ኦቲዝምና የቤተሰብ ተሞክሮ - ኦቲዝም ምዕራፍ ፫
ኦቲዝም የዕድሜ-ልክ ሁኔታ እንደሆነና መልኩ ወይም አገላለጹ ከሰው ሰው ሊለያይ እንደሚችል በምዕራፍ አንድ እና ሁለት ለማየት ችለናል። በዝርዝር ከተመለከትናቸው ዋና ዋና ነጥቦች መሀከል ጥቂቶቹን ለማስታወስ፦
- ኦቲዝም መሠረቱ የነርቮች ድር የአወጣጣር ልዩነት ሲሆን የአዕምሮ ብስለት ዝግመትን አለዚያም ደግሞ ረቂቅ የሆነ ተሰጥዖንና ልዩ ችሎታዎችንም ሊያካትት ይችላል።
- ኦቲዝም ሥውር ሆኖ ሳይታወቅ ሊቀር ወይም ደግሞ ዘግይቶ በዓዋቂ ዕድሜ ሊገኝ ይችላል።
- ኦቲዝም የሌላቸውን ሰዎች ለመምሰልና በአነጋገራቸው እንዲሁም በሁኔታቸው ከእነርሱ ለየት ብለው ላለመታየት ሲሉ ኦቲስቲክ ሰዎች (ልጆችና ዓዋቂቆች) ከተፈጥሯቸው ውጪ እራሳቸውን በማስገደዳቸው የስሜቶች (የጸባይ) መለዋወጥንና የዐቅም መሟጠጥ ምልክቶችን (ኦቲስቲክ በርናውትን - autistic burnout) ሊያስከትልባቸው ይችላል።
ኦቲዝምና የወላጆች ተሞክሮ
ምልክቶቹን አስተውለው ቀደም ሲል ጥርጣሬ የነበራቸው ቢሆንም - በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው ኦቲዝም እንዳላቸው በባለሞያዎች ሲረጋገጥና ሲነገራቸው ሁኔታውን ለመቀበል ሊያዳግታቸው ይችላል። ስለሆነም ስሜታቸውን በተለያየ መንገድ ሊገልጹና ሊያንጸባርቁ ይችላሉ። ለምሳሌ፦
ማስተባበል፣ መካድ፣ ዕውነታን አለመቀበል - የልጃቸው ኦቲዝም ዱብዕዳ ከሆኖባቸው ዕውነትነቱን ለመቀበል ተስኗቸው "ሊሆን አይችልም" ብለው ማስተባበል
ግራ የመጋባት፣ የጭንቀትና የውጥረት ስሜት - የተለያዩ አስተያየቶችንና ምክሮችን ሰዎች ሲለግሷቸው ወይም በሳይንስ ላልተደገፉ ጽሁፎችና ቪዲዮዎች በሚጋለጡበት ጊዜ የቱን ይዘው የትኛውን እንደሚተዉ ግራ ሊገባቸውና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የመንፈስ ጭንቀትና ውጥረት (ክሮኒክ ሳይኮሎጂካል ስትሬስ - chronic psychological stress) ሊያድርባቸው ይችላል።
የንዴት ስሜት - "ለምን እኔ? ለምን የእኔ ልጅ?" የሚል ጥያቄ ንዴትና ብስጭት ሊያስከትልባቸውና የቁጡነት ባህርይ ሊታይባቸው ይችላል።
የጥፋተኝነትና የቁጭት ስሜት- ምንም እንኳን ለኦቲዝም መከሰት መሠረቱ ምን እንደሆነ በሳይንስ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም ልጃቸው ኦቲስቲክ ለመሆኑ/ኗ የተለያዩ ሁኔታዎችንና አጋጣሚዎችን ምክንያት እንደሆኑ አድርገው ሊቀበሉ ይችላሉ። ለምሳሌ፦
- ከዘር ወደዘር ወደልጆቻችን ኦቲዝምን አስተላልፈን ይሆናል በማለት
- ከአመጋገባችን ወይም ከዋጥነው መድሐኒት አለዚያም የምነተነፍሰው አየር በመበከሉ የተከሰተ ነው ብለው በመጠርጠር
- ልጆቻችን በሕፃንነታቸው እንዲከተቡ ስለፈቀድን ነው ብለው እራሳቸውን ጥፋተኛ በማድረግ
- በጊዜ ልጃችንን ለሐኪም ሳናሳይ በመቅረታችን እና ሁኔታው ዘግይቶ በመታወቁ ለልጃችን በወቅቱ እርዳታ ሳናገኝ ቀረን (እርዳታ ለማግኘት ዘገየን) ብለው በመቆጨት
ተስፋ የማጣት ወይም የባዶነት ስሜት - ኦቲስቲክ ልጃቸው እንደማንኛውም ልጅ አድጎ/አድጋ ወደፊት የተሟላ የሕይወት ተለምዶ የማግኘት ወይም ቤተሰብ የመመሥረት ዕድል እንደማይኖረው/እንደማይኖራት አድርገው ገምተው የወላጆች ተስፋ ሊመነምንና ሊጨልም፣ ብሎም ሊደበቱ ይችላሉ።
የእፎይታ ስሜት (relief - ሪሊፍ) - የልጃቸው ሁኔታ ግራ ገብቷቸው ቆይተው ኦቲዝም መሆኑ ሲነገራቸው አንዳንድ ወላጆች ለልጃቸው የሕክምና እና ሌሎች ተጨማሪ እርዳታዎችን ለልጃቸው ለማግኘት እንዲሞክሩ መንገድ ስለሚከፍትላቸው ወይም ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ተረድተው መፍትሔ መፈለግ በመቻላቸው የእፎይታ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል።
ዑደታዊ የኀዘን ስሜት
ኦቲዝምን አስከትሎ የሚመጣ የወላጆች ኀዘን ለየት ያለና ረጅም ጊዜ የሚቆይ ነው። ልጃቸው ኦቲስቲክ እንደሆነ/ች ከተረጋገጠባት ደቂቃ አንስቶ በልጆቹ የዕድገት ዘመናት እና በዓዋቂነት ዕድሜያቸውም ጭምር በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎችና አጋጣሚዎች ኀዘኑ በተደጋጋሚ መልሶ መላልሶ ሊያገረሽ ይችላል። ለምሳሌ፦
- ኦቲስቲክ ልጆቻቸው ሲታመሙ ወይም አንዳንድ ምክንያቶች ሲያስሸበሯቸውና ሲያውኳቸው ወላጆች ልጆቹን ለማረጋጋት የሚያደርጓቸው ጥረቶች ሁሉ ሳይሳኩ በቀሩ ቁጥር
- ኦቲዝም-አልባ (non-autistic) እኩዮቻቸው በዕድሜያቸው መጠን ዕድገቶችንና የሕይወት ደረጃ ለውጦችን ባሳዩ ቁጥር (በትምህርት ደረጃ ፣ በቋንቋ ችሎታ፣ የፍቅርና የትዳር ጓደኛ የመያዝና ሌሎች ልዩነቶችን አስመልክቶ)
- ኦቲስቲክ ልጃቸው የዕድሜ-ልክ ድጋፍና እንክብካቤ የሚያስፈልጋት/ገው ከሆነ የወላጅነት ኀላፊነታቸው እንዲሁ የዕድሜ-ልክ እንደሚሆን ተረድተው፣ የእራሳቸውና የልጃቸው ዕጣ አሳዝኗቸውና የወደፊት ሕይወታቸው አሳስቧቸው
- ኦቲስቲክ ልጆቻቸውን ሌሎች ልጆችና ወላጆች ሲያገልሏቸው እንዲሁም ጥቃቅን ልዩነታቸውን በማጉላት ሲተቹና በትዝብት ሲመለከቷቸው ባስተዋሉ ቁጥር
- የኦቲዝም ባህርዮች አንዳንድ ቦታዎች ወይም ዘመድ ቤት ከመሄድ የሚያግዷቸው ሲሆን
- የኦቲስቲክ ልጆቻቸውን መብትና እንክብካቤ አስመልክቶ በወላጆች መሀከል የጎላ ልዩነት ሲኖርና በቤተሰብ አባላት መሀከል አለመግባባቶችና ግጭቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ
- የሚኖሩበት ሕብረተሰብ ወይም ማኅበረሰብ ስለኦቲዝም ያለው ዕውቀትና የንቃተ-ሕሊና ደረጃ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሚፈጠሩ ሁኔታዎችንንና አጉል አባባሎችን አስታኮ
- ሰዎች ሲያፈጡባቸው ምክንያቱ የኦቲስቲክ ልጆቻቸው ሁኔታ ሲመስላቸውና በየአጋጣሚው የይሉኝታ ስሜት ሲያጠቃቸው
- ጧሪ ልጅ ወይም የልጅልጅ የማየት ዕድል እንደማይኖራቸው ሆኖ ተሰምቷቸው
- የኦቲስቲክ ልጃቸውን የዕለት-ተዕለት ኑሮ ለማሻሻል ወላጆች የጊዜ፣ የጉልበትና፣ የገንዘብ መስዋዕትነቶችን ለመክፈል ሁኔታዎቹ ስላስገደዷቸው
- ወላጆች የጤና ቀውስ ሲያጋጥማቸው ወይም ዕድሜያቸው ሲገፋ ኦቲስቲክ ልጃቸውን መንከባከብ እያዳገታቸው መምጣቱን ተገንዝበውና ይህ ሁኔታ አሳስቧቸው
- ወላጆች "አርጅተን አቅም ሲያጥረን ወይም ደግሞ ስንሞት ልጃችንን ማን እንደኛ ይንከባከብልናል" የሚል ስጋት አድሮባቸው
ኦቲዝምና ቤተሰባዊ ግንኙነቶች
ሀ/ የወላጆች ግንኙነት
ወንዶችና ሴቶች በተፈጥሯቸውም ይሁን ከአስተዳደጋቸው የተነሳ ለችግሮች ያላቸው አመለካከትና የሚወጡባቸው መንገዶች የተለያዩ ናቸው።
ሴቶች በአብዛኛው ስሜታቸውን በማዳመጥና የተሰማቸውን በመግለጽ የተሻለ ስሜት እንዲሰማቸው የሚያስሏቸውን ሁኔታዎችና ተግባራት ሲመርጡ (emotion-focused = ኢሞሽን ፎከስድ ) የብዙዎች ወንዶች ትኩረት ደግሞ ችግሮችን በመረዳት መፍትሔዎችን መፈለግ ላይ ይሆናል (problem-focused = ፕሮብለም ፎከስድ)። እነዚህ ልዩነቶች ኦቲስቲክ ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ለሚያጋጥሟቸው አዳጋች ሁኔታዎች ወላጆች አብረው መፍትሔ ለማግኘት እንዲሳናቸው በማድረግ በመሀከላቸውም አለመግባባቶችና ግጭቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናሉ።
በወላጆች መሀከል የሚኖሩ የአመለካከት ልይነቶች ከኦቲስቲክ ልጃቸው ጋር በሚኖራቸው ቅርበት ላይም ተጽእኖ ያሳድራሉ። አብዛኛውን ጊዜ አባቶች ልጃቸው ኦቲስቲክ መሆኗን/መሆኑን እንዲሁም የሕይወታቸው አቅጣጫ ኦቲዝም ከሌላቸው ልጆች በብዙ መልኩ ለየት ሊል እንደሚችል ለመቀበል ያዳግታቸዋል። በተጨማሪም በኦቲዝም ምክንያት የወደፊት ተስፋቸውን እንደ ተነፈጉ ሆኖ ተሰምቷቸው ንዴት ይታይባቸዋል፣ ኦቲስቲክ ልጃቸውንም ያርቃሉ ወይም ግንኙነታቸው ውሱን ይሆናል። ስለሆነም በርካታ አባቶች "እኔ አላውቅበትም፣ አንቺን ብቻ ነው ልጃችን የሚሰማው/የምትሰማው..."- በሚል ሽፋን ኀላፊነቶችን ይሸሻሉ።
ኦቲስቲክ ልጆችን ለመንከባከብ ተገቢው የአባቶች ድጋፍና እርዳታ ካልኖረ በእናቶች ላይ የገነነ ሥነ-ልቦናዊ ጫና ያሳድራል። ስለዚህም በርካታ እናቶች የተሰማሩበትን የሥራ መስክ ለቅቀው ሙሉ ጊዜያቸውን ለኦቲስቲክ ልጃቸው እንክብካቤ እንዲያውሉ ይገደዳሉ። ይህ ሁኔታ እናቶች በአባቶች ላይ ቅሬታ እንዲኖራቸው ከማድረጉም በላይ በመሀከላቸው ተደጋጋሚ ግጭቶች እንዲፈጠሩ ወይም አለመግባባቶች እንዲገንኑ መንገድ ይከፍታል። ወላጆች ለችግሮቹ በወቅቱ መፍትሔዎችን ማግኘት ከተሳናቸው ደግሞ ሁኔታዎች ተባብሰው ወደ መለያየትና መፋታት ደረጃ ሊያደርሳቸው ይችላል።
መፍትሔዎች
የኦቲዝም ሁኔታን በተመለከተ፦
- ኦቲዝም የነርቮች ድር አወጣጠር ልዩነት እንጂ የበሽታ ምልክት እንዳልሆነ መገንዘና ማስታወስ
- በኦቲዝም ዙሪያ ሊከሰቱ የሚችሉ ሁኔታዎች ላይ በማተኮር መፍትሔዎችን ተባብሮ መፈለግ
- ዕቅዶችን በመተጋገዝ ማውጣትና በተግባር ላይ ማዋል
- ስለኦቲዝም ባህርዮችና አገላለጻቸው መረጃዎችን ፈልጎ በማግኘት የግል ዕውቀትንና በእራስ መተማመንን (confidence) መገንባት
- ኦቲስቲክ ልጆችን በማስተማርና በማለማመድ እራሳቸውን ለመርዳት የሚያስችሉ ብልሃቶችን እንዲያዳብሩ ማገዝ
- የድጋፍ ሰጪ አካላትን እርዳታ መጠየቅና ለኦቲስቲክ ልጆች መብቶች መቆም
- ኦቲዝምን አስታከው የሚከሰቱ ሁኔታዎን ለመቋቋም ልጆቹ ለሚያሳይዋቸው እድገቶችና ለውጦች ትኩረት መስጠት
ወላጆችን በተመለከተ፦
- የመጀመሪያው እርምጃ ልጆቻችን ኦቲዝም እንዳላቸው ሲነገረን ማመንና መቀበል ነው
- ስሜቶቻችንን (ኀዘን፣ ንዴት፣ ወዘተ) ጤናማ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ ጥረት ማድረጋቸን የመንፈስ ሰላምን እንድናገኝ እንደሚረዳን መገንዘብ
- አቅማችን በሚፈቅድልን መጠን ለልጆቻችን የምናደርገው ድጋፍ በቂ እንደሆነ ተረድተን ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ሲፈጠር ለእራሳችን ይቅርታ ማድረግን መልመድ
- "ለይሉኝታ" እና "ከእናንተ በላይ እኛ እናውቃለን-ባይ ተቺዎች" ቦታ አለመስጠት
- በምርመራ የተረጋገጠን ኦቲዝም ዕውነተኛነት አለመቀበል፣ እራሳችንን በትንሽ በትልቁ ጥፋተኛ ማድረግና በዕድላችን መማረር እራሳችንን ብቻ ሳይሆን ልጆቻችንንም (ኦቲስቲክ የሆኑትንም ይሁን ያልሆኑትን) ሊጎዳ እንደሚችል መገንዘብ
- ኀዘንን ለመቋቋም ለእራሳችን ጊዜንና እንክብካቤን መስጠታችን አስፈላጊ እንደሆነ በማስታወስ የዘመድንና የጓደኞችን እርዳታ እንደአስፈላጊነቱ መጠየቅ
- ኦቲስቲክ ልጆች ካሏቸው ሌሎች ወላጆች ጋር እየተገናኘን ልምዶችን መለዋወጥና እርስ-በእርስ መደጋገፍ
- "ልጆቹ ምን ዕድገት አሳዩ? እኛስ ወላጆች የእርስ-በእርስ ግንኙነታችንን እና ኦቲዝምን በተመለከተ ምን ሁኔታና የዕውቀት ደረጃ ላይ እንገኛለን?" ብለን እራሳችንን በመጠየቅ ለአዎንታዊ ለውጦቻችንና ዕድገቶቻችን ትኩረት ሰጥጠን እራሳችንን ማበረታታት
- ለጭንቀት፣ ለድባቴ፣ እንዲሁም ለተስፋ የመቁረጥ ስሜቶች ወዘተ ለእራሳችን እንክብካቤ ማድረግ እንዲሁም የአስተውሎት (mindfulness) ልምዶችን ማዳበር
- የሥነ-ልቦና ባለሞያን ወይም የሐኪምን እርዳታ መጠየቃችን ውስጣዊ ጥንካሬያችንን (courage) የሚያሳይ እንጂ የደካማነት ምልክት እንዳልሆነ ማስተዋል
ለ/ የኦቲስቲክ ልጆች እኅትና ወንድሞች
ኦትስቲክ እኅትና ወንድም ያላቸው ልጆች ምንም እንኳን ኦቲዝም ላለበት ወንድማቸው (ላለባት እኅታቸው) ፍቅር ቢኖራቸውም መግባባት ሊሳናቸው፣ ግራ ሊጋቡና እርስ-በርሳቸው ሊጋጩ ይችላሉ። ለኦቲስቲክ ወንድማቸው/ እኅታቸው ወላጆቻቸው የበለጠ ትኩረትና እንክብካቤ እንደሚሰጡ ሆኖ ከተሰማቸው ደግሞ በቅናት የቁጡነት ጸባይና ነጭናጫነት ሊታይባቸው ይችላል። የጸባያቸው መለዋወጥ ደግሞ ለአገባጣሪ ጥቃት (bullying) እንዲሁም ለጭንቀትና ድባቴ (anxiety and depression) ያጋልጣቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከወላጆቻቸው ጎን ለኦቲስቲክ ወንድማቸውና እኅታቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች እርዳታና ድጋፍ እየሰጡ፣ ከጉዳትና ከጥቃት እየተከላከሉላቸው አብረው ያደጉ ልጆች ለተጎዱ የሚያዝኑ፣ ትዕግስተኞች፣ ለሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ዜጎች ሆነው ያድጋሉ። ወላጆቻቸው በእርጅናም ይሁም በሕመም ሳብያ ኦቲስቲክ ልጃቸውን መንከባከብ በሚሳናቸው ጊዜም ወላጆቻቸውን ተክተው የኦቲስቲክ ወንድምና እኅታቸውን ኀላፊነት የሚረከቡ ይሆናሉ።
ለወላጆች ምክር፦
- ወላጆች ለልጆቻቸው (እንደ ብስለታቸው ደረጃ) ስለ ኦቲዝም ቢያስረዷቸው የኦቲስቲክ እኅታቸው ወይም ወንድማቸው ሁኔታ እንዲገባቸው በማድረግ ግራ መጋባትንና ጭንቀት ይቀንስላቸዋል።
- ወላጆች በተቻላቸው መጠን ኦቲስቲክ ላልሆኑት ልጆቻቸው በየግላቸው በቂ ጊዜና ትኩረት ሊሰጡ ይገባል።
- ወላጆች የእህትና ወንድሞች ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችን ዕርዳታ በመጠየቅ ኦቲስቲክ ያልሆኑት ልጆቻቸው የሥነ-ልቦና ባለሞያ ድጋፍ እንዲያገኙና ከሌሎች ኦቲስቲክ እኅትና ወንድም ካሏቸው ልጆች ጋር በየጊዜው እየተገናኙ ተሞክሯቸውን ማካፈል የሚችሉበት የግላቸው መድረክ እንዲያገኙ የማድረግ ኀላፊነት አለባቸው።
መረጃዎች፦












