የኦቲዝም ቁጥር መጨመር - ኦቲዝም መዕራፍ ፩

Share
የኦቲዝም ቁጥር መጨመር - ኦቲዝም መዕራፍ ፩
Photo by Hiki App / Unsplash

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም. መጀመሪያ ከአንድ መቶ ሃምሳ ልጆች መሀከል አንድ (150፡1) ኦቲስቲክ ልጅ ይገኝ እንደነበረና ከሃያ ዓመታት በኋላ ይህ ቁጥር በሶስት እጥፍ ያህል ጨምሮ በ2020 ዓ.ም. ከሰላሳ ስድስት ልጆች መሀል አንድ (36፡1) ኦቲስቲክ ልጅ መገኘቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኦቲዝም ቁጥር መጨመር ምክንያቱ ምን እንደሆነ ከመመልከታችን በፊት ኦቲዝምን አስመልክቶ ያሉትን ግንዛቤዎች በጥቂቱ እንዳስስ።

(ስለ ኦቲዝም ብዙ የምንነጋገርባቸው ነጥቦች እንዳሉ በመገንዘብ ወደፊት ሌሎች አርዕስቶችን ይዘን እንደምንመለስ አስቀድመን እናሳውቃለን።)


ኦቲዝም - ከየት ወዴት

ከ1940 - 1960 ዎቹ ዓመታት (እ.አ.አ.)

የኦቲዝም ምልክቶች አልፎ አልፎ የሚታዩ ስለነበሩና ከሃያ አምስት ሺህ ልጆች መሃል አንድ ሁኔታውን የሚያሳይ ልጅ ይገኝ ስለነበረ የአዕምሮ በሽታ እንዳለበት ሆኖ ተቆጥሮ ሁኔታው ከስኪዞፍሬንያ ጋር ተደምሮ ይታይ ነበረ።

በ1980 ዎቹ (እ.አ.አ)

የኦቲዝም ምልክቶች ከስኪዞፍሬንያ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ስለተገመገመ በነጠላ ፈርጅ ኦቲዝም ዲዞርደር (autim disorder) ተብለው እንዲጠቃለሉ ተወሰነ።

በ1990 ዎቹ (እ.አ.አ)

  • ኦቲዝም በዘር ሊወረስ የሚችል ኒውሮሎጂያዊ ልዩነት ወይም የነርቮች አወጣጠር ልዩነት (neurological difference) እንደሆነ ጥናታዊ መረጃዎች አረጋገጡ። አንዳንድ የኦቲዝም ዲዞርድር ምልክቶች የሚገኝባቸው ሰዎችም ጤናማ የአዕምሮ ብስለት እንደሚያሳዩ፣ ከዚያም አልፎ የረቀቀ አስተሳሰብና ልዩ ችሎታ ወይም ተሰጥዖ ሊኖራቸው እንደሚችል እየታወቀ በመምጣቱ አስፐርጋርስ ሲንድረም (Asperger's syndrome) በሚል ስያሜ እንዲለዩ ሆነ። (ይህ ስያሜ ጊዜው ያለፈበት ስለሆነ በአሁኑ ወቅት አንጠቀምበትም።)
  • የኦቲዝም ምልክቶች በተለያየ መልክ ሊገለጹ እንደሚችሉና ኦቲስቲክ ሰዎች ደግሞ ዋሕድ ዘር/ጋነገብ ወይም አንድዓይነት አለመሆናቸው ሲታወቅ ልዩነታቸው አንዳለ ሆኖ ሁሉም በኦቲዝም ስፔክትረም ዲዞርደር - ኤ.ኤስ.ዲ. (autism spectrum disorder - ASD) አንድ የጃንጥላ ጽንሰ-ሀሳብ ሥር እንዲካተቱ ተደረገ።

በ2000 ዎቹ (እ.አ.አ.)

ኦቲዝም በሰዎች መሀከል የሚገኝ የነርቮች ድር አወጣጠር ልዩነት ነው የሚል አስተሳሰብ እየገነነ መጥቷል። የዚህ አመለካከት አርአያ ኒውሮዳይቨርሲቲ ፓረዳይም (neurodiversity paradigm) ሲሆን ኦቲዝም - እንደ ግራኝነት - በሰዎች መሀከል ከሚገኙ በርካታ ልዩነቶች ረድፍ ሊደመር ይገባል በሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው።

የኒውሮዳይቨርዚቲ ፓረዳይም አቋም

  • ሰዎች ስንባል ትክክለኛ ወይም ኖርማል በሚባል መመዘኛ አንለካም - ሁላችንም የተለያየን ነን።
  • አንጎል ወይም የነርቮች ድር አወጣጠር ከሰው-ሰው ይለያያል - አንዱ ከሌላኛው የተሻለ ወይም ያነሰ አይደለም።
  • ኦቲዝም የተፈጥሮ ብዝሃ-ሕይወት (ባዮዳይቨሲቲ - biodiversity) አንዱ አካል ነው፣ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ኦቲዝም የማንነት አንዱ ገጽታ ነው።
  • ሰውን አቅመ-ውሱን የሚያደርገው (disability) ተፈጥሮውና ማንነቱ ሳይሆን በዚያ ሰውና በአካባቢው መሀከል የሚኖረው አለመጣጣም ወይም አለመስማማት ነው - አካባቢን ለኦቲስቲክ ሰዎች ማመቻቸት የሕክምና ዕርዳታ አንዱ ዋና ተግባር ሊሆን ይገባል።
  • በሰዎች መሀከል ልዩነቶች እንዳሉ ሁሉ ጥንካሬዎችም ይገኛሉ።
  • የኒውሮዳይቨርሲቲ ዓላማና ግብ ኦቲስቲክ ሰዎች ሙሉ-በሙሉ እራሳቸውን መሆን እንዲችሉ ማገዝና ሕይወታቸውን እነርሱ በሚመርጡት መንገድ እንዲመሩ ሁኔታዎችንና አካባቢያቸውን ማመቻቸት ነው።
  • ኦቲዝም እንደበሽታ መታየቱ እንዲቆም ሕዝብን ማስተማርና ማንቃት ያስፈለጋል።

ኦቲስቲክ ሰዎች የአካባቢያቸው ሁኔታ የሚያስከትልባቸው ውጥረት ከአቅማቸው በላይ ሲሆን ስሜታቸውን ለመግራት ተስኗቸው ኦቲስቲክ ባልሆኑት የኅብረተስብ አባላት አመለካከት ተቀባይነት የሌላቸውን ባህርያት ሊያሳዩ ይችላሉ።

ትኩረታችንን በእነዚህ ባህርያት ላይ ስናደርግና በኦቲስቲክ ሰዎች ላይ አካባቢያቸው ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ሳናስገባ ስንቀር ለኦቲስቲክ ሰዎች የባህርይ ለውጥ ምክንያቱ ኦቲዝሙ ነው የሚል የተሳሳተ ውሳኔ ላይ ልንደርስ እንችላለን።

የኒውሮዳይቨርሲቲ ፓረዳይም አርአያነት የሚከተሉትን ያጎላል፦

  • ዓለም ኦቲስቲክ ባልሆኑ (non-autistics) ሰዎች የተቀረጸች ስለሆነች ለኦቲስቲክ ሰዎች የምትመች አለመሆኗን፣
  • ኦቲስቲክ ሰዎች ከአካባቢያቸው ሁኔታ ጋር የማይስማማ የነርቭ ድር አወቃቀር እንዳላቸው፣
  • እንዲሁም አካባቢያቸውን ወይም ኦቲስቲክ ያልሆኑ ሰዎችን ለመምሰል በሚያደርጉት ጥረት ከባድ የመንፈስ ውጥረት (stress) ሊያድርባቸው እንደሚችል

ኦቲዝም ምን ይመስላል?

"እኔ ኦቲዝም ያለብኝ ሰው አይደለሁም። ኦቲዝም ከእኔነቴ ጋር የተዋሃደ ማንነቴ ነው እንጂ። ስለሆነም ኦቲዝም በእያንዳንዷ የሕይወቴ ቅጽበት ውስጥ በሚኖረኝ አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ግንዛቤ ላይ ተጽዕኖ አለው።" (ስለ ኦቲዝም መብት ተሟጋች የሆኑ አንድ ሰው ከተናገሩት የተቀነጠበ)

ብዙ ሰዎች (በርካታ የጤና ባለሞያዎችን ጨምሮ) ስለኦቲዝም ያረጀና ጊዜው ያለፈበት አመለካከት አላቸው። ማለትም - የሌላን ሰው ዓይኖች በቀጥታ የማይመለከቱ፣ ለየት ያለ ባህርይ የሚያሳዩ፣ የአዕምሮ ዝግመት የሚታይባቸው፣ መናግር የማይችሉና ሙሉ ሰዓት የሌላ ሰው እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ድኩማን ናቸው የሚል የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው ብዙኃን ናቸው።

የተሳሳቱ አመለካከቶችን እንመርምር

  • "ኦቲዝም ልጆች ሲያድጉ የሚጠፋ ሁኔታ ነው።" - አይደለም! ይህ አመለካከት ፈጽሞ የተሳሳተ ነው። ኦቲዝም የዕድሜ ልክ ሁኔታ ነው።
  • "ኦቲዝም የበለጠ በወንዶች ዘንድ የሚከሰት ሁኔታ ነው።" - በብዙ የሚቆጠሩ ኦቲስቲክ ሴቶች ሳይታወቅላቸው ይቀራል፣ አለዚያም ደግሞ ኦቲስቲክ መሆናቸው የሚታወቀው እጅግ ዘግይቶ ነው።
  • "ኦቲስቲክ ሰዎች ለሰዎች ርኅራሔ (empathy) የላቸውም።" - ይህ አባባል ከእውነት የራቀ ነው። በርካታ ኦቲስቲክ ሰዎች የላቀ ውስጣዊ ስሜታዊነትና ለሌሎች አዘኔታ ሊሰማቸው ይችላል።

የሚከተሉትን ማስተዋል ይገባል፦

  • በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት ያለው የኦቲዝም ትክክለኛው አጠራር ኦቲዝም ስፔክትረም ዲዞርደር (autism spectrum disorder) ነው። ከኦቲዝም ጋር ሊከሰቱ በሚችሉ ጉዳቶችና ለመፍትሔዎቻቸው ትኩረት እንዲሰጥ በመሻት ኦቲዝም ስፔክትረም ዲዛቢሊቲ (autism spectrum disability) የሚለውን አጠራር የሚመርጡም አሉ።
  • የኦቲዝም መከሰት ምክንያት ይህ ነው ተብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ይሁንና ልጅ የሚያድግበት የአካባቢ ሁኔታ እንዲሁም የዘር ጂኖች በመተባበር በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ኦቲዝም ሊከሰት ይችላል ተብሎ ይታመናል።
  • ኦቲስቲክ ሰዎች የተለያዩ ባህርዮችን ሊያሳዩ ይችላሉ። ለምሳሌ፦
    • ከሰዎች ጋር መስተጋብር ሊያዳግታቸው ይችላል
    • ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላ ሁኔታ መሸጋገር ወይም ለውጥ ሊከብዳቸው ይችላል
    • ለጥቃቅን ሁኔታዎች ትኩረት የመስጠት ባህርይ ሊያሳዩ ይችላሉ
    • ወዘተ
  • የኦቲስቲክ ሰዎች ችሎታ፣ ፍላጎትና ሁኔታ የአንዳቸው ከሌላኛቸው ሊለያይ ይችላል።
    • ከፊሎቹ እራሳቸውን ችለው በብቃት መኖር ሲችሉ የቀሩት ደግሞ የዕድሜ ልክ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሊሆኑ ይችላሉ
    • በትምህርትና በሥራ ዓለም ላይ ተጽዕኖ ሊያጋጥማቸው ይችላል
    • ብዙ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ኦቲስቲክ ሰዎች መንከባከብ በቤተሰብ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል
  • የኦቲዝም ምልክቶች የሚታዩት በልጅነት ዕድሜ ነው። ይሁን እንጂ ኦቲዝም እንዳላቸው ሳያውቁ ቆይተው አድገው በዐዋቂ ዕድሜያቸው ሁኔታው የሚታወቅላቸው ሰዎች ቁጥራቸው እየበረከተ መጥቷል።
  • የኦቲስቲክ ሰዎች የአዕምሮ ብስለት ከዝቅተኛ እስከ እጅግ የላቀ ደረጃ የተለያየ ሊሆን ይችላል።
  • ኦቲስቲክ ሰዎች የተለያዩ የአዕምሮ ጤና ሁኔታዎች በተደራቢነት ሊኖሯቸው ይችላል። ለምሳሌ፦ ጭንቀት፣ ድባቴ፣ የማስተዋል ብቃት መዛባት (ADHD)፣ ወዘተ

ከኦቲዝም ጋር የሚታዩ ሁኔታዎች

  • የአካባቢያቸው ሁኔታዎች በስሜቶቻቸው ላይ ከባድ ተጽዕኖ ሲያሳድሩባቸው ኦቲስቲክ ሰዎች የመረበሽ ወይም እራሳቸውን የማግለል ባህርይ ሊያሳዩ ይችላሉ። (ለምሳሌ፦ ድምፅ፣ ብርሐን፣ ወ.ዘ.ተ. ሊያውካቸው/ሊረብሻቸው ይችላል።)
  • የኦቲስቲክ ሰዎች ለጥቃቅን ነገሮች/ሁኔታዎች ትኩረት የመስጠት ባህርይ ኦቲስቲክ ካልሆኑ ሰዎች አመለካከት ጋር ላይጣጣም ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ትኩረታቸው ጥራት ያለውና ስኬታማ ውጤት ስለሚያስገኝላቸው በአንዳንድ የሥራ መስኮች ተፈላጊ ያደርጋቸዋል ።
  • ንግግራቸው ቀጥተኛና ፊትለፊት ሊሆን ይችላል፣ ሰዎች የሚሉትንም በቀጥታ የመተርጎም ዝንባሌ ሊያሳዩ ይችላሉ። ስለዚህ ቀልድ ወይም ተረብን ያካተቱ አነጋገሮችን መገንዘብ ሊያዳግታቸው ይችላል።ይህም አለመግባባትን ሊያስከትልና የኦቲስቲክ ሰዎችን ውጥረት (stress) ሊያባብስ ይችላል።
  • በአንድ ነገር ላይ ከመጠን ያለፈ የማተኮርና የላቀ የማወቅ ፍላጎት/ዝንባሌ ሊኖራቸው ይችላል። ያም ከአንድ ሀሳብ ወደ ሌላ በቀላሉ መሸጋገር እንዲሁም ለውጥን መቀበል እንዲያዳግታቸው ሊያደርግ ይችላል።

የኦቲዝም ቁጥር መጨመር

በአለፉት ሃያ ዓመታት የኦቲስቲክ ልጆች ቁጥር በየሁለት ዓምቱ ከ10 እስከ 20 በመቶ እያደገ የመጣበትን ምክንያት በሜሪላንድ የኤፒዴሚዮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት Christine Ladd-Acosta እንደሚከተለው ያብራራሉ ።

  • ኦቲዝምን ለመለየት የምንጠቀምበት መስፈርት ሰፋ እንዲል በመወሰኑ በመስፈርቱ የሚታቀፉ ሰዎች ቁጥራቸው እንዲጨምር ምክያት ሆኗል።
  • የጤና ባለሞያዎች ከ18 እስከ 24 ወር ዕድሜ ያላቸውን ሕፃናት ኦቲዝም ይኖራቸው እንደሆነ ለማጣራት ስለሚመረምሯቸው ኦቲዝም የመገኘት ዕድሉ ከፍ እንዲል ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።
  • የጤና ትምህርት በመጠናክሩና ሰዎች ስላኦቲዝም ያላቸው ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ ወላጆች የኦቲዝምን ምልክቶች ለይተው ማወቅ ችለዋል። ስለዚህም ልጆቻቸው ኦቲዝም ሊኖራቸው ይችል ይሆን ብለው ከጠረጠሩ ቶሎ ሐኪም ዘንድ ወስደው ያሳይዋቸዋል። ይህ ሁኔታ የኦቲዝም ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽዖ አድርጓል።
  • ኦቲዝም በብዙ ማህበረሰቦች ውስጥ ተቀባይነት እየኖረው መጥቷል። ስለሆነም ሰዎች ኦቲዝምን አስመልክቶ የጤና ባለሞያዎችን ዕርዳታ የመጠየቅ ድፍረት አግኝተዋል።
  • በተጨማሪም ሥውር ወይም በዓይናችን የማናያቸውን የኦቲዝም ምልክቶች ለማግኘት የተሻለ ዕውቀት፣ የመመርመሪያ ዘዴና ብቃት እየኖረን ስለመጣ ወትሮ በቀላሉ ልንስታቸው የምንችላቸውን የኦቲዝም ምልክቶች መለየት መቻላችን ለኦቲዝም ቁጥር ማደግ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።

መረጃዎች

https://publichealth.jhu.edu/2025/is-there-an-autism-epidemic

Understanding autism data in the Canadian Chronic Disease Surveillance System — Canada.ca
A resource to support the understanding and use of autism data.
What is Autism, Really? | Understanding Autism
A comprehensive guide to autism, ADHD, and neurodivergence - Brain science, coping strategies, and pathways to thriving

የአንድ የኦቲዝም ወላጅ ተሞክሮ

Read more

ኦቲዝምና የቤተሰብ ተሞክሮ -  ኦቲዝም ምዕራፍ ፫

ኦቲዝምና የቤተሰብ ተሞክሮ - ኦቲዝም ምዕራፍ ፫

ኦቲዝም የዕድሜ-ልክ ሁኔታ እንደሆነና መልኩ ወይም አገላለጹ ከሰው ሰው ሊለያይ እንደሚችል በምዕራፍ አንድ እና ሁለት ለማየት ችለናል። በዝርዝር ከተመለከትናቸው ዋና ዋና ነጥቦች መሀከል ጥቂቶቹን ለማስታወስ፦ * ኦቲዝም መሠረቱ የነርቮች ድር የአወጣጣር ልዩነት ሲሆን የአዕምሮ ብስለት ዝግመትን አለዚያም ደግሞ ረቂቅ የሆነ ተሰጥዖንና ልዩ ችሎታዎችንም ሊያካትት ይችላል። * ኦቲዝም ሥውር ሆኖ ሳይታወቅ ሊቀር

By TW
የመግደርደር ባህል ልጆችንና ሴቶችን ለጥቃት ያጋልጣል

የመግደርደር ባህል ልጆችንና ሴቶችን ለጥቃት ያጋልጣል

በቀላሉ ወይም ወዲያው "እሺ!" ወይም "አዎን!" በማለት ፍላጎትን መግለጽ እንደነውር ተቆጥሮ እየፈለጉ "አልፈልግም!" እያሉ በመግደረደር እንዲለመኑ መንገድ መክፈት በአንዳንድ የሕብረተስብ ክፍሎች ውስጥ አክብሮትን፣ ትሕትናንና ጨዋነትን የሚያመለክት ባህል ነው። መግደርደርን እንደ ባህል ለማይተገብሩ ሰዎች ግን ግራ የሚያጋባና አንዳንዶችን ደግሞ ለጥቃትና ለጉዳት የሚያጋልጥ ልማድ ነው። (አስተያየትዎን

By TW
"ይቅር ተባባሉ!"

"ይቅር ተባባሉ!"

"ይቅርታ ምንድን ነው ካልተስተካከለ፣ እሾህ አሜከላ ሆድ እያበቀለ? ..." "ይቅርታ እለምናለሁ፣ ጥፋቴን አውቅያለሁ። ..." (ጥላሁን ገሠሠ) "አንተም ተው! አንቺም ተይ! እናንተም ተዉ! ይቅር ተባባሉ" በማለት ሰዎች የተሰማቸውን ቅሬታ ወይም የደረሰባቸውን በደል ትተው ከበደላቸው ሰው ጋር ሰላም እንዲፈጥሩ መምከር በባህላችን የተለመደ ነገር ነው። አንዳንዶቻችን ለግጭቶች መፍትሔ ሳይገኝላቸው

By TW
የቤተሰብ አባላት መጠማመርና መነጣጠል - ክፍል ፪

የቤተሰብ አባላት መጠማመርና መነጣጠል - ክፍል ፪

የቤተሰብ መነጣጠል (Disconnection - ዲስኮኔክሽን) በክፍል አንድ የቤተሰብ አባላት በመሀከላቸው በሚኖረው የእርስ በእርስ ጠንካራ መተሳሰር፣ መተባበርና መረዳዳት ላይ ብቻ በማተኮር ለየግል ስሜቶቻቸው ተገቢውን ቦታና ትኩረት ሳይሰጡ በሚቀሩበት ጊዜ፣ እንዲሁም አንዳቸው የሌላኛቸውን ስሜት እንደ የእራሳቸው አድርገው በሚወስዱበት ወቅት መጠማመር ወይም ኢንሜሽመንት ሊከሰት እንደሚችል ለመረዳት ችለናል። አሁን ደግሞ የመነጣጠልን ባህርይ የሚያንጸባርቁ የቤተሰብ አባላት

By TW