አዎን! ወንዶችም ያርጣሉ!
የሴቶች እርጣት (menopause - ሜኖፖዝ) በእያንዳንዷ ሴት የሕይወት ሂደት ውስጥ በድንገት የሚከሰት ከኤስትሮጀንና ፕሮጀስትሮን የሴቶች ሆርሞኖች መጠን ማሽቆልቆል ሲሆን ከወር-አበባ ማብቃትና የሴቶች የመውለድ ችሎታ ፍጻሜ ጋር የተቆራኘ ሁኔታ ነው።
በአንጻሩ ግን የወንዶች እርጣት (andropause - አንድሮፖዝ) በአንዳንድ ወንዶች ዘንድ ብቻ የሚከሰትና ከቴስቶስትሮን የወንዶች ሆርሞን መጠን መቀነስ ጋር የተጣመረ፣ አመጣጡ ደግሞ ቀስ-በቀስ ሆኖ የወንዶችን የመውለድ ችሎታ ፈጽሞ የማያውክ ሁኔታ ነው።
የሴቶች እርጣት (ሜኖፖዝ - menopause)
የአንዲት ሴት የወር-አበባ መምጣቱን ካቆመ በተከታታይ 12 ወራት ሲያልፉ አረጠች ይባላል።
የሴቶች እርጣት ከ45 እስከ 55 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ዘንድ የሚከሰት የተፈጥሮ የሽግግር ለውጥ ነው። ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች አንዳንድ ሴቶች 40 ዓመት ሳይሞላቸው ሊያርጡ ይችላሉ።
ለዚህ ዓይነቱ ያለጊዜው ፈጥኖ የሚከሰት እርጣት (premature menopause - ፕሪማቹር ሜኖፖዝ) ምክንያቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
- በሕክምና ሳብያ
- በቀዶ ጥገና የሴቶች ዕንቁልጢዎችና ማሕፀን ሲወገዱ
- በኪሞቴራፒ ሕክምና ሳብያ ዕንቁልጢዎች ላይ ጉዳት ሲያደርስ
- ከዘር በተወረሰ የተቃወሰ የተፈጥሮ ሁኔታ ሲኖር
- ባልታወቁ ምክንያቶች ዕንቁልጢዎች ዕንቁላሎችን መልቀቅ ሲሳናቸው
- በአንዳንድ የሰውነት መከለከያ ሕዋሳት ውዥንብር ሳብያ ዕንቁልጢዎች ጉዳት ሲደርስባቸው
እርጣት ሦስት ደረጃዎችን ያካትታል
ቅድመ-እርጣት (ፔሪሜኖፖዝ - perimenopause) ወደ እርጣት የመሸጋገሪያ ወቅት ሲሆን ከእርጣት በፊት ባሉት ከ2-10 ዓመታት የሚከተሉት ምልክቶች ይታያሉ፦
- የወር-አበባ አመጣጡ ይዛባል (አዘውትሮ ወይም ወራትን እየዘለለ ይመጣል)
- የወር-አበባ መጠኑ ይጨምራል ወይም ይቀንሳል
- በርካታ ሴቶች የእርጣት ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራሉ (ምልክቶቹን ዝቅ ብለው ይመልከቱ)
እርጣት (ሜኖፖዝ menopause) የመጨረሻው የወር-አበባ ከታየ በተከታታይ 12 ወራት ካለፉ በኋላ ጀምሮ ያሉትን ዓመታት ይካትታል።
- ዕንቁልጢዎች ዕንቁላል መልቀቃቸውን ሙሉ በሙሉ ያቆማሉ (የበለጠ ለመረዳት ዝቅ ብለው ይመልከቱ)
- ዕንቁልጢዎች የሚያመነጯቸው የሆርሞኖች መጠን እጅጉን አነስተኛ ይሆናል
ድኅረ-እርጣት (ፖስት ሜኖፖዝ - post menopause)
- የእርጣት ምልክቶች እጅጉን እየቀነሱ በመጨረሻ ፈጽመው ይወገዳሉ
- በኤስትሮጀን እጥረት ሳቢያ የሚከሰቱ የአጠቃላይ ጤና ዕክሎች ይበረክታሉ
ዕንቁልጢዎችና ተግባሮቻቸው
ዕንቁልጢዎች (ovaries) በማሕጸን ግራና ቀኝ እንደ ቀንዶች ባሉ ቱቦዎች ጫፍ ላይ የሚገኙ የዘር ፍሬዎችን ወይም ዕንቁላሎችን ማቀፊያ ዕጢዎች ናቸው። ለወር-አበባና ለእርግዝና የሚያስፈልጉ ዕድገንጥሮችንም (hormones - ሆርሞውንስ) ያመነጫሉ።
የዘር ፍርሬዎችን መሸከም - ሴቶች ከ1 እስከ 2 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዕንቁላሎችን ወይም የዘር ፍሬዎችን ያዘሉ እንቁልጢዎች ኖሯቸው ይወለዳሉ። 25 ዓመት ሲሞላቸው ይህ ቁጥር ቀንሶ ወደ 300 ሺህ ይወርዳል። ዕድሜያቸው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ደግሞ የዕንቁላሎቹ ቁጥር እንደዚሁ የበለጠ እየቀነሰ መጥቶ ከ35 ዓመት ዕድሜ በኋላ ግን የሚያሽቆለቁልበት ፍጥነት እጅጉን እየጨመረ ይሄዳል።
ሆርሞኖችን ማመንጨት - ኤስትሮጀንና (estrogen) ፕሮጀስትሮን (progesterone) የሴት ሆርሞኖች (ዕድገንጥሮች) ናቸው። ከእርጣት በፊት ባሉት ጥቂት ዓመታት (ወይም የእርጣት መግቢያ - perimenopause) የኤስትሮጀን እና የፕሮጀስትሮን መጠን እየቀነሰ ይመጣል። ስለሆነም የእርጣት ምልክቶች (ዝቅ ብለው ይመልከቱ) መታየት ይጀምራሉ።
የኤስትሮጀን ተግባር
- ፆታዊ ዕድገቶችን ማሳካት (sex characteristics development) እንዲሁም የዘር ማፍሪያ አካል ክፍሎችን ተግባራት መቆጣጠር (reproductive system regulation and maintenance)
- የማሕጸንን ውስጣዊ ሽፋን በማደልበት ለእርግዝና ማመቻቸት
- ጡቶች ወተት እንዲያመርቱ ማድረግ
- ለአጥንቶች ጥንካሬ ድጋፍ መስጠት
- ወደ ማሕፀን የሚያስገባውን ቱቦ (ቨጃይና - vagina ወይም በርዝ ከናል -birth canal) እርጥበት እንዲኖረው ማድረግ
- በሴሮቶኒን (serotonin) ምርት ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ሀድራን (mood) መቆጣጠር
የፕሮጀስትሮን ተግባር
- የማሕጸንን ውስጣዊ ሽፋን በማጠናከር እንዲሁም የማሕፀንን መኮማተር በማገድ እርግዝና እንዳይጨናገፍ መከላከል
- የወር-አበባን ወርሃዊ ዑደት መቆጣጠር
- ጡቶች ወተት እንዲያመነጩ መደገፍ
- የመንፈስ ሰላምንና የተረጋጋ እንቅልፍን ማገዝ
የወር አበባ
በየ 24 እስከ 38 ቀናት በየተራ ከግራ ወይም ከቀኝ ዕንቁልጢ አንድ የበሰለ የዘር ፍሬ/ዕንቁላል ይለቀቃል። ነፃ የተለቀቀው ሴት የዘር ፍሬ ከወንድ የዘር ፍሬ ጋር በሚገናኝበት ጊዜ ለእርግዝና በተደላደለው ውስጣዊ የማኅፀን ሽፋን ውስጥ ልጅ ይጸነሳል። ልጅ ካልተጸነሰ ደግሞ ይህ የማሕጸን ሽፋን እየተገፈፈ በወር-አበባ መልክ ከደም ጋር ተቀላቅሎ ከሰውነት ይወገዳል።
የእርጣት ምልክቶች
በቅድሚያ የሚታዩ ምልክቶች፦
- መለስተኛ ወይም የተጋነኑና በድንገት የሚከሰቱ ከደረት በላይ የግለት/ የወበቅ እንዲሁም የማላብ ስሜቶች
- በሌሊት ዕንቅልፍ ጊዜ በላብ መጥለቅለቅ (night sweats - ናይት ስዌትስ)
- ቀናቱን ያተስተጓጎለ የወር አበባ አመጣጥ (irregular menstruation - ኢሬጉለር ሜንስትሩዌሽን)
- በሴት ብልትና የመውለጃ ቧንቧ ድርቀት (vaginal dryness - ቫጂናል ድራይነስ) ምክንያት የሚከሰቱ የማሳከክ፣ የመለብለብና የሕመም ስሜቶች
- የሽንት ፊኛ መታወክ ምልክቶች (bladder symptoms - ብላደር ሲምፕተምስ) - አዘውትሮ መሽናት እንዲሁም ሌሊት ለሽንት ደጋግሞ መነሳት፣ ሽንትን መቋጠር ማዳገት፣ ሲሸኑ የማስማጥ እና የመለብለብ ስሜቶች
- የዕንቅልፍ መዛባት
- የሀድራ መለዋወጥ (mood changes - ሙድ ቼንጅስ) - ድባቴና ንጭንጭ ወዘተ.
- የአፍ፣ የዓይኖችና የቆዳ ድርቀት
ዘግየት ብለው የሚከሰቱ ምልክቶች፦
- የድካም ስሜት
- የማስተዋልና የማስታወስ ችሎታዎች መቀነስ
- የልብ ምት መጨመር
- የራስ ምታት
- የመገጣጠሚያዎችና የጡንቻዎች ሕመም
- የክብደት መጨመር - በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል እስከ 4.5 ፓውንድ፣ በ50ና 60ዎቹ የዕድሜ ክልል ደግሞ 1.5 ፓውንድ ያህል ክብደት ይጨመራል
- የጡንቻዎች መቀነስ - ከ30 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ በየዓመቱ በግማሽ ፓውንድ ያህል የጡንቻዎች መጠን ይቀንሳል፤ ከ50 ዓመት ዕድሜ በኋላ ደግሞ አንድ ፓውንድ ያህል የጡንቻዎች ይዘት በየዓመቱ ይቀንሳል
- የጸጉር መሳሳት እንዲሁም ፊት ላይ ጸጉር ማብቀል
- የወሲብ ፍላጎት ለውጥ (መጨመር ወይም መቀነስ)
እርጣትን አስከትለው የሚመጡ የጤና ዕክሎች
- የአጥንቶች መዘርዘርና መሳሳት
- የልብ በሽታ
- ከየሽንት ፊኛና ከአንጀት ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች
- የሀድራ መለዋወጥ
- የቆዳ መሸብሸብ የበለጠ መጨመር
- የጡንቻዎች ጥንካሬ መዳከም
- የዓይኖች መዳከም
- የአልዝሃይመርስ የአዕምሮ መዳከም የመከሰት ዕድሉ ከፍ ይላል
ድንገተኛ የሙቀትና የማላብ ስሜት
"በድንገት እሳቱን ይለቅብኝና ላብ ያጥለቀልቀኛል። ወድያውኑ በረዶውን ያፈስብኝና ብርድ ብርድ ሲለኝ እንደገና ቆየት በሎ ደግም መልሶ እሳቱን ይለኩስብኛል..." (አንዲት በማረጥ ላይ ያሉ ሴት የታመሙ መስሏቸው ሐኪም ዘንድ ሄደው የሚሰማቸውን በማስረዳት ከተናገሩት የተቀነጨበ)
መንስኤው ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም በእርጣት ጊዜ ከደረት አንስቶ አንገትንና ፊትን የሚያጠቃልል ድንገተኛ የግለትና የማላብ ስሜት (ሆት ፍላሽስ - hot flashes) በኤስትሮጀን እጥረት ምክንያት እንደሚከሰት ይታወቃል።
እርጣትን አስታኮ የሚሰማ የግለትና የማላብ ስሜት አብዛኛውን ጊዜ እስከ 5 ደቂቃዎች ቆይታ ሲኖረው በአማካዩ በቀን 4-5 ጊዜ በተደጋጋሚ ሊከሰት ይችላል። አንዳንድ ሴቶች በቀን እስከ 20ና 30 ጊዜ ሲያጋጥማቸው ሌሎች ደግም በሳምንት አንዴና ሁለቴ ብቻ ሊሰማቸው ይችላል። ሰዓት ሳይለይ በማንኛውም ጊዜ የሚሰማ ስሜት ሲሆን ሌሊት በእንቅልፍ ጊዜ ሊበረታ ይችላል።
የእነዚህ ምልክቶች መታየት እንዲሁም ቆይታቸው ከሴት ሴት ይለያያል። ይሁን እንጂ እርጣት የተፈጥሮ ለውጥና የሽግግር ክስተት እንደመሆኑ መጠን ምልክቶቹም ከጊዜ ጋር እየከሰሙ በ7 እስከ 10 ዓመታት ውስጥ ፈጽመው ይጠፋሉ፡፡
(ማስታወሻ፦ hot flashes - ሆት ፋላሽስ ውስጣዊ የግለት ስሜትን መግለጫ ሲሆን flushing ፍለሺንግ ደግሞ ውጫዊ የደረትና የፊት ቆዳ ደም መምሰልን የሚያመለክት ነው። ይሁንና hot flashes ይበልጡን በሰሜን አሜሪካ የሚዘወተር አባባል ሲሆን hot flushes ደግሞ እንግሊዞች የሚገሉበት አጠራር ነው። ስለሆነም ሁለቱን በተለዋዋጭነት መጠቀም ስህተት አይሆንም።)
ከእርጣት ጋር የሚከስቱ የሀድራ (mood) ለውጦች
- የኀዘንና የጭንቀት እንዲሁም የድባቴ ስሜቶች
- ተስፋ መቁረጥና ስለእራስ እንዲሁም ስለወደፊቱ ሕይወት አሉታዊ አመለካከቶችን ማብዛት/ማጉላት
- መነጫነጭ፣ መቆጣት፣ እንባ-እንባ የማለት ስሜት
- የሰውነት ድካም ስሜት
- የእንቅልፍ መዛባት - እንቅልፍ ማጣት ወይም እንቅልፍ ማብዛት
- የምግብ ፍላጎት እንዲሁም የሰውነት ክብደት ለውጥ
- የማስተዋል፣ የምስታወስ፣ እንዲሁም ውሳኔዎችን የመወሰን ችሎታ መቀነስ
- ለእራስ ጥንቃቄ ማድረግ መቀነስና እራስን ከሰዎች ማግለል
- አልፎ አልፎ የሚከሰት - ስለሞትና እራስን ስለማጥፋት ማሰብና ማብሰልሰል
የሽንት ፊኛና የሴት ጾታዊ የአካል ክፍሎች መታወክ
- በማረጥ ላይ ያሉ ከ27 እስከ 84 በመቶ የሚሆኑትን ሴቶች ያጋጥማል
- ከመጨረሻው የወር አበባ በኋላ በሚከተሉት ጥቂት ወራትና ዓመታት ይከሰታል
- የሴት ብልት ድርቀት፣ ማሳከክና የፈሳሽ ለውጥ እንዲሁም በሚሸኑበት ጊዜ የመለብለብ ስሜቶችን ያስከትላል
- ይህ የጤና ቀውስ የጾታ ግንኙነት ፍላጎትንና እርስ-በርስ መግባባትን ያውካል
- በእራስ ማንነትና በጾታዊ ግንኙነት ደስተኝነት እንዲቀንስ ያደርጋል
የሕክምና መፍትሔዎች
የትኛውንም ዓይነት መድሐኒት ከመጠቀምዎ በፊት ሐኪምዎን ያማክሩ
- ኤስትሮጀንና ፕሮገስቶጀን ሆርሞኖችን በመድሐኒት መልክ በመውሰድ - በኪኒን፣ ቆዳ ላይ በሚለጠፍ፣ በቅባት መልክ (hormone replacement therapy - ሆርሞን ሪፕሌይስመንት ቴራፒ) የግለትና የማላብ ስሜቶችን መቆጣጠር
- ሆርሞኖችን ያዘለ የወሊድ መከላከያን መጠቀም
- የድባቴ መድሐኒቶችን በዝቅተኛ መጠን መውሰድ
- ሆርሞን-አልባ መድሐኒቶችን በመጠቀም የሰውነት ግለትን መቆጣጠርና እንቅልፍን ማስተካከል
- የመውለጃ ቱቦ ውስጥ የሚከተት/ የሚቀባ መድሐኒት - ድርቀትን፣ የሽንት ማቃጠልንና በግንኙነት ጊዜ የሚሰማ ሕመምን ለማስታገስ
የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች
አመጋገብንና ተጨማሪ በአፍ የሚወሰዱ ንጥረ-ነገሮችን በተመለከተ፦
- የተመጣጠነና ጤናማ አመጋገብ - ክብደትን፣ የሰውነት ግለትንና የአጥንቶችን መሳሳት ለመቆጣጠር (ቅባት-አልባ ዕርጎና ወተት፣ ቺዝ፣ ብሮክሊ፣ ሶያ፣ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች፣ ወዘተ)
- ቡና፣ ሻይ፣ የአልኮሆል መጠጥችንና ማጤስን መቀነስ/ማስወገድ
- የአጥንቶችን ጤና ለመንከባከብ ካልሲየምና ቫይታሚን ዲ ማከል
የሰውነት እንቅስቃሴ፦
- የተሻለ እንቅልፍ ለመተኛት
- የልብና የስኳር በሽታዎችን ለማገድ
- አጥንቶችን ለማጠንከር - ለምሳሌ፦ የክብደት ማንሳት ልምድ
- የኪገል ልምምዶች (Kegel exercises) - የሽንት ፊኛን፣ ማህጸንንና አንጀቶችን በማቀፍ የሚደግፉ የዳሌ ወለል ጡንቻዎችን (pelvic floor muscles - ፔልቪክ ፍሎር ማስልስ) እና ሽንትን ለመቋጠር የሚያስችሉ ጡንቻዎችን ለማጠንከር
ተጨማሪ ጠቃሚ ተግባራት፦
- ታይቺና (tai-chi) ዮጋ
- አክዩፓንክቸር (acupuncture)
- ሳይኮቴራፒ (psychotherapy)
- አስተውሎት (mindfulness) እና ጥልቅ የአተነፋፈስ ዘዴ (deep breathing)
- የሰውነት ማሳዥ
- ከሰዎች ጋርና የሚወዱትን በማድረግ ጊዜ ማሳለፍ
- በጊዜ መተኛትና በቂ እንቅልፍ ለማግኘት መጣር
የሴቶችን እርጣት ምልክቶች ስለ መቋቋም፣ ስለ አመጋገብና የአካል እንቅስቃሴ ለውጦች፣ ስለቤተሰብ አባላት እርዳታ ጥቅም፣ ከማረጥ በኋላ ወይም የድኅረ-እርጣት ሕይወት ምን እንደሚመስልና አብረው ስለሚከሰቱ ሁኔታዎችና መፍትሔዎቻቸው የበለጠ ለመረዳት ከዚህ በታች ያሉትን ሊንኮች ይጫኑ።
የወንዶች እርጣት (አንድሮፖዝ - Andropause)
አንድሮፖዝ በወንዶች የ30ዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል አንስቶ የሚከሰት የለውጥ ሂደት ሲሆን በዓመት ከአንድ እስከ ሦስት በመቶ ያህል የሚሆን የቴስቶስተሮን ሆርሞን መጠን ማሽቆልቆል የሚታይበት ሁኔታ ነው፡፡
ቀስ-በቀስና በስውር ለ15-20 ዓመታት የሚከሰተው የአንድሮፖዝ ለውጥ የወንዶችን ዘር የማፍራት ችሎታ አያውክም፤ ምክንያቱም የቴስቶስተሮን መጠኑ ቢቀንስም የብዙዎችን ፍሬያማነት እንደተጠበቀ የሚያቆይ ያህል በቂ የቴስቶስተሮን መጠን ስለሚተርፍ ነው። ስለሆነም ወንዶች በ60ዎቹና ከዚያም የበለጠ በገፋ ዕድሜያቸው ሴትን ማስረገዝ ይችላሉ።
በአንድሮፖዝ ወቅት ወንዶች እንደሴቶች የሀድራ መለዋወጥ (mood swings - ሙድ ስዊንግዝ) እንዲሁም የድካም ስሜትና የጾታዊ ግንኙነት ፍላጎት መቀነስ ሊሰማቸው ይችላል። የጡንቻዎች ጥንካሬና ብርታት መቀነስ፣ የሆድ ላይ ውፍረት መጨመር፣ ንጭንጭና ድብርት፣ የአጥንቶችና የጸጉር መሳሳት እንዲሁም የእንቅልፍ መዛባት፣ የማስተዋልና የማስታወስ ብቃት መቀነስና የሰውነት ግለት ስሜት አንድሮፖዝን ከሜኖፖዝ ጋር የሚያዛምዱ ምልክቶች ናቸው። ከሜኖፖዝ ለየት የሚያደርጓቸው ምልክቶች ደግሞ ስንፈተ-ወሲብ (erectile dysfunction - ኢሬክታይል ዲዝፈንክሽን) እና የጡቶቻቸው ማደግ ናቸው።
የአንድሮፖዝን ምልክቶች ለማከም በቅድሚያ ሐኪም ዘንድ በመሄድ በደም ምርመራ የቴስቶስተሮንን መጠን ማስለካት ያስፈልጋል። ቴስቶስተሮን ለመቀነሱ ሌሎች የጤና መታወክ ምክንያቶች መኖር አለመኖራቸውንም ማጣራት ይገባል። ስለዚህ ስለ ወንዶች ጤናና ሆርሞኖቻቸው ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው ስፔሻሊስት ዘንድ ሄዶ መታየት ይመከራል።
ቴስቶስተሮንን የመተካት ሕክምና (testosterone replacement therapy - ቴስቶስትሮን ሪፕሌይስመንት ቴራፒ) የተለያዩ በኪኒን፣ በቅባትና ቆዳ ላይ በሚለጠፍ መልክ የሚሰጡ መድሐኒቶችን ያካትታል። የጡትና የፕሮስቴት ካንሰር ተገኝቶባቸው የሚያውቁና የልብ በሽታ የሚያሰጋቸው ወንዶች እነዚህን መድሐኒቶች ከመውሰዳቸው በፊት ሐኪማቸውን ማማከር ይገባቸዋል።
መድሐኒቶችን ከመጠቀም በፊት በሜኖፖዝ ወቅት እንደሚመከረው በአመጋገብ ለውጥና በሰውነት እንቅስቃሴ የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር ያስፈልጋል። የክብደት ማንሳት ስፖርትን በማዘውተር ጡንቻዎችንና አጥንቶችን ማዳበር ይጠቅማል። በተጨማሪም ለአዕምሮ ጤንነት ትኩረትና ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል።