በመምታት ልጆችን መቅጣት? - አስተዳደግ ክፍል ፪

በመምታት ልጆችን መቅጣት?                                        - አስተዳደግ ክፍል ፪
Photo by Jess / Unsplash

በ1989 እ.ኤ.አ. በተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ 196 አገራት የልጆችን ሰባዓዊ መብቶች የሚያስጠብቅ ስምምነት ተፈራርመዋል (United Nations Conventions on the Rights of the Child - UNCRC)። ይህንን ስምምነት ኢትዮጵያና ካናዳ - በ1991 (እ.ኤ.አ.)፣ ኤርትራ ደግሞ በ1994 (እ.ኤ.አ.) በሕጎቻቸው ውስጥ አካትተው አጽድቀዋል።

የሚከተሉትን የስምምነት አንቀጾች እንመልከት፦

  • አንቀጽ ፲፱ (19) - ልጆች በወላጆቻቸው፣ በአሳዳጊዎቻቸውና በማናቸውም የልጆች እንክብካቤ ሰጪ ሰዎች አካላዊ ወይም አዕምሯዊ ተጽዕኖ(abuse)፣ጥቃት(violence)፣ ቸልተኝነትና (neglect) በደል (maltreatment) ፣ እንዲሁም ወሲባዊ በደል (sexual abuse) እንዳይደርስባቸው ፈጽሞ የተጠበቁ መሆናቸው መብታቸው ነው።
  • አንቀጽ ፳፬ (24) - ልጆች ጤናቸው በከፍተኛ ደረጃ የተጠበቀ ሆኖ ማደጋቸው መብታቸው ነው።
  • አንቀጽ ፳፯ (27) - የልጆችን የአካልና የአዕምሮ ጤና ዕድገት ለመጠበቅና ለመንከባከብ መሠረታዊ ቁሳቁሶች እንዲሟሉላቸው ተደርጎ ማደጋቸው መብታቸው ነው።
  • ንቀጽ ፴ (30) - ማናቸውም ከህዳጣን ወይም ከአናሳ ብሔረሰብ (minority) እንዲሁም ከአገር በቀል (indigenous) ዘር ተወላጅ የሆኑ ልጆች የባሕል፣ የዕምነት፣ እንዲሁም የቋንቋ ነፃነታቸው ተጠብቆ ማደጋቸው መብታቸው ነው።

ከዚህ በታች ያሉትን አባባሎች ደግሞ እንመርምር፦

  • "አሳዳጊዎቼ ሁልጊዜ እንደተቹኝ፤ ስለእኔ ያላቸውን ቅሬታና ምሬታ ነጋጠባ እየነገሩኝ ነው ያደግሁት።"
  • "እንደ ሌሎች ልጆች ሳልጫወት ኀላፊነት ተሸክሜ ነው የልጅነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት።"
  • "ቤተሰቦቼ ከመጠን በላይ እየተቆጣጠሩኝ ነው ያሳደጉኝ።"
  • "የእኔ ወላጆች መብላት መጠጣቴን እንጂ የት ሄድኩ፣ መቼ መጣሁ፣ ከማን ጋር ምን ሳደርግ ውዬ ገባሁ፣ ምንም ደንታ ሳይሰጣቸው መረን ተለቅቄ ነው ያደግሁት።"
  • "በብቸኝነት ማንም ሳይመለከተኝና ሳይደግፈኝ፣ የወላጅና የአሳዳጊን ጣዕም ሳላውቅ ነው የልጅነት ዕድሜዬን ያሳለፍኩት።"
  • "በየምክንያቱ እየተቀጣሁ/እየተገረፍኩ/እየተደበደብኩ በሰቀቀን ነው ያደግሁት።"

በቅርቡ አንድ ለቅሶ ላይ ጨዋታ ተነስቶ አንድ ወላጅ - "ልጆቼን (በካናዳ ውስጥ) በደንብ ገርፌ ነው ያሳደግኋቸው። እኔም ተገርፌ ነው ያደግሁት፤ ምንም አልተጎዳሁም፣ ልጆቼም አይጎዱም።" - በማለት ልጆችን በግርፊያ መቅጣት ትክክል እንደሆነ ለማሳመን የሞከሩበትን አጋጣሚ እንደ ተጨማሪ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

ምንም እንኳን በአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልማዶች፣ ተሞክሮዎችና አመለካከቶች መሠረት ልጆችን መግረፍ ተቀባይነት ያለው የቅጣት መንገድ ቢሆንም ከፍ ብሎ እንደተመለከትነው አንቀጽ ፲፱/19 እና ፳፬/24 የደነገጉትን ይቃረናል። ስለሆነም የልጆችን ሰብዓዊ መብቶች የሚረግጥ ልማድ እንደሆነ ማስተዋል ይገባል።

ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉባቸው መንገዶች የአንዳቸው ከሌላኛቸው ለየት ሊሉ እንደሚችል በክፍል ፩ በቀረበው የጦማር ጽሑፍ ላይ ተብራርቷል። ፍጹም የሆነ አሳዳጊነት ወይም አስተዳደግ ሊኖር እንደማይችልም ለመረዳት ችለናል።

ይሁንና አንዳንድ አሳዳጊዎች ሆን ብለውም ይሁን ሳያውቁ በሁኔታቸው (ለምሳሌ ልጅን ፊት በመንሳት)፣ በንግግራቸውና (ለምሳሌ ልጅን በማንቋሸሽ) በድርጊቶቻቸው (ለምሳሌ ልጅን በመግረፍ ) ወይም ተገቢውን የአሳዳጊነት እንክብካቤ ልጆችን በመንፈጋቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፉ የሚችሉ ጉዳቶች ሊያደርሱ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ።

የትኛዎቹ ሁኔታዎችና የአስተዳደግ መንገዶች በልጆች ላይ በደልና አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ቀጥለን እንመለከታለን።

ቀዝቃዛ አስተዳደግ

(Cold parenting)

  • አሳዳጊዎች ስሜቶቻቸውን ያግዳሉ ወይም ስሜታቸውን አይገልጹም
  • ልጆቻቸውን አይቀርቡም፣ ለቀልድና ጨዋታ ዕድል አይሰጡም
  • ስለልጆቻቸው ፍላጎቶች፣ ስሜቶች፣ ተሞክሮዎች፣ ውጤቶችና ግቦች ግድ እንደሚሰጣቸው አያሳዩም/አይገልጹም
  • ልጆቻቸው ስሜታቸውን ወይም አስተሳሰባቸውን ሲገልጹ/ለመግለጽ ሲሞክሩ ንቀት ያሳያሉ ወይም ይተቻሉ

የአሳዳጊዎቻቸውን ፈለግ በመከተል ሰዎች ስሜቶቻቸውን (ሀዘን፣ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ወዘተ) እንዲያፍኑ/እንዳይገልጹ/እንዲያግዱ ይሆናሉ። ለሁሉ ነገር የሚሸማቀቁና እራሳቸውን ከሰው ሁሉ ዝቅ አድርገው የሚያዩ ሆነው የሌሎችን ፍላጎቶች የማስቀደም (people-pleasing) እንዲሁም የሽቁጥቁጥነት ባህርይ ያሳያሉ።

ቁጥጥር የበዛበት አስተዳደግ

(Controlling parenting)

  • አሳዳጊዎች ሁሉ ነገር እነርሱ በሚፈልጉትና በሚፈቅዱት መንገድ ብቻ እንዲሆን ይጠብቃሉ/ያስገድዳሉ
  • ፍቅራቸውን የሚገልጹት/የሚያሳዩት ልጆቻቸው ያለጥያቄ ሲታዘዟቸው ወይም ውጤት ሲያመጡና ስኬት ሲያሳዩ ብቻ ነው
  • ልጆቻቸው ምን እንደሚፈልጉ/እንደሚያስፈልጋቸው ለማወቅ እጅግም ፍላጎት አያሳዩም
  • ልጆቻቸውን ያስፈራራሉ፣ ይተቻሉ፣ ያለአግባብ ይቀጣሉ፤ በጉቦ ያስገድዳሉ
  • ልጆቻቸው እራሳቸውን ችለው ማድረግ ለሚችሉት ነገር ዕድል አይሰጧቸውም
  • ልጆቻቸውን እንደ የእራሳቸው ነጸብራቅ ወይም ተቀጥያ አድርገው ስለሚያዩአቸው ጭነትና ቁጥጥር ያበዙባቸዋል

ይህ አስተዳደግ ሰዎች የእራሳቸውን ውሳኔ የመወሰን ችሎታቸውን ስለሚገድብ ዘዎትር የሌሎችን ሰዎች አስተያየትና ሀሳብ የሚጠይቁ ይሆናሉ። ጭንቀት፣ ድብርትና ሌሎች የስነ-ልቦና ተጽዕኖዎች እንዲያድሩባቸው፣ ከሰዎችም ጋር እንዲቃቃሩ ምክንያት ይሆናል።

ትችት የበዛበት አስተዳደግ

(Critical parenting)

  • አሳዳጊዎች ከልጆቻቸው ፍጹምነትን ይጠብቃሉ
  • ለጥፋት ትኩረት በመስጠት ልጆቻቸውን ይተቻሉ፣ አጉል ስም ይሰጣሉ/ይሳደባሉ
  • ልጆቻቸውን ከሌሎች ልጆች እያወዳደሩ በመንቀፍ ሊቆጣጠሯቸው ይሞክራሉ
  • በአነጋገራቸው ልጆቻቸው ስሜታቸው ሊጎዳ ወይም ቅር ሊላቸው እንደሚችል ከግምት ውስጥ አያስገቡም

ይህ ዓይነት አስተዳደግ ሰዎች የበታችነትና የችሎታ ማነስ/አልባነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል። ፍጹምነትን (perfectionism) ፍለጋ ከአቅማቸው በላይ ሲጥሩ ጭንቀት፣ ድብርትና፣ ተስፋ የመቁረጥ ስሜቶች ያድሩባቸዋል። በእራሳቸው ብቃት ስለማይተማመኑ ሌሎችን ሰዎች በጥርጣሬ ዓይን ይመለከታሉ። ስለሆነም ከሰዎች ጋር በቀላሉ ይጋጫሉ።

ግፊት የበዛበት አስተዳደግ

(Demanding parenting)

  • አሳዳጊዎች በሁሉም መስክ ከፍተኛ ውጤቶችን ስለሚጠብቁ በልጆቻቸው ላይ ከባድ ግፊት ያሳድራሉ
  • ስህተቶችን በቀላሉ አያልፉም
  • በማስፈራራት፣ በመቅጣትና ፍቅራቸውን በመንፈግ ልጆቻቸው ትዕዛዛቸውን ያለ ምንም ጥያቄ እንዲከተሉ ያስገድዳሉ
  • ልጆቻቸው ምን እንደሚያስቡ ለመረዳት አይሞክሩም፣ ወይም ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ፍላጎት አያሳዩም
  • ስለእራሳቸው፣ ስለልጆቻቸውና ስለቤተሰቦቻቸው ሌሎች ሰዎች ስለሚኖሯቸው አስተያየቶች ቦታና ትኩረት ስለሚሰጡ በየአጋጣሚው ስኬቶቻቸውንና ውጤታማነታቸውን ለማሳየት ሲሉ ልጆቻቸው ላይ ጭነት ያሳድራሉ።

ይህ ዓይነቱ አስተዳደግ ልጆች አድገው ሥርዓት ያላቸው ሰዎች እንዲሆኑ አድርጎ ይገራል። ቅጣትን ፍራቻ ትዕዛዞችንና ደንቦችን ያለማወላወል/ ያለ ምንም ጥያቄ የሚከተሉ ይሆናሉ። ጭንቀት፣ ድብርትና ዝቅተኛ በራስ መተማመን ኖሯቸው ውሳኔዎችን የመወሰን ችሎታና ብቃት ስለሚያጥራቸው ስሜታቸውን ለመግዛት ይሳናቸዋል፣ በቀላሉም የሚቆጡ/የሚናደዱ ይሆናሉ።

ርቀት-አዘል አስተዳደግ

(Distant parenting)

ከቸልተኛ አስተዳደግ (neglectful parenting) ጋር ተመሳሳይነት አለው። (አስተዳደግ - ክፍል ፩ን ይመልከቱ)

  • አሳዳጊዎች በጤናማ መልኩ ከልጆቻቸው ጋር ቅርበት ሳይኖራቸው ሲቀር
  • በችሎታና በብቃት ዕጥረት ተገቢውን ድጋፍ እየሰጡ ልጆቻቸውን በሥርዓት መንከባብ ሲሳናቸው
  • በሥራ ወይም በሌሎች ጉዳዮችና ኀላፊነቶች ተወጥረው ለልጆቻቸው በቂ ጊዜ መስጠት ካልቻሉ
  • የአዕምሮ እንዲሁም የአካል ጤናቸው በመጓደሉ፣ አለዚያም በመጠጥና በአደንዛዥ ዕጾች ሱሰኝነት ምክንያት ለልጆቻቸው ትኩረት መስጠት ሲሳናቸው

ይህ ዓይነቱ አስተዳደግ በልጆች ላይ አሉታዊ የጸባይ ወይም የባህርይ ለውጥ ስለሚያስከትል የትምህርታቸውን ሂደት ከማወኩም በላይ አድገውም በግል ሕይወታቸው፣ በሥራ ዓለም፣ በግልና በማሕበራዊ ኑሮ ግንኙነቶቻቸው ከሰዎች ጋር መግባባት እንዲያቅታቸው ምክንያት ይሆናል።

ጣልቃ-ገብ አስተዳደግ

(Intrusive parenting)

  • ከሚገባው በላይ በልጆች ላይ ቁጥጥር ማብዛት
  • ልጆች ዕርዳታ ሳያስፈልጋቸው ወይም ሳይጠይቁ ተቻኩሎ ማገዝ
  • ለልጆች ያለአግባቡ ወይም ከመጠን በላይ መጨነቅና መጠበብ
  • ልጆችን ማስጨነቅ
  • ልጆች በአቅማቸው ማድረግ ከሚችሉት በላይ ብዙ ከእነርሱ መጠበቅና መተቸት
  • ልጆች ሲሳሳቱ ማንቋሸሽና ማዋረድ

ጣልቃ-ገብ አስተዳደግ ልጆች ዕድሜያቸውን በሚመጥን ሁኔታ ሊኖሯቸው የሚገባቸውን ዕድገት በማገድ ብስለታቸውን ይገታል። አድገውም እራሳቸውን በትንሽ-በትልቁ እንዲተቹና በእራሳቸው እንዳይተማመኑ፣ እራሳቸውን እንዲያገሉና ከአዲስ ተሞክሮዎች እንዲሸሹ ምክንያት ይሆናል።

አቀማጣይ አስተዳደግ

(Overinvolved parenting)

ከአንዣባቢና ከደልዳይ አስተዳደጎች (helicopter & lawnmower parenting) ጋር ተመሳሳይነት አለው (አስተዳደግ - ክፍል ፩ን ይመልከቱ)

  • አሳዳጊዎች ለልጆቻቸው ሁሉን ነገር ያመቻቻሉ
  • ልጆቻቸው ኀላፊነት ወስደው ማድረግ የሚችሉትን በመጋፋትና ጣልቃ በመግባት ሁኔታዎችን ያከናውናሉ/ይፈጽማሉ
  • አሳዳጊዎች የእራሳቸውን በራስ አለመተማመን፣ ፍርሃትና ጭንቀት (anxiety) ለማቃለል ሲሉ ልጆቻቸውን ይጎዳል ብለው ካሰቡት/ከፈሩት ነገር በማንዣበብ እየተከላከሉና ከመጠን በላይ እየተንከባከቡ ያቀማጥሏቸዋል

ይህ ዓይነቱ አስተዳደግ ሰዎች በይገባኛል ትዕቢት (entitlement) ተሞልተው ሌሎች ሰዎች እንዲታዘዟቸው/ የፈለጉትን እንዲያደርጉላቸው/ እንዲያግዟቸው የሚጠብቁ እንዲሆኑ ያደርጋል። የሕይወትን ውጣውረዶች ተጋፍጠው ለመወጣት ዝግጁ ስለማይሆኑ በትምህርትና በሥራ ዓለም ውስጥ ከእኩዮቻቸው ወደኋላ ቀረት የማለት ዕድል ይገጥማቸዋል። በቶሎ ተስፋ የመቁረጥ ባህርይ ኖሯቸው የመንፈስ ጭንቀትና ድብርት ያጠቃቸዋል። ተያይዞም ከሰዎች ጋር ተግባብተውና ተቻችለው ለመኖር ያዳግታቸዋል።

ጥብቅ ወይም ገዳቢ አስተዳደግ

(Strict parenting)

  • የከረረ ደንብና ስነ-ሥራዓትን የሚያስጠብቅ
  • መነጋገርና መግባባትን ያላካተተና ታዛዥነት ላይ ብቻ ያተኮረ
  • ልጆች ከተሳሳቱ/ካጠፉ በማስረዳትና በማስተማር ከመግራት ይልቅ በከባዱ መቅጣትን (ለምሳሌ መግረፍ) የሚያስቀድም

ይህ አስተዳደግ በልጆች ላይ ፍርኀትና ጭንቀትን በማሳደር እንዲዋሹና ሁኔታዎችን ከአሳዳጊዎቻቸው እንዲደብቁ ይገፋፋቸዋል። በእራሳቸው መተማመን እንዳይኖራቸው ከማድረጉም በላይ በባህርያቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ያስከትላል። የንዴትና የተጻራሪነት አለዚያም የዝምተኛነትና የዓይን-አፋርነት ጸባይ ወይም ባህርይ እንዲኖራቸው ያደርጋል። አጠቃላይ ዕድገታቸውን በመግታት የፈጠራ ችሎታቸውንና ማንነታችውን በነጻነት የመግለጽ ብቃታቸውን (creativity and self-expression) አፍኖ ያስቀራል። ከባድ ሁኔታዎችን የመቋቋም እንዲሁም የኑሮ ፈተናዎችን ታግሎ የመወጣት ብቃትና ችሎታቸው መንምነው እንዲቀሩ ምክንያት ይሆናል።

የማያስተማምን አስተዳደግ

(Unreliable parenting)

  • አሳዳጊዎች ቃላቸውን አይጠብቁም
  • እራሳቸውን የመግዛት ችሎታ ተስኗቸው አዘውትረው ያመነታሉ
  • በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ወጣ-ገባ ማለት ያበዛሉ

ይህ አስተዳደግ ልጆች እምነት እንዲያጡ/ተጥራጣሪዎች ሆነው እንዲያድጉ ያደርጋል (አሳዳጊዎቻቸውን በተመለከተ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ሰዎች ጭምር)። በእራስ መተማመናቸው ያልዳበረ ስለሚሆን ከሰዎች ጋር መግባባትና መቻቻል ያዳግታቸዋል። ስለዚህም በትምህርትና በሥራ ዓለም እንዲሁም በግልና በማሕበራዊ ኑሮ ግንኙነቶቻቸው ውስጥ ለግጭቶች የተጋለጡ ይሆናሉ ። ጭንቀትና ድብርትን የመሳሰሉ የስነ-ልቦና ጤና መዛባት ምልክቶችን ያሳያሉ።

እስካሁን እንደተመለከትነው አሳዳጊቺዎች በልጆች ላይ ጉዳት የሚያደርሱት በጎጂ ተግባራቸው - ለምሳሌ መግረፍ (physical abuse) እና በጎጂ አነጋገራቸው - ለምሳሌ ማንቋሸሽ (verbal abuse) ብቻ ሳይሆን ልጆቻቸው ሲፈልጓቸው ባለመገኘታቸውና የሚያስፈልጓቸውን ሁኔታዎች ባለሟሟላታቸውም (neglect) ጭምር ነው። ለምሳሌ፦

    • የልጆች መሠረታዊ ፍላጎቶች እንደ ምግብ፣ ንጹሕ ውኃ፣ መጠለያ፣ ንጽሕና፣ በቂ ልብስና ሰላማዊ የመኖሪያ ቤትና አካባቢ ሳይሟሉ ሲቀሩ (physical neglect)
    • ልጆችን ፍቅርና እንክብካቤ መንፈግ፣ ሰላምና ደህንነት እንዲሰማቸው ሁኔታዎችን አለማመቻቸት፣ ለምናባቸው ዕድገትና ለአእምሯቸው ብስለት የሚያስፈልጓቸውን ሁኔታዎች አለሟሟላት (emotional & psychological neglect)
    • የልጆችን የትምህርት ስኬታማነት አለማመቻቸት፣ ለእውቀታቸው መዳበር ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ አለመሞከር/አለመጣር (educational neglect)
    • የአካል፣ የጥርስ እና የአዕምሮ ጤናቸውን አስመልክቶ እንክብካቤና ሕክምና መንፈግ (medical neglect)

ልጆችን ለመግራት ትክክለኛ መንገዶች ናቸው በማለት የበላይነትን ማሳየት፣ ከመጠን በላይ መቆጣጠር፣ በልጆች ላይ ጭነትን ማሳደር ወይም ፍቅርንና እንክብካቤን መንፈግ የልጆችን ዕድገት የሚገታና ስብዕናቸውን የሚጋፋ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል። አድገውም የእራሳቸውን ሕይወት በሚመሩበት ጊዜ የዝቅተኝነትና ሌሎችን የመጠራጠር ጸባይ፣ በእራሳቸውና በሌሎች ላይ አላስፈላጊ ግፊትን የማሳደርንና የመሳሰሉትን ባህርያት በማሳየት ከሰዎች ጋር መግባባት ሊያዳግታቸው እንደሚችልም ተገንዝበናል። ተያይዞም በሕይወታቸው ደስተኛ መሆን ተስኗቸው ለድብርትና ለሌሎች የስነ-ልቦና ጤና መዛባት ሁኔታዎች ሊያጋልጣቸው እንደሚችልም ተብራርቶልናል።

አብዛኛዎቻችን አሳዳጊዎቻችን አቅማቸውና ችሎታቸው በፈቀደው መሠረት የተቻላቸውን አድርገው አሳድገውናል ብለን ስለምናምን፣ አለዚያም መቅጣታቸው አለአግባብ የነበረ ቢሆንም አልጎዳንም ብለን እራሳችንን ስላሳመንን ለባህርያችንም ይሁን ለስነ-ልቦና ጤናችንና ለግንኙነቶቻችን መዛባት ምክንያት ናቸው ብለን ልንወነጅላቸው አንፈልግም ይሆናል። ይሁን እንጂ ከአስተዳደጋችን የወረስናቸውን ልምዶች እንደገና በልጆቻችን አስተዳደግ ሂደት ውስጥ መተግበራችን ለሚያስከትሏቸው አሉታዊ ተጽዕኖዎች ተጠያቂዎች ነንና የሚከተሉትንና የመሳሰሉትን ሁኔታዎች ልንመረምር ይገባል።

    • ለቁጣ ችኩል በመሆንና ድምፅን ከፍ በማድረግ መፈራትንና መከበርን መፈለግ
    • በፍርሃትና በንዴት በመገፋፋት ልጆችን መኮነን፣ መገሰጽ፣ መውቀስ፣ መቅጣት
    • እኛ ያልነው ብቻ ነው ትክክል በሚል አመለካከት ልጆችን መቅጣትና በፍርኀት እንዲሸማቀቁ/ እንዲሳቀቁ ማድረግ
    • "ጨዋ ልጅ እንዲህ አያደርግም" በማለት ወይም ልጅን "ባለጌ" ብሎ በመስደብ ማሳፈርና ማዋረድ
    • ልጆችን ያበረታታን መስሎን ከሌሎች ልጆች ጋር ማወዳደር
    • ወዘተ

ተከታዩ ትውልድ የተሻለ አስተዳደግ እንዲኖረው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ ስነ-ልቦናዊ ውጥረቶችን (inter-generational stressors) ማገድና ማስወገድ የእያንዳንዳችን ኀላፊነት ነው። ስለዚህም ባህርዮቻችንና ተግባሮቻችን በልጆች ዕድገት ላይ ምንን ሊያስከትሉ ይችላሉ ብለን እራሳችንን እንድንጠይቅ ያስፈልጋል፡፡

አመጣጣችንና አስተዳደጋችን እንዲሁም የሕይወት ተሞክሮዎቻችን በማነታችንና በባህርያችን ላይ ያስከተሏቸው አሉታዊ ሁኔታዎች ይኖራሉ ብለን ካሰብን ወይም ከጠረጠርን ምንጫቸውን መርምረን ለመረዳት መጣራችንና መፍትሔ መፈለጋችን እጅጉን ሊበረታታ የሚገባ ነው።


Read more

የኮንሸስ ፓረንቲንግ  ፍልስፍና                                              - አስተዳደግ ክፍል ፫

የኮንሸስ ፓረንቲንግ ፍልስፍና - አስተዳደግ ክፍል ፫

ኮንሸስ ፓረንቲንግ (conscious parenting = የንቁ-ሕሊና የአስተዳደግ ዘዴ) በአስተውሎት ወይም በmindfulness ላይ የተመሠረተ የልጆች አስተዳደግ ፍልስፍና ሲሆን የሚከተሉትን ዋና-ዋና ባህርያት ያካትታል። * ወላጆች ስለእራሳቸው የተሻለ ግንዛቤ (self-awareness) እንዲኖራቸው እንዲሁም 'እውነተኛ ማንነታቸውን' (authentic self) በበለጠ ለመረዳት ሲሉ ለስሜቶቻቸው ትኩረት እየሰጡ እራሳቸውን ይመረምራሉ (self-reflection) * የልጆችን አስግተዳደግ አስመልክቶ ያሏቸውን ቅድመ-ግንዛቤዎች በመመርመር አመለካከቶቻቸውንና ተግባሮቻቸውን

By TW
የአንጀት ደህንነት-ለጠቅላላ ጤንነት

የአንጀት ደህንነት-ለጠቅላላ ጤንነት

በአዕላፋት የሚቆጠሩ የተፈላጊ ረቂቃን ነፍሳት ሕብረተሰብ ወይም ማይክሮባዮም (microbiome) በቆዳችን ላይና በሰውነታችን ውስጥ ይገኛል። ከሌሎቹ የሰውነታችን ክፍሎች ጋር ሲነጻጸር በአንጀታችን ውስጥ የሚገኘው የማይክሮባዮም መጠን ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። የአንጀት ውስጥ ማይክሮባዮም ማይክሮባዮም እንደ ባክቴሪያ (የbacteria ነጠላ ስም ባክቴሪየም- bacterium ነው)፣ ቫይረሶች (virus/ viruses)፣ ፈንገሶችና (fungus/fungi) ጥገኛ ነፍሳት (parasites) ያሉ ተህዋሳትን

By TW
"ሆዴ ነግሮኝ ነበረ!"

"ሆዴ ነግሮኝ ነበረ!"

"እኔኮ ታውቆኝ ነበረ፣ ሆዴ ነግሮኝ ነበረ፤ ..." ስንል ምን ማለታችን ነው? * ለመረዳትና ለማብራራት በሚያዳግት ሁኔታ አንዳንድ አጋጣሚዎች ወይም ቦታዎች በውስጣችን ያለመመቸት ስሜት የሚቀሰቅሱብን ለምን ይሆን? * ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅነውን ሰው፣ ስለማንነቱ ብዙም ሳንውቅ ሆዳችን እንድንርቀው የሚገፋፋንስ ለምንድን ነው? * ደግሞስ ሆዳችን ነግሮን በእርግጠኝነትና በፍጥነት ትክክለኛ ውሳኔ የምንወስነው እንዴት ሆኖ ነው? የሆድ

By TW
የአስተዳደግ ዓይነቶች - አስተዳደግ  ክፍል ፩

የአስተዳደግ ዓይነቶች - አስተዳደግ ክፍል ፩

የወላጆችና የአሳዳጊዎች ኀላፊነት ልጆች አድገው እራሳቸውን እንዲችሉ እንዲሁም የኑሮ ውጣውረዶችን ለመቋቋም ብቃት እንዲኖራቸው ኮትኩቶ ማሳደግ ነው። ከስህተታቸው ትምህርት እንዲያገኙ ድጋፍ በመሆን ዕድሜያቸው በሚፈቅደው መጠን ለልጆች ኀላፊነትን መስጠትና ለሚገጥሟቸው ችግሮች መፍትሔዎችን ፈልገው እንዲያገኙ ዕድል መክፈት ከመልካም አሳዳጊዎች የሚጠበቁ ዋና ተግባሮች ናቸው። ይሁንና የወላጆችና የአሳዳጊዎች ብቃት፣ በወቅቱ የሚገኙበት ሁኔታ፣ እንዲሁም እራሳቸው በዕድገታቸው

By TW