ይሉኝታ፡ ምንድነው?

ይሉኝታ፡ ምንድነው?
Photo by David Sacks - gettyimages

 

የይሉኝታ ባሕል

ይሉኝታ በተለያዩ የኢትዮጵያ ጎሳዎችና ማሕበረስቦች የሚተገበር የትሕትናና የጨዋነት ባሕል ነው።

የትሕትና፡ ልምዶች (ሩክያ፡ ሐሰን - 2008)

  • እንደየማሕበረሰቡ ባህልና ቋንቋ በተለያዩ መንገዶች የሚገለጹ እንጂ ዓለም አቀፍ ባሕርይ ያላቸው አይደሉም።
  • በአንድ አካባቢ የትሕትና፣ የጨዋነት ወይም የአክብሮት ባሕል ተብሎ የሚወሰድ/የሚታይ አባባል/ ሁኔታ/ ተግባር በሌላ አካባቢ አሳፋሪና አስቆጪ ነው ተብሎ ሊገመገምና ሊወሰድ ይችላል።
  • ትሕትና የሐቀኝነት ወይም የእውነተኛነት መለኪያ አይደልም። በአንድ በኩል ሰዎችን ላለማስቸገር፣ ላለማሳፈር ወይም ላለማስቀየም የሚተገበር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች ሰዎች ስለእኛ መልካም አመለካከት እንዲኖራቸው የምንገለገልባቸው የማስመሰል ተግባሮች፣ ባሕርይና አነጋገሮች ናቸው።
  • እርስ በርሳችን እንድንግባባና እንድንቀራረብ የሚያግዙን ልምዶች ናቸው።

 የይሉኝታ ጽንሰ-ሐሳብ (ኒና፡ ኢቬይሰን - 2018)

  • ደንብና ሥርዓትን አዘል ባህል ስለሆነ ይሉኝታ ትብብርንና ሁሉ-አቀፍነትን ያበረታታል
  • መልካም ስምና ክብርን ለመጠበቅ ይጠቅማል
  • “ሰዎች ምን ይላሉ?” ብለን በማሰብ አኳኋናችን፣ ተግባራችን ወይም አነጋገራችን በሌሎች ዘንድ ትዝብት ላይ እንዳይጥለን እንድንጠነቀቅና እንድንቆጠብ ያደርገናል
  • ጠቃሚ ባህላዊ እሴቶችን እንዲሁም የእርስ በእርስ መስተጋብርን በማበረታታት መልካም ሥነ-ምግባርን ለማጠናከር ያግዛል

የይሉኝታ፡ ተጽዕኖ (ዳርጌ፡ ዎሌ - 2018)

  • የማህበረሰብን ስሜትና የንቃተ ህሊና ደረጃ ይገልጻል/ ያሳያል
  • የተጋነነ “ሰዎች ምን ይሉኛል” የሚል ጋትና ጭንቀት በሰዎች ላይ የሳድራል
  • ትችትን በመፍራት እራሳችንን ከሚጠቅም ዕድል/ ሁኔታ/ተግባር እንድንቆጠብ ወይም እራሳችንን እንድናግድ/እንድንገታ ያደርገናል
  • ከሰዎች ተግሣጽ እራስን ለማዳን ሲባል የማስመሰል ባሕርይ እንድናሳይ ይገፋፋናል:: ስለዚህም፣- ከዕምነታችን/ ከእሴቶቻችን የራቀ ተግባር ወይም ባሕርይ እናሳያለን፤ እንዲሁም ለማንፈልገውና ለማይመቸን ውጤት እራሳችንን እንዳርጋለን።

ቀላልም ይሁን ከባድ ፈተና በሚያጋጥመን ወቅት ሰው ምን ይለኛል ብለን በመፍራት ችግራችንን ለሌሎች ከማካፈል ይልቅ በውስጣችን አፍነን መያዝ ይሉኝታ ከሚያስከትላቸው አሉታዊ ተጽዕኖዎች አንዱ ነው። በይሉኝታ ላይ የተመሠረተ ፍርሃት የአካል ወይም የአዕምሮ ጤና ቀውስ ሲደርስብን በወቅቱ ዕርዳታና ድጋፍ እንዳንሻ ከማገዱ ባሻገር ልንወጣው የማንችለው ፈተና የገጠመን መስሎ ታይቶን እራሳችንን ለሥጋትና ጭንቀት እንድንዳርግ መንገድ ይከፍታል። በይሉኝታ ሳብያ ዕርዳታን ከመጠይቅ ወደኋላ ከማለት ይልቅ የማይበጁንን ልምዶች በመመርመር በአመለካከቶቻችን፣ በተግባሮቻችንና በሁኔታዎቻችን ላይ ለውጦችን እናምጣ።

ተረትና፡ ምሳሌ

  • ለሰው መድሐኒቱ ሰው ነው
  • ሕመሙን የደበቀ መድሐኒት የለውም

ማመሳከሪያ፤

አቢሲኒካ መዝገበ ቃላት

https://www.researchgate.net/publication/301252950

https://culturalatlas.sbs.com.au/ethiopian-culture/ethiopian-culture-coreconcepts#yilugnta-selflessness-or-public-self-consciousness-

https://ijer.inased.org/makale/437