሳቸው ያላቸው አመለካከትና ጸባያቸው ይዛባል፣ እንዲሁም የስነልቦና ጤናቸው ሊታወክ ይችላል።

በልጆቻቸው ፊት አንደኛው ወላጅ ስለሌላኛው ወላጅ ክፉ ከመናገር በመቆጠብ ልጆቻቸውን በተመለከተ አንድ ግንባር እንደሆኑ ማሳየት ይኖርባቸዋል። ስለ ልጆች አስተዳደግ አመለካከታቸው ቢለያይ ወይም ቢጻረን እንኳን ልዩነታቸውን ወደጎን ሊተዉና ለልጆቻቸው ደኅንነት ትኩረትና ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል። ልጆቻቸውን በተመለከተ በሒደት ለሚገጥሟቸው እንቅፋቶችና ፈተናዎች መፍትሔዎችን ተባብረው መፈለጋጀው እጅጉን የሚበጅ ይሆናል።

Read more

'አስተውሎት'  Mindfulness

'አስተውሎት' Mindfulness

ለአሁኒቷ ሰከንድ (present moment) ሙሉ ትኩረት በመስጠት ሀሳባችንን (thoughts)፣ ስሜታችንን (feelings)፣ እና ሕውስታችንን (sensations) የማስተዋል ተግባር ወይም ልምድ ማይንድፉልነስ (mindfulness) በመባል ይታወቃል። በዚህ ጽሑፍ ላይ 'አስተውሎት' ተብሎ ተተርጉሟል። የኑሮን ውጣ ውረድ ለመወጣት አብዛኛዎቻችን ትኩረታችን በየዕለቱ መደረግ የሚገባውን ማከናወናችንን እንጂ ሁኔታዎች በውስጣችን ስለሚያስከትሉት/ስላስከተሉት የስሜት ለውጥ በአብዛኛው የምናስበው ነገር

By TW
ሐዘን ሲተነተን

ሐዘን ሲተነተን

ሐዘን (grief) የምናውቀው፣ የምንቀርበው ወይም የምንወደው ሰው በሞት ሲለየን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ከሕይወት ጋር የተገናኙ ከባድ የማጣት ጉዳቶችን (loss) አስከትሎ የሚከሰት ስሜት ነው። ለምሳሌ፦ * ጤናችን ሲታወክና መፍትሔ የማይገኝለት ሁኔታ ሆኖ የአካላችን ክፍል ወይም አዕምሯችን ሙሉ በሙሉ መዳን ሲሳነው * የትዳር ወይም የፍቅር ወዳጅነት መፍረስ፣ * ከሰዎች ጋር የነበረን ቅርበት በተለያየ ምክንያት ሲታወክና

By TW
ለሥነ-ልቦናና  ለሥነ-አዕምሮ ጤና  ትርኩረት  እንስጥ

ለሥነ-ልቦናና ለሥነ-አዕምሮ ጤና ትርኩረት እንስጥ

የሥነ-ልቦናና የሥነ-አዕምሮ ጤና አገልግሎት ሰጪዎች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ። ለምሳሌ፦ በግል ተቋማት፣ በሆስፒታሎች፣ በክሊኒኮች፣ በድጋፍ መስጫዎች፣ በማገገሚያ ተቋማት፣ በከፍተኛ ትመህርት ተቋማት እና በሌሎችም ሥፍራዎች አገልግሎት ይሰጣሉ። ሳይኮተራፒ  (psychotherapy) የአስተሳሰብ፣  የባህርይ ፣  የተግባር፣  እንዲሁም  የማሕበራዊ  ኑሮ ግንኙነት  አዎንታዊ  ለውጦችን  ለማስገኘት የሚያገለግል የሥነ-ልቦና ዕርዳታ መስክ ሲሆን በመወያተትና  በመመካከር (talk therapy) ላይ የተመሠረተ የሞያ

By TW
ኮንሴንት ምንድን ነው?

ኮንሴንት ምንድን ነው?

ኮንሴንት = ፈቀደ፣ ተስማማ፣ እሺ አለ - ማለት ነው። (አቢሲኒካ መዝገበ ቃላት) https://dictionary.abyssinica.com/consent ኮንሴንት (Consent) በዓለም-አቀፍ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ደንቦችና ሕግጋት ላይ የተመሠረት ደንብና ልማድ ሲሆን ማንም ሰው አካሉን/ አከላቱን አስመልክቶ በሕይወቱ፣ በጤናው፣ በወሲባዊ ግንኙነቱና ሌሎችም ከአካል ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች ዙሪያ ራሱ በራሱ የመወሰን ሙሉ ነጻነት እንዳለው

By TW