አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች
ተፈላልገውና ተመራርጠው አብረው ለመሆን ወይም ኑሮን አብረው ለመመሥረት የሚወስኑ ሁለት ሰዎች ወይም ጥንዶች (couples - ካፕልስ) ለግንኙነታቸው መሳካት ወይም አለመሳካት የየግላቸው የሕይወት ልምዶችና ተሞክሮዎች፣ እሤቶቻቸው እንዲሁም ሕልማቸውና ስለወደፊቱ ሕይወታቸው ያላቸው ተስፋ ወሳኝነት አላቸው።
ጆን እና ጁሊ ጎትማን የተባሉ ሁለት ሳይኮሎጂስቶች (Drs. John & Julie Gottman) የጎትማን ሜተድ በመባል የሚታወቀውን የጥንዶች ሥነ-ልቦናዊ የእርዳታ ዘዴ (Gottman Method Couples Therapy) ፈልሳፊዎችና የጎትማን ኢንስቲትዩት መሥራቾች ናቸው ።
በጎትማን ኢንስቲትዩት ለበርካታ አሥርተ-ዓመታት በጥንዶች ላይ ባደረጓቸው ጥናቶች መሠረት አራት ዋና የግንኙነት ዕንቅፋቶች እንዳሉ ለመረዳት ችለዋል። የእነዚህ መሰናክሎች በተደጋጋሚ መከሰት ደግሞ የትዳርን መፍረስ ወይም የግንኙነትን አለመሳካት ለመተንበይ እንደሚያስችል በመረጃዎች የተደገፉ ጽሑፎቻቸው ያስረዳሉ።
በእነዚህ ጥናቶች ላይ በመመርኮዝ እነ ጎትማን ስለ አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶችና መፍትሔዎቻቸው ያበረከቱትን ቀጥለን እንመለከታለን።
ነቃፊ ትችት
የሰውን ባህርይና ማንነት በመንቀፍ መተቸት ወይም መዝለፍ
በጎ አመለካከትን ያዘለ ትችት (complaint - ኮምፕሌይንት) በመሠረቱ ክፋት የለውም። አክብሮትን ያስቀደመና በጥንዶች መሀከል አለመግባባትን ባስከተለው ጉዳይ ላይ ያተኮረ ትችት መፍትሔን ለማስግኘት የሚደረግ ጥረት እንደመሆኑ መጠን አዎንታዊ ሂደት ነው።
በአንጻሩ ጥንዶች ግጭቶች ሲያጋጥሟቸው አንዳቸው የሌላኛቸውን ባህርይና ማንነት በማንቋሸሽ ሆን ብለው ለጥቃት የሚሰነዝሯቸው ነቃፊ ትችቶች (criticism - ክሪቲሲዝም) ግን የሁለቱን ሰዎች ግንኙነት በማሻከር በመሀከላቸው መራራቅን ሊያስከትሉ ይችላሉ ።
ለምሳሌ፦ "አንተ ስለሌላ ሰው ስሜት ጭራሽ ግድ የለህም፣ ሁሌ እራስህን ማስቀደምና ስለእራስህ ብቻ ማሰብ ልማድህ ነው - ሴልፊሽ (selfish) ነህ! እኔ ምን ሊሰማኝ እንደሚችል ፈጽሞ አታስብም!"
ይህ አባባል የተሰነዘረበት ሰው የተጠቃ ሆኖ ሊሰማው ይችላል። የተጠቃን ሲመስለን ሰዎች በተፈጥሯችን እራሳችንን መከላከልን እናስቀድማለን። ስለሆነም አንዳቸው ለሌላኛቸው የመልስ-ምት ሲሰጡና አንድ-ሁለት ሲባባሉ ሁኔታው ተባብሶ ወደ ጠብ ሊያመሩ ይችላሉ።
የሰውን ማንነትና ባህርይ በመንቀፍ መተቸት በጥንዶች ግንኙነት ወይም በትዳር ውስጥ እየተለመደ በመጣ ቁጥር ተተቺውን ቅር በማሰኘት በቀልን ያበረታታል ። አንተ-አንቺ እየተባባሉ መነቃቀፍ በትንሽ-በትልቁ መጋጨትንና ምሬትን ይባስ ብሎርም መናናቅን ሊያስከትል ይችላል።
ንቀት
ማንነቴና የእኔ አመለካከት የተሻለ ነው የሚል የበላይነት አቋም ማሳየት
ንቀት (contempt - ኮንቴምት) የሌናን ሰው ማንነት ዝቅ አድርገን እንድንመለከትና አሽሙርን፣ ፌዝንና በሰው ማላገጥን እንዲሁም ስድብን፣ ግልምጫንና ፊት መንሳትን የመሳሰሉትን አሉታዊ ባህርያት እንድናሳይ ሊያደርገን ይችላል።
የሚያድጉ ልጆች ወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው እነርሱንም ይሁን ሌላን ሰው በንቀት ሲመለከቱና አዘውትረው ሲተቹ ካዩ፣ እንዲሁም አሳዳጊዎቻቸው በየአጋጣሜ የሚዋሹ ወይም ቃላቸውን የሚያጥፉ ከሆኑና ልጆች ያንን እያዩ ካደጉ እነርሱ እራሳቸው የንቀት ባህርይ ሊያሳዩ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ።
የንቀት ባህርይ አሉታዊ አመለካከቶቻችን እንዲጠናከሩ ከማድረጉ ባሻገር ለትዳር ወይም ለግንኙነት መፍረስ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የጎትማን ኢንስቲትዩት ጥናቶች ያሳያሉ። ስለሆነም ፈጽሞ ሊወገድ የሚገባ ባህርይ መሆኑን አጥብቀው ያሳስባሉ።
አዘውትረው የመናናቅ ባህርይ የሚያሳዩ ጥንዶች የሰውነት የመከላከያ ኃይላቸው ዝቅ ሊል እንደሚችል በዚያም ሳብያ እንደጉንፋን ያሉ ተላላፊ ሕመሞች ሊያጠቋቸው እንደሚችሉ የሚያስረዳውን ጽሁፍ ከዚህ በታች ይመልከቱ።
መቃወምና ተበዳዩን መልሶ መኮነን
በእንግሊዝኛ defensiveness (ዲፌንሲቭነስ) ለሚለው ቃል ቀጥተኛ የአማርኛ ትርጉም ባይገኝለትም ጥፋተኝነትን አለመቀበል፣ የሌላን ሰው የመከፋት ወይም የመጎዳት ስሜት በማንቋሸሽና በመቃወም ተበዳዩን ጥፋተኛ አድርጎ የመኮነን ባህርያትን ያካትታል።
ለምሳሌ፦ " አሁን ይሄ የሚያስከፋ ነገር ሆኖ ነው? ለምን ታጋንኛለሽ? በትልቅ በትንሹ ዝም ብለሽ መቆጣት ትወጃለሽ። ደግሞ አንቺ መጀመሪያ እንዲያ ባትዪ ኖር እኔም ያልኩትን አልልም ነበረ!"
ሰዎች ተጎዳሁ፣ ቅር ብሎኛል፣ አልተደሰትኩም፣ አስከፍቶኛል በማለት ስሜታቸውን ሲገልጹልን ለቅሬታቸው መሠረቱ ምን እንደሆነ ለመረዳት ከመጣር ይልቅ ፈጥነን በመቃወም መልስ መስጠት፣ ቅሬታቸው ለተፈጠረው ሁኔታ መጣኝ እንዳልሆነ እየገለጽን ስሜታቸውን ማጣጣል፣ በተጨማሪም ተበደልኩ ባዩን ጥፋተኛ ለማድረግ ምክንያቶችን መደርደር ዲፌንሲቭነስን ያንጸባርቃል። የዲፌንሲቭነስ አቋም ሁኔታዎችን በማባባስ የከረረ ጥል ሊያከትል ይችላል።
ኩርፍያ
ኩርፍያ (stonewalling - ስቶውንዎሊንግ) ብዙውን ጌዜ ከፍ ብለው የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ተከትሎ የሚከሰት አጉል ዓመል ነው። አለመግባባቶች ሲኖሩ፣ የተተቹ ሲመስላቸው ወይም ቅሬታ ሲሰማቸው ስሜታቸውን ገልጸው በተፈጠረው ጉዳይ ላይ ተነጋግረው መፍትሔን የመሻት ልምድና ብቃት የሌላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ኩርፍያ ይቀናቸዋል። ሲያናግሯቸው ፊት በመንሳትና መልስ በመንፈግ፣ ቅር የተሰኙበትን ሰው በማግለል፣ ሥራ ወጥሮ የያዛቸው ወይም አስቸኳይ ጉዳይ እንዳለ በማስመሰል አብሮ መሆንን በመሸሽ ኩርፍያ ሊገለጽ ይችላል።
የኩርፍያ አጉል ዓመል በፍጥነት ሥር የመስደድ ባህርይ ስላለው በቀላሉ ለመግታት ሊያዳግት ይችላል።በተጨማሪም በኩርፍያ ስሜት ውስጥ ስንሆን በአሉታዊ ስሜቶች ስለምንዋጥ (overwhelm) በመወያየት ችግሮችን የመፍታት ብቃትና ችሎታ አይኖረንም።
መፍትሔዎች
አለመግባባቶች በሚከሰቱበት ጊዜ ከአራቱ የግንኙነት ዕንቅፋቶች መሀል አንዱ መኖሩን ካስተዋልን የሚከተሉትን እርምጃዎች ብንወስድ ይጠቅማል፦
ነቀፌታን ያዘለ የመተችት ባህልን መተው
(criticism)
ማንነትን ወይም ባህርይን ከማጥቃት በመቆጠብ አለመግባባትን ላስከተለው ሁኔታ ወይም ጉዳይ ትኩረት መስጠት፦
- ምንድን ነው የተከሰተው?
- የተበዳዩን ቅሬታና ስሜት በትጋት ለማዳመጥ የሚያስችል በቂ ትዕግስት አሁን አለኝ ይሆን? ከሌለኝ ደግሞ እራሴን ለመንከባከብ ምን ባደርግ ይሻላል?
- እኔስ ስለሆነው ነገር ምንድን ነው የተሰማኝ?
- ለዚህ ሁኔታ የእኔ ኃላፊነት ምን ይሆን?
- እንዲሆን የምፈልገው ውጤትስ ምን ይመስላል?
ስለተፈጠረው ሁኔታ የተሰማንን ስሜት እና ፍላጎታችንን በትኅትናና በግልጽ መናገር።
ለምሳሌ፦ "የሚያስመሸን ነገር በድንገት ሲፈጠር አንዳችን ለሌላኛችን እንድናሳውቅ ተስማምተን ነበረ። ሳትነግረኝ ስታመሽ ሀሳብ ገባኝና ምን ደርሶብህ ይሆን ብዬ ስለተጨናቅሁ ነው እኮ! እንዳልጨነቅ አስቀመህ እንድትነግረኝ እፈልጋለሁ።"
ንቀትን መቅረፍ
(contempt)
መልካምና አዎንታዊ ስሜቶችን አዘውትሮ የመግለጽን ባህል በማዳበር የንቀትን ስሜት መቅረፍ ይቻላል።
ጥንዶች በየአጋጣሚው አንዳቸው ስለሌላኛቸው የሚሰማቸውን እንደ ፍቅር፣ አክብሮት፣ አድናቆትና፣ ውለታ ያሉ አዎንታዊ ስሜቶችን መግለጽ ቢያዘወትሩ ግንኙነታቸው የበለጠ የተጠናከረ ይሆናል - ይላሉ እነጎትማን። ይህ የግንኙነት ጥንካሬ ደግሞ በጥንዶች መሀል ግጭት በሚፈጠርበት ወቅት በተሻለ ሁኔታ አብረው መፍትሔ በመፈለግ ችግሩን ለመፍታት ያስችላቸዋል ይላሉ።
የስሜታዊ ባንክ ሚዛን - እንደ እነጎትማን አገላለጽ
አምስት እጅ ለአንድ እጅ (5፡1) - አምስት በጎ አመለካከቶች በጥንዶች ስሜታዊ ባንክ ውስጥ ሲጠራቀሙ አንድን ግጭት በቀላሉ ለመወጣት ያስችላቸዋል።
ተቃውሞን ባዘለ መልኩ ተበዳይን መልሶ መኮነንን ማስወገድ
(defensiveness)
- ተበድያለሁ ባዩ የሚሉንን ልባችንን ክፍት አድርገን በማዳመጥ የተሰማቸው ስሜት ምን እንደሆነ ለመረዳት መጣር
- ተበዳዩ የተሰማቸውን ስሜት መቀበል (validation - ቫሊዴሽን)
[በተበዳዩ አቋም ተስማምተናል ማለት ሳይሆን ተበዳዩ የተሰማቸው ስሜት ዕውነተኛ ስሜታቸው እንደሆነ አምነን ተቀብለናል ማለት ነው]
- ለግጭቱ መከሰት እኛ የተጫወትነው ሚና ቢኖር ኃላፊነት ወስደን ይቅርታ መጠየቅ
ለምሳሌ፦ "የምትዪውን በጥሞና ሳዳምጥ ለምን ቅር እንዳለሽ ለመረዳት ቻልኩ። እኔም ባንቺ ቦታ ብሆን ይከፋኝ ነበር። አነጋገሬ/ተግባሬ በእርግጥ ተገቢ አልነበረምና ይቅርታ!"
በኩርፍያ ፈንታ ስሜትን ማረጋጋት
ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው በኩርፍያ ጊዜ በአሉታዊ ስሜቶች ስለምንዋጥ (overwhelm) በውይይት ችግሮችን የመፍታት ብቃትና ችሎታ አይኖረንም።
ለዚያ ምክንያቱ ግጭቶችን ሰውነታችን እንደጥቃት አርድጎ ስለሚወስድና የልብ ትርታችን እንዲጨምር ስለሚያደርግ፣ ተያይዞም የጭንቀትና የውጥረት ዕድገንጥሮች (hormones - ሆርሞኖች) መጠን ደማችን ውስጥ ከፍ ስለሚል ጥቃቱን እንድንጋፈጥ ወይም እንድንሸሽ የሚገፋፋ ስሜት ያድርብናል (fight or flight response - ፋይት ኦር ፍላይት ሪስፖንስ)።
እነ ጎትማን በግጭት ሳብያ ጥንዶች ክርክር ላይ እያሉ በፊልም ሲቀርጿቸው ቆይተው በድንገት የመቅረጫ መሣሪያችን ስለተበላሸ አንዳፍታ እስኪሠራ ድረስ ክርክራችሁን አቋርጡ፣ ከተሠራ በኋላ ትቀጥላላችሁ በማለት ክርክራቸውን ካስቆሟቸው በኋላ እስከዚያው የሚያነቧቸውን መጽሔቶች ሰጧቸው። ከግማሽ ሰዓት በኋላ ጥንዶቹ ክርክራቸውን እንዲቀጥሉ ሲጋብዟቸው ቀደም ብሎ እንደነበረው በቁጣና በንዴት ሳይሆን በተረጋጋና አክብሮት በተመላበት መንፈስ እየተደማመጡ መነጋገር መቻላቸውን አስተዋሉ። የልብ ትርታቸውም እንደዚያው ቀደም ሲል ከነበረው መጠኑን ቀንሶ አገኙት። ለኩርፍያ መፍትሔው እራስን ማረጋጋት እንደሆነም ሊገመግሙ ቻሉ።
መደምደሚያ
በመከባበርና በመዋደድ ላይ የተመሠረተ መቀራረብ ለጥንዶች ግንኙነት ስኬታማነት መሠረትነቱ ግልጽ ቢሆንም በማንኛውም ዓይነት የቅርብ ግንኙነት ውስጥ - ስኬታማ ናቸው የምንላቸውንም ጨምሮ - አለመግባባቶችና ግጭቶች መፈጠራቸው የማይቀር ነገር ነው። ስለሆነም አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች ማንኛውንም ሰው ሊፈትኑ የሚችሉ ሁኔታዎች እንደሆኑ ማስታወስ ያስፈልጋል።
አለመግባባቶች ሲከሰቱ እርስ-በእርስ በመጠነቋቆል ሌላኛውን ሰው ጥፋተኛ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ወደእራሳችን በመመልከት ጥፋት ከኖረን ማመንና ይቅርታ መጠየቅ መቻላችን የእያንዳንዳችንን ስሜታዊ ልህቀትና የብስለት ደረጃን (emotional intelligence - ኢሞሽናል ኢንቴሊጀንስ) ያሳያል።
ጤናማ በሆነ መልኩ ስለ ግጭቶች መወያየትና መፍትሔን አብሮ መፈለግ ለጥንዶች ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ዓይነት ግንኙነት እጅጉን አስፈላጊና ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ችሎታ ቢሆንም ለግጭቶች ሁሉ መፍትሔ ይገኝላቸዋል ማለትም እንዳልሆነ በማስተዋል ይቅር እንተወው በመባባል ነገሮችን ማለፍ መቻልም ዐዋቂነት ነው።
ግጭቶች ከርረው መግባባት በሚያዳግትበት ወቅት ጥንዶች ክርክራቸውን መቀጠላቸው - ውኃን ቢወቅጡት እንቦጭ እንዲሉ - ፋይዳ አይኖረውም። ለየብቻቸው ከ20-30 ደቂቃዎች ዕረፍት አድርገው መንፈሳቸው ከተረጋጋ በኋላ ተመልሰው ግጭታቸውን ለመፍታት ቢስማሙ የተሻለ የሆናል ።
ለጥንዶችና ለሌሎች ግንኙነቶች መሳካት ከመራራቅና ጀርባን ከመሰጣጣት ይልቅ እራስን ማረጋጋት መልመድና መቀራረብን መሻት አጥብቆ ይመከራል። በመተባበርና አክብሮትን በተጎናጸፈ መንፈስ ግጭቶችን በውይይት መፍታትና ተስማሚ ውሳኔ ላይ አብሮ መድረስ መቻል ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ እሤት ነው።
References:
