የኮንሸስ ፓረንቲንግ ፍልስፍና - አስተዳደግ ክፍል ፫
ኮንሸስ ፓረንቲንግ (conscious parenting = የንቁ-ሕሊና የአስተዳደግ ዘዴ) በአስተውሎት ወይም በmindfulness ላይ የተመሠረተ የልጆች አስተዳደግ ፍልስፍና ሲሆን የሚከተሉትን ዋና-ዋና ባህርያት ያካትታል።
- ወላጆች ስለእራሳቸው የተሻለ ግንዛቤ (self-awareness) እንዲኖራቸው እንዲሁም 'እውነተኛ ማንነታቸውን' (authentic self) በበለጠ ለመረዳት ሲሉ ለስሜቶቻቸው ትኩረት እየሰጡ እራሳቸውን ይመረምራሉ (self-reflection)
- የልጆችን አስግተዳደግ አስመልክቶ ያሏቸውን ቅድመ-ግንዛቤዎች በመመርመር አመለካከቶቻቸውንና ተግባሮቻቸውን ለማሻሻል ወይም ለመለወጥ ጥረት ያደርጋሉ
- ያለምንም ተጽዕኖ ለልጆቻቸው ዕርዳታን ለመለገስ ትጋት ያሳያሉ
የዚህ ፍልስፍና መሠረታዊ ሀሳብ የልጆችን አስተዳደግ ከወላጆቻቸው 'ውስጣዊ ዕድገት' (internal growth) ጎን ለጎን ማካሄድ ሲሆን Dr. Shefali Tsabary የተባሉ የስነ-ልቦና ባለሞያ በጻፍዋቸው መጻሕፍትና ባቀረቧቸው ንግግሮች ዝናን እያተረፈ የመጣ የአስተዳደግ ዘዴ ነው።
የንቁ-ሕሊናን የአስተዳደግ ዘዴ ተግባራዊ ለማድረግ የሚሹ ወላጆች ለሚከተሉት ነጥቦች ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
- ምን-ምን ዓይነት ሁኔታዎች በውስጣቸው ስሜቶቻቸውን እንደሚቀሰቅሱ ማስተዋል
- የልጆቻቸውን እንዲሁም የእራሳቸውን መሠረታዊ ፍላጎቶች በትዕግስት መርምረው ለመረዳት መጣር
- አስተውሎትን (mindfulness)፣ ርኅራሔንና (compassion)፣ እውነተኝነትን (authenticity) መተግበር
ዶ/ር ሸፋሊ ስለ የንቁ-ሕሊና አስተዳደግ ጥቅም ሲያስረዱ በወላጆችና በልጆቻቸው መሀከል መቀራረብንና መከባበርን የሚያበረታታ ፍልስፍና መሆኑን ይናገራሉ። ልጆች ወላጆቻቸው እንደሚያዳምጧቸው፣ ለማንነታቸውና ለአመለካከቶቻቸው ቦታ እንደሚሰጡ እምነት እንዲያድርባቸው ያደርጋል ይላሉ። ስለሆነም በወላጆችና በልጆቻቸው መሀከል መተባበርንና መተጋገዝን በማጠናከር የልጆችን ስሜታዊ ብልህነት ወይም ብስለት (emotional intelligence) ሊያዳብር እንደሚችልም ይናገራሉ።
የንቁ-ሕሊና የአስተዳደግ ዘዴ በክፍል ፩ እና ፪ ከተነጋገርንባቸው የአስተዳደግ ዘዴዎች ለየት ይላል። የበፊተኞቹ የአስተዳደግ ዘዴዎች በአሳዳጊዎችና ልጆቻቸው ግንኙነት ላይ የሚያተኩሩ ሲሆኑ የንቁ-ሕሊና አስተዳደግ ደግሞ አሳዳጊዎች ወደ ውስጣቸው እንዲመለከቱና ለስሜቶቻቸውና ለተግባሮቻቸው መሠረቱ ምን እንደሆነ መርምረው እንዲገነዘቡ፣ ተገንዝበውም በትጉ-መንፈስ (presence) ልጆቻቸውን ለማሳደግ እንዲሞክሩ የሚጋብዝ የአስተዳደግ ፍልስፍና ነው።
እራስን መረዳት
፩ኛ/ ስሜትን በመከታተልና ባህርይን በመገምገም
- ስሜትን በተመለከተ - ለምሳሌ፦
- "ልጆች ሲንጫጩ ለምን ትዕግስት የማጣት/ የንዴት/ የጭንቀት ስሜት ይሰማኛል?"
- "ወንድ ልጄ ከእኅቶቹ ጋር በአሻንጉሊት ሲጫወት ለምንድን ነው ፍርኀት-ፍርኀት የሚለኝ ወይም የሚያስጨንቀኝ?"
- "ወጣቷ ልጄ ከጓደኞቿ ጋር አይስክሪም ለመብላት በአቅራቢያችን ወዳለው ሱቅ በእግሯ ለመሄድ ስታስፈቅደኝ ምንድን ነው እንድጠራጠርና እንድፈርራ የሚያደርገኝ?"
- ወዘተ
- ባህርይና ተግባርን በተመለከተ - ለምሳሌ፦
- "ስናደድ ለምን ልጆቼ ላይ እጮሃለሁ? ለምንስ እማታለሁ?"
- "ልጆቼ በትምህርታቸው የጠበቅሁትን ውጤት ካላመጡ ለምን ፊት እነሳቸዋለሁ?"
- ልጆቼ ጥያቄ ሲጠይቁኝ ዕውነቱን ለምን አድበሰብሳለሁ?"
- ወዘተ
፪ኛ/ እውነተኝነትን በመተግበር (authenticity)
- የምናምንባቸውን ሁኔታዎች/ነገሮች/አመለካከቶች በግልጽ ለይተን ለማወቅ በመሞከር (self-awareness)
- እሴቶቻችን፣ አስተሳሰባችን እና ተግባሮቻችን እንዲስማሙ በመጣር (alignment)
- በሐቀኝነት በመመራት (integrity)
- ለአመንንበት ነገር በመቆም (አዳጋች ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ጭምር)
- ማስመሰልን በማስወገድ - ሌሎች ባይቀበሉትም የምናውቀውንና ያመንንበትን በሐቅ በመግለጽ፣ ለይሉንታ ባለመገዛት
- በተለያዩ አካባቢዎችና ሁኔታዎች ባህርያችን/ጸባያችን አይለዋወጥም (consistency)
- አቋማችን/ተግባራች/ምርጫችን/ ጥፋታችን ለሚያስከትሏቸው ሁሉ ኀላፊነትን በመውሰድ (responsibility)
የእውነተኝነት ጥቅም
- የአዕምሮ ጤንነትን ያዳብራል - እውነተኝነት በእራስ መተማመንን፣ በፍላጎት መመራትን በማጽናት የውስጣዊ ሰላምንና ደህንነትን ያበረታታል
- ጤናማ ግንኙነቶችን ያጠናክራል - በሰዎች መሀከል እምነት እንዲኖር በማድረግ የእርስ-በእርስ መተሳሰርን ያጎለብታል
- ችግሮችን የመቋቋም ችሎታን (resilience) ያዳብራል - ብቸኝነት የሚያስከትለውን ጉዳት እንዲሁም የዕለት-ተዕለት ፈተናዎችን ተጋፍጦ የመወጣት ዐቅምና ችሎታ እንዲጠነክር ያደርጋል
የይሉኝታ ባህል በተስፋፋበት ኅብረተሰብ ውስጥ በሁሉም ዘርፍ እውነተኝነትን ማሳየት በሌሎች ዘንድ ሊያስገምተንና አሉታዊ አመለካከትን ሊያስከትልብን እንደሚችል ግልጽ ነው። ይሁንና ዶ/ር ሸፋሊ ከተናገሩት ውስጥ ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው በልጆች አስተዳደግ ሂደት ውስጥ የሚተገበር እውነተኝነት ጥቅሙ ከፍተኝነቱ የሚታመንበት ስለሆነ እጅጉን የሚበረታታ ነው።
የስሜት ቃታዎች
(triggers)
መልስ ለማግኘት በሚያዳግት መልኩ ኢምንት ናቸው ብለን የምንገምታቸው ሁኔታዎች ከፍተኛ ስሜት ሰጥተውን በመናደድ ተቆትጥተን፣ በፍርኀት ተሽቆጥቁጠን፣ በስጋት ተጠራጥረን፣ ... ይሆናል። "ምን ነክቶኝ ነው ይህንን ዓይነት ጸባይ/ ባህርይ ያሳየሁት?" ብለንም እራሳችንን ጠይቀንም ይሆናል።
በልጅነታችን የደረሱብን በደሎች እንዲሁም ካደግንም በኋላ ያጋጠሙን አደገኛ ሁኔታዎች በውስጣችን የሚያሳድሯቸው ከባድ ስሜቶች በአዕምሯችን ውስጥ ጠባሳን ሊተዉ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ። እነዚህ በጠባሳ ተሸፍነው የቆዩ ሥር-ሰደድ ስሜቶች ለእኛ ግልጽ ባልሆኑ አነሳሽ ምክንያቶች ከደነዘዙበት በድንገት ሲቀሰቀሱ ከመጠን በላይ የገነነ ስሜት ሊሰማንና የመበርገግ፣ የመሸሽ፣ የመፍራት፣ የመደንዘዝ፣ ወይም ሌሎች ያለተጠበቁ ባህርያትን ልናሳይ እንደምንችልም መረጃዎቹ ጨምረው ያስረዳሉ።
የደነዘዘ ውስጣዊ ስሜትን ቀስቃሽ/ ስሜትን አንቂ/ ስሜትን አስታዋሽ ሁኔታዎች ትሪገርስ (triggers) በመባል ይታወቃሉ። (የgoogle translate ትርጉም ቀስቅሴዎች ነው) እነዚህ የስሜት ቃታዎች ከተለያዩ የሕይወት ተሞክሮዎቻችን ጋር ተጣምረው ይገኛሉ። ለምሳሌ፦
- ስለእራሳችን ካሉን ስሜታዊ ግንዛቤዎች ጋር በመጣመር (emotional triggers)- የብቃት ማነስ ስሜት፣ ጥቃት ወይም ጉዳት ይደርስብናል ብለን ስንገምትና ፍርሃት ሲያድርብን፣ ወዘተ
- በአካባቢያችን ከሚገኙ ሁኔታዎች ጋር በመጣመር (environmental triggers)- ቦታዎች፣ ቁሳቁሶች፣ ድምጾች፣ ጠረኖች፣ ወዘተ
- ከአካላዊ ስሜቶች ጋር በመጣመር (internal/physical triggers) - እንደ ሕመም፣ በሽታ፣ ድካም፣ ረሃብ፣ ወዘተ
በስሜት ቃታዎች አማካኝነት በውስጣችን ለሚከሰቱት ስሜታዊ ውጥረቶች (stress) እንዲሁም የጸባይና የባህርይ አሉታዊ ለውጦች ትኩረት በመስጠት ለመረዳት መሞከራችን ውስጣዊ ቁስሎቻችን የትኛዎቹ እንደሆኑና መሠረታቸው ምን እንደሆነ ለመገንዘብ ያስችለናል። ለአዕምሮ ጤናችን መታወክ ምክንያቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እንድንመረምርና አስፈላጊውን መፍትሔ እንድንፈልግም መንገድ ይከፍታል።
እራሳችንን ተገንዝበን ተገቢውን መፍትሔና እርዳታ ስናገኝ ደግሞ በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ ሊከሰቱ የሚችሉ የስነ-አዕምሮ እንዲሁም የስነ-ልቦና ጉዳቶቻችን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዳይተላለፉ ለመከላከል የሚያስችል ብቃት ይሰጠናል። በተጨማሪም ጤነኛ ቤተሰባዊና ማሕበራዊ የእርስ-በእርስ ግንኙነቶችን በመገንባት ጤነኛ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ያመቻችልናል።
ስድስቱ የንቁ-ኅሊና የአስተዳደግ ዘዴ መርሆዎች፦
፩/ እራስን ለማወቅና ለመረዳት መትጋት
(Self-awareness)
የንቁ ሕሊናን የአስተዳደግ ዘዴ የሚመርጡ ወላጆች የሚከተሉትን ሊያስተውሉ ይገባል፦
- ለሁኔታዎች የሚያሳይዋቸውን ባህርዮች እንዲሁም የሚሰጧቸውን ምላሾች
- በውስጣቸው የሚቀሰቀሱትን ስሜቶች
- በአዕምሯቸው የሚመጡትን ሀሳቦች
- ትክክል ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውን አመለካከቶች ወይም ግንዛቤዎች
- በተደጋጋሚ በእራሳቸው ላይ ያስተዋሏቸውን ባህርያትና የስሜት ቃታዎች
፪/ በአስተውሎት መገኘት
(Mindfulness)
አሳዳጊዎች ከልጆቻቸው ጋር በሚኖሯቸው መስተጋብሮች ሙሉ ልባቸውን በመስጠት የእዚህና-የአሁን (here and now) ቆይታ ይጠበቅባቸዋል ።
- ሀሳባቸውን የሚበትኑ ሁኔታዎችን ማስወገድ
- ስለወደፊቱ እያሰቡ አለመጨነቅ
- ስላለፈው እያብሰለሰሉ አለመቆጨት
የዚህ ዓይነቱ ሙሉ ልብን ሰጥቶ የእዚህና-የአሁን ቆይታ (presence) ወላጆች ርኅራሄ (empathy) ኖሯቸው ልጆቻቸውን በማዳመጥ እንዲገነዘቧቸውና ከልጆቻቸው ጋር ያላቸው ቅርበት እንዲሁም መተሳሰር እንዲሻሻልና እንዲጠናከር ዕድል ይከፍታል።
፫/ አለመኮነን ወይም አለመፍረድ
(Nonjudgmental approach)
ይህ አመለካከት በልጆች አስተዳደግ ሂደት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሕይወታችን ልንተገብረው የሚገባ እሴት ነው።
- ስለእራሳችን፣ ስለልጆቻችን፣ ስለአሳዳጊነት ብቃታችን፣ ወዘተ ያሉንን ቅድመ-ግምቶችና (expectations) አመለካከቶች (notions) ወደጎን ተወት በማድረግ
- እኛ ስለሚኖሩን ወይም ልጆቻችን ስለሚኖሯቸው ሀሳቦች፣ ስሜቶችና ባህርዮች "ጥሩ ነው" ወይም "መጥፎ ነው" የሚል ግምትና አስተያየት ከመስጠት በመቆጠብ
- ሁኔታዎች በእኛና በልጆቻችን ውስጥ የሚቀሰቅሷቸውን ስሜቶችና የምናንጸባርቃቸውን ባህርያት ለመረዳት/ለመገንዘብ ጉጉት በማሳየት
፬/ መታገስ
(Patience)
ልጆችን ማሳደግ ከወላጆችና ከአሳዳጊዎች ሰፊ ትዕግስትን የሚጠይቅ ከባድ ኀላፊነት መሆኑ ግልጽ ነው። ስለሆነም የሚከተሉትን ዕውነታዎች ማስታወስ ይጠቅማል፦
- ለውጥ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሂደት ነው
- ልጆች በዕድገታቸው ሂደት ያለማቋረጥ ዕውቀትን ይቀስማሉ፣ ይለወጣሉ
አሳዳጊዎች ትዕግስትን የዕለት-ተዕለት ልማዳቸው ሲያደርጉ በልጆች አስተዳደግ ሒደት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አዳጋች ሁኔታዎች ለመወጣት በሚያደርጉት ጥረት ስሜታዊ ሆነው የከፋ ባህርይ ከማሳየት ይልቅ ዕርጋታ በተሞላበትና ሚዛናዊ በሆነ መንፈስ ፈተናዎችን ለመቋቋምና ለመወጣት ያስችላቸዋል።
፭/ ርኅራሄን ማሳየት
(Empathy)
ርኅራሄን ማሳየት የንቁ-ኅሊና አስተዳደግ ዋና መሠረት ስለሆነ የሚከተሉትን እንድናስተውል ይመከራል፦
- ፍጹምነት ከማንም ሰው የሚጠበቅ ነገር አለመሆኑን አሳዳጊዎች እንዲያስታውሱ
- የእራሳቸውንና የልጆቻቸውን ስሜቶች እንዲሁም ባህርዮች የበለጠ ለመረዳት ጥረት እንዲያደርጉ
- ለእራሳቸውና ለልጆቻቸው ይቅርታ ማድረግን፣ ኀዘኔታንና ደግነትን እንዲለግሱ
- ከትችትና (criticism) እራሳቸውንም ይሁን ልጆቻቸውን ከመኮነን (judgment) እንዲቆጠቡ
አሳዳጊዎች ለእራሳቸውም ይሁን ለልጆቻቸው ርኅራሄን በሚያስዩበት ጊዜ ልጆች መረጋጋትና ደህንነት ይሰማቸዋል። በተጨማሪም አሳዳጊዎቻቸው እንደሚወዷቸው፤ ስሜታቸውን፣ ሃሳባቸውንና ፍላጎታቸውን ለመረዳት እንደሚተጉ ሆኖ ተሰምቷቸው ውስጣዊ ሰላም ያገኛሉ።
፮/ ለእራስ እንክብካቤን መለገስ
(Self-care)
አሳዳጊዎች የዕረፍትና የመዝናኛ እንዲሁም እራስን የመገምገሚያ (self-reflection) ጊዜ ለእራሳቸው ሊሰጡ ይገባል። የእንክብካቤና የጥንቃቄ ጊዜ ለእራሳቸው መፍቀዳቸው ጤናቸው እንዲጠበቅ ከማገዙም በላይ የተሻለ ዐቅምና ትዕግስት ኖሯቸው አዳጋች ሁኔታዎችን በጥሩ ሁኔታ ለመወጣት ያስችላቸዋል፤ ለልጆቻቸውም በትጋት መንፈስ የሚገኙ (present & attentive) መልካም አሳዳጊዎች በመሆን ደስተኞች፤ ጤነኞችና የተረጋጉ ዜጋዎችን ለማሳደግ ብቁ ያደርጋቸዋል ።
መደምደሚያ፦
ከአስተዳደግ በደል ጋር የተያያዙ የስሜት ቃታዎች በዕድገታችን ወቅትም ይሁን ካደግንም በኋላ ባልጠበቅነው ጊዜና ሁኔታ የተጋነኑ ስሜቶች እንዲሰሙን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተረድተናል። ተያይዞም ልጆችን ስናሳድግ ባህርያቸው፣ ጸባያቸው ወይም ተግባሮቻቸው ለእኛ ስሜትን ቀስቃሽ ቃታዎች ሊሆኑና በውስጣችን የንዴት፣ የኅዘን፣ የፍርኃትና የመሳሰሉትን ስሜቶች በማነሳሳት ባህሪያችንን ሊያውኩ እንደሚችሉም ተገንዝበናል።
የንቁ-ኅሊና የአስተዳደግ ዘዴ በዚህ ዕውነታ ላይ የተመረኮዘና በልጆች አስተዳደግ ሒደት ውስጥ አሳዳጊዎች ውስጣዊ ጠባሳቸውን መርምረው እንዲረዱ የሚጋብዝ እንዲሁም ስሜታቸውን ለመግራት እንዲተጉ የሚያበረታታ እንደሆነም ልናይ ችላናል።
ጤናማና ሰላማዊ መንፈስ ለተሞላበት የአስተዳደግ ዘዴ መንገድ ከፋች ፍልስፍና በመሆኑ የንቁ-ሕሊናን የአስተዳደግ መንገድ መከተል ይጠቅማል።
Core Principles of Conscious Parenting፡
- Healing Yourself First: The focus is on parents' inner work and on addressing their own triggers and past traumas.
- Connection Over Control: Moving away from controlling behaviour to building a deep, authentic bond with the child.
- Presence Over Performance: Being fully present in the moment rather than trying to achieve a perfect, idealized family image.
- Viewing Children as Mirrors: Recognizing that a child's "misbehaviour" often reflects the parent's unresolved issues.
መረጃዎች፦
- Gottman & DeClaire, 1998
- Kabat-Zinn, 2013
- Tsabary, 2010 & 2023