"ሆዴ ነግሮኝ ነበረ!"
"እኔኮ ታውቆኝ ነበረ፣ ሆዴ ነግሮኝ ነበረ፤ ..." ስንል ምን ማለታችን ነው?
- ለመረዳትና ለማብራራት በሚያዳግት ሁኔታ አንዳንድ አጋጣሚዎች ወይም ቦታዎች በውስጣችን ያለመመቸት ስሜት የሚቀሰቅሱብን ለምን ይሆን?
- ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅነውን ሰው፣ ስለማንነቱ ብዙም ሳንውቅ ሆዳችን እንድንርቀው የሚገፋፋንስ ለምንድን ነው?
- ደግሞስ ሆዳችን ነግሮን በእርግጠኝነትና በፍጥነት ትክክለኛ ውሳኔ የምንወስነው እንዴት ሆኖ ነው?
የሆድ ውስጥ የማወቅ ስሜት ወይም gut feeling (ገት ፊሊንግስ = 'የአንጀት ስሜት') በደመነፍስ የማወቅ ችሎታ(instinct) ነው። አስበንና አብላልተን፣ እንዲሁም በምክንያት ወይም በመረጃ ላይ ተመርኩዘን ሳይሆን በአቋራጭ መንገድ በፍጥነት ወስነን እርምጃ ለመውሰድ የሚያበቃን ልዩ ስሜት ነው።
ይህ ቅጽበታዊ 'በሆድ የማወቅ' ችሎታ በአንድ በኩል ለኅልውናችን (safety) የሚያሰጋ ሁኔታ ሲያጋጥመን እራሳችንን ለማዳን/ለመከላከል የሚያስችለን ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አንድን ሁኔታ በፍጥነት ተገንዝበን በሙሉ ልብ ትክክለኛ ውሳኔ ለመወሰን የሚያበቃን የረቀቀ ተፈጥሯዊ ዐቅም/ኃይል ነው።
ሳይንሳዊ መረጃዎች ምን ይላሉ?
"ሆዴ ነገሮኛል" ወይም "እኔኮ ታውቆኛል" ለማለት የሚያበቃን ልዩ ችሎታ የተለያዩ ሥውር አካላዊ ተግባራትን ትብብር ይጠይቃል።
፩ኛ/ የአዕምሯችን በደመነፍስ የማስተዋል ችሎታ
አዕምሯችን ያለማቋረጥ ገጠመኞቻችንን፣ ተሞክሮዎቻችንን፣ ትዝታዎቻችንንና ስሜቶቻችንን ይመዘግባል። መልካምና ጠቃሚ ናቸው እለዚያም አደገኛና ጎጂ ናቸው ብሎ ከፋፍሎ እየመደበ ይጠብቃል። በዕለት-ተዕለት ሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ሁኔታዎች ቀደም ብሎ ሰብስቦ ካከማቻቸው ተሞክሮዎች ጋር በማነጻጸር ስለሁኔታው አስበንና ገምግመን ከመረዳታችን በፊት አዕምሯችን ቅጽበታዊ መልዕክቶችን ወደ አንጀታችንና ጠቅላላ ሰውነታችን ያሰራጫል፡፡ የሚከተሉትንም ምልክቶች ልናስተውል እንችላለን፦
ሀ/ የማይመች ወይም የመጠራጠር ስሜት
- በአንጀታችን/በሆዳችን ውስጥ የባዶነት፣ የመርገብገብ፣ የመንሰፍሰፍ፣ የመፍራት፣ የማቅለሽለሽ፣ ወዘተ ስሜት
- በተጨማሪም የልብ ትርታ መጨመር፣ የእጆቻችን ማላብ፣ የምላስ መድረቅ፣ መጨነቅ፣ ወዘተ
ለ/ ቅጽበታዊና ድንገተኛ የመረጋጋት፣ የማወቅና የእርግጠኝነት ስሜት
- ምን ተፈጠረ ብለን አስበን ለመረዳት ከመሞከራችን በፊት ሁኔታዎች ጥርት ባለ መንገድ ከመቅጽበት ግልጽ ይሆኑልናል።
፪ኛ/ ስውሩ የመገናኛ መስመር
በአዕምሯችንና በአንጀታችን መሀከል ብርቱ የመተሳሰር ግንኙነት አለ። እንደ የስልክ ግንኙነት በቬገስ ነርቭ (vagus nerve)፣ በሆርሞኖችና በመከላከያ ህዋሳት አማካኝነት በሁለቱም አቅጣጫዎች መልዕክቶች ይተላለፋሉ፤ ከአንጀታችን ወደ አዕምሯችን - ከአዕምሯችን ወደ አንጀታችን።
አዕምሯችንንና አንጀታችንን የሚያገናኛቸው መልዕክት ማስተላለፊያ ስውር የመገናኛ መስመር Gut-Brain Axis (GBA ገት-ብሬይን አክሲስ) በመባል የሚታወቅ ሲሆን በሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች አማካኝነት በስሜቶቻችን (mood)፣ በአስተሳሰባችን (cognition)፣ በውሳኔዎቻችንና (decision) በአካላዊ ጤናችን (physical health) ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ጥናቶች ያስረዳሉ።
በቅድሚያ በስሜቶቻችን፣ በአስተሳሰባችንና በውሳኔዎቻችን ላይ ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ እንመልከት። (አካላዊ ጤናችንን አስመልክቶ የሚኖረውን ተጽዕኖ በተከታዩ የጦማር መጣጥፍ ላይ እንመለከታለን።)
የሆነ ሁኔታ ወይም ሰው አጋጠመን እንበል፦
- በአንጀታችን/በሆዳችን ውስጥ በድንገት የመርገብገብ፣ የመንሰፍሰፍ፣ የመኮማተር፣ የማቅለሽለሽ ወዘተ ዓይነት ስሜት ሲሰማን
- ወዲያውኑ በገት-ብሬይን አክሲስ ስውር የመገናኛ መስመር አድርጎ ከአንጀታችን ወደ አዕምሯችን መልዕክት ይሰራጫል።
- አዕምሯችን መልዕክቱን ሲተረጉምልን "ፈራሁ፣ ደነገጥኩ፣ ጓጓሁ፤ የመረጋጋት ስሜት ተሰማኝ፣ ወዘተ" ብለን ስሜታችንን እንገልጻለን።
- አዕምሯችን ስሜታችንንና የምንገኝበትን ሁኔታ ወይም ያጋጠመንን ሰው ከዚህ ቀደም ከነበሩን ተሞክሮዎች ጋር ፈጥኖ ያመሳክራል፣
- ስለሁኔታው ቅጽበታዊ ግንዛቤ ኖሮን ውሳኔዎችን እንወስናለን።
- "ይህ አጋጣሚ ትክክልና መልካም ሁኔታ ነው።" =› ሁኔታውን እንቀበላለን
- "ይህ ሰው ጥሩ ሰው ይመስላል።" =› እንቀርባለን/ እናስጠጋለን
- "ይህ ሁኔታ ጥሩ አይመስልም/አደገኛ ይመስላል።" =› እንሸሻለን/ እናስወግዳለን
- "ይህ ሰው አይበጀኝም።" =› እናርቃለን/ እንርቃለን
- ወዘተ
፫ኛ/ በደመነፍስ እራስን የማዳንና የመኖር ፍላጎት
ሰዎች ሁሉ - እንደማንኛቸውም ነፍስ ያላቸው ፍጡራን - ከተወለድንባት ደቂቃ አንስቶ እስክንሞት ድረስ በሕይወት ለመቆየት ወይም ነፍሳችንን ለማዳን የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። ይህ ስንወለድ ጀምሮ ከማንነታችን ጋር የተጣመረ በሕይወት ለመቆየት የመፈለግ ደመነፍሳዊ ጉጉትና ትጋት ወይም ሰርቫይቫል ኢንስቲንክት (survival instinct) እራሳችንንና ፍለጎቶቻችንን እንድናስቀድም ይገፋፋናል። ስሆነም የሚከተሉትን እናደርጋለን፦
- መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን እናሟላለን
- ረሃብንና ጥማትን ውኃና ምግብ ፈልገን በማግኘት እናስታግሳለን
- ሲበርደን ወይም ሲሞቀን - እንለብሳለን፣ እንጠለላለን
- ሲደክመን - ዕረፍት እናደርጋለን
- እራሳችንን ከአደገኛ ሁኔታዎች እንከላከላለን
- አምስቱን የስሜት ሕዋሳታችንን ተጠቅመን (ማየት፣ ማዳመጥ፣ ማሽተት፣ መዳሰስና፡መቅመስ) አካባቢያችንና ሁኔታዎችን እንገመግማለን
- በውስጣችን በሚከሰቱት ስሜቶች ተመርተን ክፉና ደጉን እንለያለን
- በሰውነታችን ውስጥ በሚረጩ እዠቶች (secretions) በመታገዝ እርምጃዎችን እንወስዳለን
- ደኅንነታችንን/ህልውናችንን እናስጠብቃለን - ፋይት ኦር ፍላይት (fight or flight) በመባል የሚታወቀውን ደመነፍሳዊ የሰውነት ምላሽ መሠረት ያደርጋል
- አደገኛ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን በድፍረት ተጋፍጠን እንታገላቸዋለን (fight)
- መጋፈጥና መታገል ካልተቻለን እንሸሻለን፣ እራሳችንን እናርቃለን ወይም በተገኘው መንገድ እራሳችንን እንከላከላለን (flight)
- ከሌሎች ጋር ቅርበትን፣ ጓደኝነትን ወይም ዝምድናን እንሻለን
- በሰውነታችን ውስጥ በሚረጨው አቀራራቢ እዠት (Oxytocin - ኦክሲቶሲን) አማካኝነት መቀራረብንና መደጋገፍን እንፈልጋለን
- መተሳሰርን፣ አሉልኝ ብለን በሌሎች ላይ ዕምነት መጣልን (trust)፣ ኅብረተሰብ መገንባትንና ተባብሮ መኖርን እንሻለን
- ጾታዊ ግንኙነት መመሥረትና ዘርን መተካት
- የሚመስለንን ሰው በመቅረብ ጾታዊ ግንኙነት እንገነባለን
- ዘራችንን ለመተካት በመሻት ልጆች እንወልዳለን
ታድያ እነዚህን የተለያዩ ተፈጥሯዊ ክውንታዎች መሠረት በማድረግ 'ሆዳችን ሲነግረን' ልናምነው ይገባልን?
- እራሳችንን ለማዳን እንደሚያግዘን ተገንዝበን "ከዚህ ቦታ ራቁ" ወይም "ይህንን ሰው አትቅረቡ" ብሎ 'ሆዳችን ሲነግረን' በቂ መረጃ ባይኖረንም እንኳን ማዳመጣችን መልካም ይሆናል።
- ስለማንነታችን (identity)፣ ስለጾታዊ ግንኙነታችን (romance)፣ እንዲሁም የፈጠራ ችሎታንን (creativity) አስመልክቶ ውሳኔ መስጠት ካስፈለገን 'ሆዳችንን ማዳመጥ' ይጠቅማል።
- በሃሳብ ብዙ ማብሰልሰልን፣ መጨነቅን ካስከተለብን ወይም የሌላ ሰው/ሁኔታ ተጽዕኖ ከኖረብን ግን 'ሆዳችን የነገረንን' በማዳመጥ እርምጃ ከመውሰዳችን ይልቅ ተጨማሪ መረጃዎችን መሰብሰባችንና ሁኔታውን የበለጠ ለመረዳት መምከራችን እጅጉን ይበጃል ።
'የሆዳችን ስሜት' ከስጋትና ጭንቀት (anxiety) በምን ይለያል?
'ሆዳችን ሲነግረን' በአሁኒቷ ደቂቃ ላይ የተመሠረተ የመረጋጋት፣የማያወላውል እርግጠኝነትና የማወቅ ስሜት የሚሰማን ሲሆን አንግዛየቲ ግን ብርቱ የሰውነት መረበሽን (ለምሳሌ የልብ ትርታ መጨመር) እና ስለወደፊቱ እያሰቡ መጨነቅን የሚያካትት ስሜት ነው።
ከጥልቅ የማወቅ ስሜት (intuition) ጋርስ ልዩነቱ ምን ይሆን?
ሁላቱም በሕይወት ልምድና ተሞክሮ ላይ የተመሠረቱ በደመነፍስ የማወቅ ችሎታዎች ናቸው። ይሁንና በሆድ የማወቅ ስሜት (ገት ፊሊንግ) እራስን በአሁኒቷ ደቂቃ በማትረፍ/በማዳን (survival instinct) ላይ የሚያተኩር ሆኖ ከመፍራት፣ ከመስጋትና ደኅንነትን ከመሻት ጋር የተቆራኘ ነው። በአንጻሩ ደግሞ ጥልቅ የማወቅ ስሜት (ኢንቱኢሽን) ትኩረቱ ሕይወትን በማትረፍ ላይ ሳይኖን ሕይወትን በመምራት ላይ ነው።በእርጋታ ላይ የተመሠረተ ማስተዋልን፣ መገንዘብንና እርግጠኝነትን ያካትታል።