ለሥነ-ልቦናና ለሥነ-አዕምሮ ጤና ትርኩረት እንስጥ

ለሥነ-ልቦናና  ለሥነ-አዕምሮ ጤና  ትርኩረት  እንስጥ
የአዕምሮ ጤናና የአካል ጤና አይነጣጠሉም

የሥነ-ልቦናና የሥነ-አዕምሮ ጤና አገልግሎት ሰጪዎች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ። ለምሳሌ፦ በግል ተቋማት፣ በሆስፒታሎች፣ በክሊኒኮች፣ በድጋፍ መስጫዎች፣ በማገገሚያ ተቋማት፣ በከፍተኛ ትመህርት ተቋማት እና በሌሎችም ሥፍራዎች አገልግሎት ይሰጣሉ።

ሳይኮተራፒ  (psychotherapy) የአስተሳሰብ፣  የባህርይ ፣  የተግባር፣  እንዲሁም  የማሕበራዊ  ኑሮ ግንኙነት  አዎንታዊ  ለውጦችን  ለማስገኘት የሚያገለግል የሥነ-ልቦና ዕርዳታ መስክ ሲሆን በመወያተትና  በመመካከር (talk therapy) ላይ የተመሠረተ የሞያ ዘርፍ ነው።

ግለሰቦች የሳይኮቴራፒ አገልግሎት የሚሹት  በተዛቡ አስተሳሰቦች፣ ስሜቶች፣ ሀድራዎች/ባህሪዎችና ተግባሮች ምክንያት በሕይወታቸው እንዲሁም ከሰዎች ጋር ባሏቸው ግንኙነቶች ውስጥ ችግሮች ገጥመዋቸው መፍትሔ ማግኘት ሲያዳግታቸውና የዕላት-ከዕለት ኑሮን ማሸነፍ/መግፋት ሲሳናቸው አለዚያም ሁኔታዎች ውስጣዊ ሰላም ሲነሷቸው ነው።

ሳይኮተራፒስቶች (psychotherapists) በመግባባት፣ በማዳመጥ፣ አስተያየታቸውን ከመስጠት በመቆጠብና ከተገልጋዮች ጋር የተወያዩባቸውን ጉዳዮች በምሥጢር  በመጠበቅ  ላይ የተመተመሠረተ የሥነ-ልቦና ዕርዳታ ይሰጣሉ። በተጨማሪም በባህርይም ይሁን በሕይወት ልምድ ሰው ከሰው እንደሚለያይ በመገንዘብ አዕምሯቸውን ክፍት አድርገው ያለ ምንም ትዝብት የተገልጋዩን ሃሳብና ስሜት ይከተላሉ። ስለሆነም ተገልጋዮች  የተናገሩት ወደ ሌላ ሰው ጆሮ እንደማይዛመት እንዲሁም በተናገሩት ነገር ሳይኮቴራፒስቱ እንደማይታዘቧቸው ዕምነት ኖሯቸው የልባቸውን ለማውራትና ስሜታቸውን ለመግለጽ ድፍረት ያገኛሉ።

የኑሮ ጫናና ዕክሎች እንዲሁም የተለያዩ የሕይወት ገጠመኞች የአዕምሮ ውጥረት (stress)፣ ጭንቀትና (anxiety) ድብርት (depression) ሊያስከትሉ ይችላሉ። እነዚህን ስሜቶች ለመቋቋምና የመንፈስ እርጋታን ለማግኘት ከሳይኮቴራፒስት ጋር የመወያየት(individual therapy) ጥቅሙ ከፍተኛ ነው ተብሎ ይታመናል ።

በትዳር ወይም በጾታዊ ወዳጅነት ውስጥ (couples therapy) እና በቤተሰብ አባላት መካከል በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እንዲሁም ልጆችን በማሳደግ ዙሪያ ስለሚከሰቱ ውጣ ውረዶች (family therapy) በአማካዩ በየሁለት ሳምንታት ለአንድ ሰዓት ያህል በመገናኘት መወያየትና መፍትሔዎችን ከተገልጋዮች ጋር አብሮ መፈለግ በሳይኮቴራፒ ከሚሰጡ አገልግሎቶች ውስጥ እንደምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው። ሌላ ውጤታማነቱ የታመነበት የሥነ-ልቦና ዕርዳታ አሰጣት ዘዴ ከአሥር የማይበልጡ ሰዎችን በማሰባሰብ በየጊዜው እየተገናኙ የሚደረግ የእርስ-በእርስ የመደጋገፍ ውይይት (group therapy) ነው።

ሳይኮቴራፒ (psychotherapy) ከካውንስሊንግና  (counselling) ከመንፈሳዊ  ካውስሊንግ (spiritual counselling) ጋር በአያሌ ገጽታዎቹ ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም በመካከላቸው ጥቂት ልዩነቶች እንዳሉ ይታወቃል። ካውንስሊንግ መረጃና  ምክር መለገስን እንዲሁም መመሪያ  መስጠትን  ያከለ ሲሆን መንፈሳዊ  ካውንስሊንግ  ደግሞ  መንፈሳዊና  ዕምነትን  ያዘሉ ምክሮችን  የሚያካትት የሥነ-ልቦና ዕርዳታ አሰጣጥ መንገድ ነው።

ሳይካያትሪ (psychiatry) ወይም የሥነ-አዕምሮ ሕክምና  ከፍ ብሎ ከተጠቀሱት የሚለየው ከሕክምና ልዩ ዘርፎች (specializations) አንዱ በመሆኑ ነው። ሳይካያትሪስቶች (psychiatrists) ወይም የሥነ-አዕምሮ ሐኪሞች በምርመርራ የአዕምሮ ሕመም መኖር ወይም አለመኖሩን የሚያረጋግጡ፣ እንደየአስፈላጊነቱ መድሐኒት የሚያዝዙ፣ በተጨማሪም የመድሐኒት ዓይነትም ይሁን የመጠን ለውጥ ቢያስፈልግ ለታካሚዎች በማስተማርና በማስረዳት ተገቢውን ክትትል የሚያደርጉ የጤና ባለሞያዎች ናቸው።

በግል  ሕይወትዎም  ይሁን  ከሌሎች ሰዎች  ጋር ባልዎት  ግንኙነቶች  ውስጥ ግራ የመጋባት፣ መላ ወይም  ደስታን የማጣት፣ እንዲሁም የጭንቀት፣  የኅዘን፣  የድብርትና ሌሎች  ሥነ-ልቦናን የሚረብሹ ጉዳዮች ወይም ሁኔታዎች ቢያጋጥምዎ በይሉኝታ ተገድበው ለብቻዎ ከማብሰልሰል ይልቅ ከሥነ-ልቦና ጤና ባለሞያ ዕርዳታ በመጠየቅ ለአዕምሮዎ ጤና እንክብካቤ ማድረግዎ ለአካልዎ ጤና ከሚያደርጉት እንክብካቤ ጎን-ለጎን ሊያካሄድ የሚገባና የሚበረታታ ነው ።

ለልብ ህመምና ለሌሎች በሽታዎች ከስፔሻሊስት ተጨማሪ አስተያየትና እንክብካቤ እንደሚጠይቁ ሁሉ የሥነ-አዕምሮ ህመም/በሽታ  ይኖረኝ ይሆን ብለው ከጠረጠሩ  ሐኪምዎ ወደ ሳይካያትሪስት  ይልክዎት ዘንድ (ሪፈራል - referral ) መጠየቅዎ ለአዕምሮዎ ጤና ተገቢውን እንክብካቤ መስጠትዎን፣ መንፈሰ ጠንካራነትዎንና ወኔ(courage) እንዳልዎት የሚገልጽ እንጂ ድክመትዎን የሚያመለክት አይሆንም።


ለድንገተኛና ለአጠቃላይ የአዕምሮ ውጥረት ዕርዳታ ካስፈለግዎ

Immediate & General Crisis Helplines

  • ሕይወትዎን ለማጥፋት የሚገፋፋ ስሜት ካደረብዎ ወይም የሚያውቁት ሰው እራሳቸውን ለማጥፋት ፍላጎት ካደረባቸው 9-8-8 ይደውሉ ወይም ቴክስት ያድርጉ Suicide Crisis Helpline: Call or text 9-8-8 for suicide and crisis hotline toll-free, anytime across Canada, for support if you or someone you know is thinking about suicide.
  • ከፖሊስ ነጻ የሆነና በማኅበረሰብ አባላት የሚመራ - ለማያስቸኩል የአዕምሮ ጤና ዕርዳታ ለማግኘት 211  ይደውሉ Toronto Community Crisis Service (TCCS): Call 211 to access this non-police, community-led service that dispatches trained crisis workers for non-emergency mental health crises and wellness checks in certain areas of Toronto.
  • የ24 ሰዓት የስልክ የአዕምሮ ውጥረት ዕርዳታ ለቶሮንቶና አካባቢዋ Distress Centres of Greater Toronto: Offers 24/7 crisis intervention and emotional support.
  • በአስተርጓሚ በመታገዝ አስቸኳይ የአዕምሮ ጤና የ24 ሰዓት ዕርዳታ ለማግኘት Gerstein Centre Crisis Line: Provides 24/7 community-based crisis support with language interpretation services available.
  • ለአዕምሮ ጤና፣ ለሱሰኝነት፣ እንዲሁም የቁማር ሱስ የ24 ሰዓት የስልክ ዕርዳታ ለማግኘት ConnexOntario: Provides 24/7 information and referral services for mental health, addiction, and problem gambling services across Ontario.
  • ለልጆች የ24 ሰዓት የስልክ ዕርዳታ Kids Help Phone: Offers 24/7 free, confidential, and anonymous professional counselling and support to young people across Canada.
  • ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የ24 ሰዓት የስልክ ዕርዳታ ለማግኘት Assaulted Women's Helpline: Provides 24/7 crisis counselling and safety planning for women in the GTA.
  • ለአረጋውያን የስልክ ዕርዳታ Toronto Seniors Helpline: A single point of access for seniors and caregivers to access community, home, and crisis services.

ለቶሮንቶ እና አካባቢው አጠቃላይ መረጃዎችን ለማግኘት 211 ይደውሉ Call 211 to find information on a comprehensive list of community and social services throughout the GTA. 


Read more

የኮንሸስ ፓረንቲንግ  ፍልስፍና                                              - አስተዳደግ ክፍል ፫

የኮንሸስ ፓረንቲንግ ፍልስፍና - አስተዳደግ ክፍል ፫

ኮንሸስ ፓረንቲንግ (conscious parenting = የንቁ-ሕሊና የአስተዳደግ ዘዴ) በአስተውሎት ወይም በmindfulness ላይ የተመሠረተ የልጆች አስተዳደግ ፍልስፍና ሲሆን የሚከተሉትን ዋና-ዋና ባህርያት ያካትታል። * ወላጆች ስለእራሳቸው የተሻለ ግንዛቤ (self-awareness) እንዲኖራቸው እንዲሁም 'እውነተኛ ማንነታቸውን' (authentic self) በበለጠ ለመረዳት ሲሉ ለስሜቶቻቸው ትኩረት እየሰጡ እራሳቸውን ይመረምራሉ (self-reflection) * የልጆችን አስግተዳደግ አስመልክቶ ያሏቸውን ቅድመ-ግንዛቤዎች በመመርመር አመለካከቶቻቸውንና ተግባሮቻቸውን

By TW
የአንጀት ደህንነት-ለጠቅላላ ጤንነት

የአንጀት ደህንነት-ለጠቅላላ ጤንነት

በአዕላፋት የሚቆጠሩ የተፈላጊ ረቂቃን ነፍሳት ሕብረተሰብ ወይም ማይክሮባዮም (microbiome) በቆዳችን ላይና በሰውነታችን ውስጥ ይገኛል። ከሌሎቹ የሰውነታችን ክፍሎች ጋር ሲነጻጸር በአንጀታችን ውስጥ የሚገኘው የማይክሮባዮም መጠን ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። የአንጀት ውስጥ ማይክሮባዮም ማይክሮባዮም እንደ ባክቴሪያ (የbacteria ነጠላ ስም ባክቴሪየም- bacterium ነው)፣ ቫይረሶች (virus/ viruses)፣ ፈንገሶችና (fungus/fungi) ጥገኛ ነፍሳት (parasites) ያሉ ተህዋሳትን

By TW
"ሆዴ ነግሮኝ ነበረ!"

"ሆዴ ነግሮኝ ነበረ!"

"እኔኮ ታውቆኝ ነበረ፣ ሆዴ ነግሮኝ ነበረ፤ ..." ስንል ምን ማለታችን ነው? * ለመረዳትና ለማብራራት በሚያዳግት ሁኔታ አንዳንድ አጋጣሚዎች ወይም ቦታዎች በውስጣችን ያለመመቸት ስሜት የሚቀሰቅሱብን ለምን ይሆን? * ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅነውን ሰው፣ ስለማንነቱ ብዙም ሳንውቅ ሆዳችን እንድንርቀው የሚገፋፋንስ ለምንድን ነው? * ደግሞስ ሆዳችን ነግሮን በእርግጠኝነትና በፍጥነት ትክክለኛ ውሳኔ የምንወስነው እንዴት ሆኖ ነው? የሆድ

By TW
በመምታት ልጆችን መቅጣት?                                        - አስተዳደግ ክፍል ፪

በመምታት ልጆችን መቅጣት? - አስተዳደግ ክፍል ፪

በ1989 እ.ኤ.አ. በተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ 196 አገራት የልጆችን ሰባዓዊ መብቶች የሚያስጠብቅ ስምምነት ተፈራርመዋል (United Nations Conventions on the Rights of the Child - UNCRC)። ይህንን ስምምነት ኢትዮጵያና ካናዳ - በ1991 (እ.ኤ.አ.)፣ ኤርትራ ደግሞ በ1994 (እ.ኤ.አ.) በሕጎቻቸው ውስጥ አካትተው አጽድቀዋል። የሚከተሉትን የስምምነት አንቀጾች እንመልከት፦

By TW