ሐዘን ሲተነተን

ሐዘን ሲተነተን
Photo by Thomas Bormans / Unsplash

ሐዘን (grief) የምናውቀው፣ የምንቀርበው ወይም የምንወደው ሰው በሞት ሲለየን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ከሕይወት ጋር የተገናኙ ከባድ የማጣት ጉዳቶችን (loss) አስከትሎ የሚከሰት ስሜት ነው።

ለምሳሌ፦

  • ጤናችን ሲታወክና መፍትሔ የማይገኝለት ሁኔታ ሆኖ የአካላችን ክፍል ወይም አዕምሯችን ሙሉ በሙሉ መዳን ሲሳነው
  • የትዳር ወይም የፍቅር ወዳጅነት መፍረስ፣
  • ከሰዎች ጋር የነበረን ቅርበት በተለያየ ምክንያት ሲታወክና መራራቅ/መለያየት ሲፈጠር፣
  • ጽንስ ሲጨናገፍ ወይም ዕርግዝና ሲቋረጥ፣
  • በድንገት ከሥራ መባረር፣ በጡረታ መገለል፣
  • ንብረትን ወይም ሀብትን ማጣት/መነጠቅ ፣
  • ከኖሩበት አካባቢ መፈናቀል ወዘተ

ማጣት በሦስት ፈርጆች ይከፈላል፦

  • ንብረትና ሀብትን ማጣት፤ ሥራን ማጣት/ከሥራ መባረር፣ ወዘተ (External loss)
  • በራሳችን/ በግላችን/ በውስጣችን ማጣት ሲደርስብን/ ሲያጋጥመን (የአካል/የአዕምሮ ጤና ማጣት፣ ያለምነውን ወይም ተስፋ ያደረግነውን ማጣት ፣ ወዘተ (Intra-psychic loss)
  • ከሌላ ሰው ጋር ያለንን ግንኙነት አስታኮ የሚከሰት ማጣት፦ ከሰው ጋር ያለን ግንኙነት በሞት ወይም በሌላ ምክንያት ሲስተጓጎል/ ሲሰናከል/ ሲቋረጥ፣ ወዘተ (Inter-psychic loss)

ሰውን በሞት ማጣትን አስከትሎ የሚከሰት ሐዘን ከሁሉ በላይ የከበደና ቅስምን የሚሰብር ነው። የቅርባችን የሆነ ሰው በሞት ሲለየን የሚሰማን ሐዘን ያ ሰው ስለተለየን ብቻ ሳይሆን ከሟች ጋር የተያያዙ ትውስታዎችን ስለምናጣ፣ ሟች በሕይወት ሳለ/ሳለች/ሳሉ እና አብረን በኖርንባቸው ጊዜያት ለቅርበታችን ሰጥተነው የነበረው ልዩ ቦታ ባዶውን ቀርቶ በቀን ተቀን ሕይወታችን ውስጥ ክፍተት ስለሚፈጠር፣ ከዚያም አልፎ ስለወደፊቱ አብረን አልመነው እና ተስፋ አድርገነው የነበረውን ሁሉ ስለምናጣም ጭምር ነው።

በሞትም ይሁን ከፍ ብልው በተዘረዘሩት የማጣት ሁኔታዎች ምክንያት የሚደርስብን ሐዘን በሰውነታችንና በአዕምሯችን ውስጥ ከዚህ በታች የተጠቀሱትንና ሌሎች ለውጦችን ያስከትላል

አካላዊ ለውጦች ፦

  • የድካም ስሜት
  • የዕንቅልፍ መዛባት እንዲሁም የቅዠት ዕንቅልፍ
  • የምግብ ፍላቶት መለወጥ፣ የማቅለሽልሽ ወይም የጨጓራ መቆጣት ስሜት፣ ተቅማጥ ወይም የሆድ ድርቀት
  • የራስ ምታት፣ የጡንቻዎች ህመም፣ የደረት ውጥረት ወይም የጉሮሮ ጥበት ስሜት
  • ሰውነታችን በሽታዎችን የመከላከል ኅይሉን በማጣቱ ምክንያት ለበሽታዎች መጋለጥ
  • የልብ ምትና የደም ግፊት ከፍ ማለት፣ "የልብ መሰበር" ወይም የባዶነት ስሜት
  • የማጥወልወል ስሜት፣ የአፍ መድረቅ፣ ወዘተ

ስሜታዊ ለውጦች፦

  • የስሜት መደንዘዝ (shock, numbness)፣ ሞትን ወይም ማጣትን አለመቀበል ወይም አለማመን (denial & disbelief)
  • የስሜት መተረማመስ (disorganization)፣ ግራ መጋባት (confusion)፣ ለጥያቄ መልስ ማጣት (searching)፣ መናፈቅ/ መንሰፍሰፍ/ መጓጓት (yearning)
  • መጨነቅና መጠበብ (anxiety)፣ መደናገጥ (panic) ፣ መፍራት (fear) ፣ መሸበር (terror)
  • መናደድ፣ መበሳጨት፣ መማረር
  • ራስን ወይም ሌላን መውቀስ/ መኮነን
  • መቅናት፣ መቆጨትና የጥፋተኝነት ስሜት መሰማት
  • ማዘን - መከፋት፣ መደበር፣ የቅስም መሰበር፣ ተስፋ መቁረጥ፣
  • ዕምነትን መፈተን/መጠየቅ/ መጠራጠር
  • ራስን ለመጉዳት ወይም ለማጥፋት የመፈለግ ስሜት
  • የብቸኝነት ስሜት
  • የእፎይታ ስሜት (ሟችን ለረጅም ጊዜ ስናስታምም ቆይተን ስቃያቸውን አስተውለን "አሁንስ ስቃዩ በዛባቸው - በቃ ይበላቸው" ብለን በምንመኝበት ጊዜ የሚሰማን የመቀበልና የመረጋጋት ስሜት)፣ ወዘተ

አንዳንድ ሰዎች ጮክ ብለው በማልቀስ ሐዘናቸውን የሚገልጹ ሲሆን ሌሎች ዝምታና ለብቻቸው የማብሰለሰል ባህርይ ሊያሳዩ ይችላሉ። እንደገና ሌሎች ደግም ስለሟች ትውስታቸውን ማውራትንና በሟች ስም አንዳንድ በጎ ተግባራትን ማድረግ ይመርጡ ይሆናል። ታድያ ይህ ሰዎች በተለያየ መንገድ የሐዘን ስሜታቸውን እንደሚገልጹ/ እንደሚወጡ የሚያሳይ እንጂ የሐዘናቸውን ጥልቀት/ክብደት ወይም መጠኑን የሚያመለክት አይደለም።

ሐዘን የራሱ የሆነ ሂደት ስላለው ማፋጠን ወይም ከላይ የተዘረዘሩት የማጣት ስሜታዊ ለውጦች እንዳይኖሩን ማድረግ አይቻልም። በትዕግስት ስሜቶቻችንን እያዳመጥን ለእራሳችን ጊዜንና እንክብካቤ መስጠታችን እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ሐዘንን ካፈንነው ጤናችንን በማወክ የተለያዩ የአካል ህመሞችና በሽታዎች እንዲሁም እንደ የገነነ ቁጭት/ ራስን መኮነን፣ ድብርት እና ራሳችንን ለማጥፋት የመፈለግ ስሜት ያሉ የሥነ-አዕምሮ ውጥረቶችን ሊያስከትል ይችላል።

ብዙውን ጊዜ ሰዎች በአንድ ዓመት ውስጥ ሊጽናኑና ሐዘናቸው ሊቀልላቸው ይገባል የሚል አመለካከት አለ። ይሁንና ሐዘን እንደ ቋሚው ባህርይና የሕይወት ልምድ፣ ከሟች ጋር እንደነበረን ቅርበት፣ እንደ ሟች ዕድሜና አሟሟት ወዘተ ይለያያል።

አንዳንዶቻችን ዛሬ ሐዘን በርትቶብን ውሎ ነገ ደግሞ ቀለል ሲለን፣ እንደገናም ወሎ አድሮ ሲከብደን፣ ወራት ወይም ዓመታት ተቆጥረው ሐዘኑ እንደገና ሲያገረሽብን ግራ ገብቶን "ምን ሆኛለሁ?" ብለን እራሳችንን እንጠይቅ ይሆናል። ሰው ይታዘበናል ብለንም ስሜታችንን እናፍን ይሆናል። በተለይም በልጅነታችን ወላጃችንን አጥተን ከሆነ በዕድገታችን ጉዞ ውስጥ በሚከሰቱት ለውጦች እና አዳዲስ ምዕራፎች ወላጃችን በሕይወት ኖሮ/ኖራ ይህንን ለማየት በቻለ/በቻለች ነበር ብለን በመቆጨት በየምዕራፉ የሐዘን ስሜቶች እንደገና ጎብኝተውን ይሆናል። እዚህ የተጠቀሱትና እነዚህን የመሳሰሉ ስሜቶች በሐዘን ጉዞ ውስጥ ሊደርሱ እንደሚችሉ አውቀን በተከሰቱ ጊዜ ለእራሳችን ተገቢውን እንክብካቤ እንድንሰጥ ይመከራል።

ስለደረሰብን ሐዘን ጥሩ የማዳመጥ ችሎታ ካለው ሰው ጋር ብናወራና በግልጽ የሐዘን ስሜታችንን ብናካፍል፣ የዕለት ከዕለት ተግባራትን ማከናወን ከተሳነን ደግሞ ከሐዘን አማካሪ (grief counsellor) ዕርዳታ ብንጠይቅ እራሳችንን እየተንከባከብን ሐዘናችንን ጤናማ በሆነ ሁኔታ እንድንወጣ ይረዳናል።

ሰው ሲሞት መሰባሰብና መተጋገዝ እንዲሁም የየማሕበረሰቡን ባህል፣ ደንብና ሥርዓት በተከተለ መንገድ ሐዘነተኛን ማስተዛዘንና ማጽናናት የሚጠበቅ ነገር ነው። ይሁንና ከላይ እንደተገለጸው ሐዘንን የምናስተናግድበትና የምንገልጽበት መንገድ ከሰው ሰው ሊለያይ እንደሚችል ተገንዝበን ሀሳባችንን/ምክራችንን ለሐዘነተኞች ከመለገሳችን በፊት ለማጽናናት ተብሎ በተለምዶ የሚባል አነጋገር በሐዘነተኞች ስሜት ላይ ምን ሊያስከትል ይችላል ብለን እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል ።

ለምሳሌ፦

  • “ላይችል አይሰጥም።”
  • “ሁሉም ለበጎ ነው።”
  • “ገና ወጣት ነሽ፣ ሌላ ልጅ ትወልጃለሽ።”
  • “አይዞህ - ዕድሜህ ለጋ ነው ሌላ ሚስት እንደገና ታገባለህ።”
  • “ተዉ፤ ማልቀስ ከእንግዲህ አያስፈልግም።”
  • "ሟች ረጅም ዕድሜ ኖረዋልና ማዘን አይገባም።" ወዘተ

እንደዚህ ዓይነት አባባሎች ሐዘነተኞችን ከማጽናናት ይልቅ ሐዘናቸው ተገቢ እንዳልሆነ ሆኖ እንዲሰማቸው፣ እራሳቸውን የበለጠ እንዲኮንኑና ሐዘናቸውን እንዲያፍኑ ያደርጋል። ከፍ ተብሎ እንደተገለጸው ሐዘንን ማፈን በጤናችን ላይ በርካታ አሉታዊ ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል።

ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች “እንዲህ አድርጉ” ወይም “እንዲያ አታድርጉ” ብለን ሳንጠየቅ ምክር መካሪዎች ሆነን ከመገኘት ይልቅ በትዕግስት ከልባችን አዳማጮች በመሆን ሐዘነተኞች ስሜታቸውን በፈቃዳቸው እንዲያካፍሉን ዕድል ብንሰጣቸው ይመረጣል። አንዳንዴ በዝምታ ከጎናቸው ብንቀመጥ በቂ ሊሆን እንደሚችል እናስተውል። ምን ብናደርግላቸው ወይም ምን ዓይነት ዕርዳታ ከእኛ እንደሚፈልጉ ብንጠይቃቸው (በባህላችን መግደርደር ያለ ነገር ቢሆንም) ፍላጎታቸውን እንዲገልጹና ለእነርሱ በሚመች መንገድ ድጋፍ እንድንሆናቸው ዕድል ይሰጠናል።

ማጣት፣ ሞትና ሐዘን ማናችንንም የማያበላልጡ በሁላችንም ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ክስተቶች ናቸው። ስለሆነም ስለሕይወት ገጠመኞቻችን/ልምዳችን በነጻነት እንደምንወያየው ሁሉ ስለማጣት፣ ስለሞትና ሐዘንም በግልጽ ማውራትንና በሐዘናችን ጊዜ አስተዛዛኞች በምን መንገድ እንዲደግፉን እንደምንፈልግ ያለይሉኝታ መናገርን እንልመድ።

ሐዘነተኞችን የሐዘን ስሜቶቻቸው ቀለል እንዲሉላቸው ወይም መጽናናታቸው እንዲፋጠን የሚያስችለን ኅይል ወይም ችሎታ ማናችንም እንደሌለን በመገንዘብ በትዕግስት ከሐዘን ጋር አብረን መቆየትን ለእራሳችንም ይሁን ለሌሎች እንፍቅድ። መካሪዎች ከምንሆን ይልቅ ጥሩ አዳማጮች በመሆን ሐዘነተኞች ስሜቶቻቸውን በእራሳቸው መንገድና ጊዜ እንዲያስተናግዱ ተገቢውን ቦታና አክብሮት እንስጣቸው።


Read more

አስተዳደግ - ክፍል ፩

አስተዳደግ - ክፍል ፩

የአስተዳደግ ዓይነቶች የወላጆችና የአሳዳጊዎች ኀላፊነት ልጆች አድገው እራሳቸውን እንዲችሉ እንዲሁም የኑሮ ውጣውረዶችን ለመቋቋም ብቃት እንዲኖራቸው ኮትኩቶ ማሳደግ ነው። ከስህተታቸው ትምህርት እንዲያገኙ ድጋፍ በመሆን ዕድሜያቸው በሚፈቅደው መጠን ለልጆች ኀላፊነትን መስጠትና ለሚገጥሟቸው ችግሮች መፍትሔዎችን ፈልገው እንዲያገኙ ዕድል መክፈት ከመልካም አሳዳጊዎች የሚጠበቁ ዋና ተግባሮች ናቸው። ይሁንና የወላጆችና የአሳዳጊዎች ብቃት፣ በወቅቱ የሚገኙበት ሁኔታ፣ እንዲሁም

By TW
'አስተውሎት'  Mindfulness

'አስተውሎት' Mindfulness

ለአሁኒቷ ሰከንድ (present moment) ሙሉ ትኩረት በመስጠት ሀሳባችንን (thoughts)፣ ስሜታችንን (feelings)፣ እና ሕውስታችንን (sensations) የማስተዋል ተግባር ወይም ልምድ ማይንድፉልነስ (mindfulness) በመባል ይታወቃል። በዚህ ጽሑፍ ላይ 'አስተውሎት' ተብሎ ተተርጉሟል። የኑሮን ውጣ ውረድ ለመወጣት አብዛኛዎቻችን ትኩረታችን በየዕለቱ መደረግ የሚገባውን ማከናወናችንን እንጂ ሁኔታዎች በውስጣችን ስለሚያስከትሉት/ስላስከተሉት የስሜት ለውጥ በአብዛኛው የምናስበው ነገር

By TW
ለሥነ-ልቦናና  ለሥነ-አዕምሮ ጤና  ትርኩረት  እንስጥ

ለሥነ-ልቦናና ለሥነ-አዕምሮ ጤና ትርኩረት እንስጥ

የሥነ-ልቦናና የሥነ-አዕምሮ ጤና አገልግሎት ሰጪዎች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ። ለምሳሌ፦ በግል ተቋማት፣ በሆስፒታሎች፣ በክሊኒኮች፣ በድጋፍ መስጫዎች፣ በማገገሚያ ተቋማት፣ በከፍተኛ ትመህርት ተቋማት እና በሌሎችም ሥፍራዎች አገልግሎት ይሰጣሉ። ሳይኮተራፒ  (psychotherapy) የአስተሳሰብ፣  የባህርይ ፣  የተግባር፣  እንዲሁም  የማሕበራዊ  ኑሮ ግንኙነት  አዎንታዊ  ለውጦችን  ለማስገኘት የሚያገለግል የሥነ-ልቦና ዕርዳታ መስክ ሲሆን በመወያተትና  በመመካከር (talk therapy) ላይ የተመሠረተ የሞያ

By TW
ኮንሴንት ምንድን ነው?

ኮንሴንት ምንድን ነው?

ኮንሴንት = ፈቀደ፣ ተስማማ፣ እሺ አለ - ማለት ነው። (አቢሲኒካ መዝገበ ቃላት) https://dictionary.abyssinica.com/consent ኮንሴንት (Consent) በዓለም-አቀፍ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ደንቦችና ሕግጋት ላይ የተመሠረት ደንብና ልማድ ሲሆን ማንም ሰው አካሉን/ አከላቱን አስመልክቶ በሕይወቱ፣ በጤናው፣ በወሲባዊ ግንኙነቱና ሌሎችም ከአካል ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች ዙሪያ ራሱ በራሱ የመወሰን ሙሉ ነጻነት እንዳለው

By TW