የመግደርደር ባህል ልጆችንና ሴቶችን ለጥቃት ያጋልጣል
በቀላሉ ወይም ወዲያው "እሺ!" ወይም "አዎን!" በማለት ፍላጎትን መግለጽ እንደነውር ተቆጥሮ እየፈለጉ "አልፈልግም!" እያሉ በመግደረደር እንዲለመኑ መንገድ መክፈት በአንዳንድ የሕብረተስብ ክፍሎች ውስጥ አክብሮትን፣ ትሕትናንና ጨዋነትን የሚያመለክት ባህል ነው። መግደርደርን እንደ ባህል ለማይተገብሩ ሰዎች ግን ግራ የሚያጋባና አንዳንዶችን ደግሞ ለጥቃትና ለጉዳት የሚያጋልጥ ልማድ ነው።
(አስተያየትዎን ለመስማት እንጓጓለን - ሰብስክራይብ በማድረግ ያካፍሉን)
"በሞቴ፣ አፈር ስሆን?"
የምግብን ወይም የመጠጥን ግብዣ ይብቃኝ ይቅርብኝ ካሉ በኋል "እባክዎን፣ በሞቴ፣ አፈር ስሆን..." ሲባሉ ግን ከመቅመስ አልፎ አስጨምሮ መብላት ወይም ብርጭቆ ጎደል ሲል ባናት-ባናቱ እያስሞሉ መጠጣት የመግደርደር ባህል ያስከተላቸው ልማዶች ናቸው።
መግደርደር ሰዎች ፍላጎታቸውን በሚናገሩበት ጊዜ ያሉት ነገር እውነት መሆኑን እንድንጠራጠርና እንደገና እንድንጠይቃቸው ወይም ሀሳባቸውን እንዲለውጡ ግፊት እንድናሳድርባቸው የሚያበረታታ ነው፣ ስለሆነም በተለይ ልጆችንና ሴቶችን ለጉዳት የሚዳርጉ ሁኔታዎች እንዲከሰቱ መንገድ ሊከፍት የሚችል አጉል ባህል ነው።
ተረትና ምሳሌ፦
- "አፌን ቢላዋ ቢቆርጠው፣ ልቤን በለው!"
- "አፏ እምቢ ይላል፣ እጇ ያጎርሳል!"
ልጆች በተፈጥሯቸው ሰዎችን ያምናሉ፣ የማይፈልጉትንም ያውቃሉ።
ሕፃናት ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ እንክብካቤ የሚያደርጉላቸውን እንዲሁም በአካባቢያቸው አዘውትረው የሚያዩአቸውን ሰዎች ያቀርባሉ። የማያውቁትንና ለመጀመሪያ ጊዜ ያዩትን ወይም ባዕድ የሆነን ሰውም ቢሆን እሲኪለምዱ ጊዜ ይፍጅባቸው እንጂ ቤተሰብ ሲቀርብ ካዩ ቀስ-በቀስ ማስጠጋታቸው አይቀርም።
በሌላ በኩል ደግሞ ልጆች በተፈጥሯቸው የማይፈልጉትን ለይተው ስለሚያውቁ በሚቻላቸው መንገድ ሁሉ ያንን ይገልጻሉ። ለምሳሌ የሚጠቡ ሕፃናት ሆዳቸው ሲጠግብ ፊታቸውን ከጡት ወይም ከጡጦ ዞር በማድረግ መጥባት አለመፈለጋቸውን ይገልጻሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ ዕድሜያቸው ከፍ ሲል ደግሞ የጎረሱትን በመትፋት ወይም የምግባቸውን ሰሀን በእጆቻቸው ገፋ በማድረግ እንደበቃቸው ወይም አለመፈለጋቸውን ያሳያሉ። ካስገደዷቸው ደግሞ ይነጫነጫሉ፣ ይቆጣሉ፣ ያለቅሳሉ፣ ከባሰም የበሉትን ያስመልሳሉ።
ሰውን ለመጠጋት ካልፈለጉ እንደዚሁ በድምጻቸውና በሁኔታቸው - ማለትም ፊታቸውን በእጆቻቸው በመሸፈን ወይም የሚወዱት ሰው ጉያ ውስጥ በመሸሸግ፣ ከከፋም ደግሞ በመነጫነጭና በማልቀስ - ይገልጻሉ። ስሜታቸውን በቋንቋ መግለጽ በሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ደግሞ "በቃኝ! አልፈልግም! ተዉኝ! ኖ! እምቢ! ወዘተ" በማለት አለመፈለጋቸውን ያሳውቃሉ።
ልጆች ጎጂ ልማዶችን ከአካባቢያቸው ይቀስማሉ
ዕውነተኛ ስሜታቸውን እንዲገልጹ እየተበረታቱ የሚያድጉ ልጆች የውስጥ ስሜታቸውን የማዳመጥ ችሎታቸው ከጊዜ ጋር እየዳበረ ይመጣል። ስለሆነም የማይመቻቸውንና የማይፈልጉትን ያለማመንታት ይናገራሉ። ሰዎች ከዕውነት የራቀ ነገር ሲናገሩ ከሰሙ እንዲሁም ሰው ሰውን ወይም እንሰሳን ሲበድል ካዩ፣ በአጠቃላይ የሰዎችን የማይገባ ባህርይ ካስተዋሉ የውስጥ ስሜታቸውን በማዳመጥ "አይደለም፣ አይባልም፣ አይሆንም፣ አይደረግም!" ከማለትና ለሰዎችና ለእንሰሳት መብት ከመቆም ወደኋላ አይሉም።
በአንጻሩ ደግሞ ልጆች ዕውነተኛ ስሜታቸውንና አስተያየቶቻቸውን በሚገልጹበት ጊዜ አሳዳጊዎቻቸው ከተናደዱባቸው፣ ከተቆጧቸው ወይም ከቀጧቸው ልጆቹ ስሜታቸውን በግልጽ ከመናገር መቆጠብ ይጀምራሉ። ሆዳቸውን/ልባቸውን ወይም የውስጥ ስሜቶቻቸውን በመከተል ፈንታ በአካባቢያቸው (በቤተሰብ፣ በት/ቤትና በኅብረተሰባቸው ውስጥ) ተቀባይነት ያለውን ነገር ማድረግና ማሳየት ይጀምራሉ። ዕውነተኛውን ስሜታቸውን ከመግለጽ ይልቅ ሳይፈልጉ እሺ ማለትን፣ እየፈለጉ አልፈልግምን እና መግደርደርን ጭምር ከአካባቢያቸው ይማራሉ።
በሌላ አነጋገር - አብሯቸው የተፈጠረውንና ጥሩውን ከመጥፎ በመለየት የሚመራቸውን ወስጣዊ ኮምፓስ ወይም ሆዳቸው/ልባቸው የሚነግራቸውን ከመከተል ይልቅ በአካባቢያቸው ተቀባይነት ያለውን ማንጸባረቅ ይለምዳሉ። ለምሳሌ፦
- ዕውነትን ከመናገር መቆጠብን ብሎም መዋሸትን
- ማስመሰልንና መግደርደርን
- ሌሎች ልጆች/ሰዎች አለመፈለጋቸውን እየነገሯቸው የማይፈልጉትን እንዲያደርጉ ማደፋፈርንና ማስገደድን፤ ወዘተ
መግደርደርና ማግደርደር ከልጅነታችን ጀምሮ አብሮን ካደገ እራሳችንን ለጉዳት የሚያጋልጠን ከመሆኑ ባሻገር የሌሎችንም ሰዎች ስሜታዊ ድንበር (personal boundaries - ፐርሰናል ባውንድሪዝ) እንድንተላለፍና እኛ የምንፈልገውን እንዲያደርጉ በሰዎች ላይ ተጽዕኖ እንድናደርግም መንገድ ይከፍታል።
የመግደርደር ባህል በልጆችና በሴቶች ላይ አደጋ ያስከትላል
ስሜታቸውን ወይም ሀሳባቸውን ሲገልጹ ልጆችን ካላዳመጥናቸው፣ ከዚያም አልፎ ከፍላጎታቸው ውጪ ወይም ልባቸው ሳይፈቅድ ካስገደድናቸው የእራሳቸው አለመፍቀድና አለመሻት ትርጉም እንደሌለው ወይም ቦታ እንደማይሰጠው ሆኖ እንዲሰማቸውና ሀሳባቸውንና ስሜታቸውን ከመግለጽ እንዲቆጠቡ ያደርጋቸዋል። ለምሳሌ፦
- ልጆች በቃኝ እያሉ በግድ ማብላት፣
- ልጆቹ ሳይፈልጉ በይሉኝታ ሰዎች እንዲያቅፏቸው ወይም እንዲስሟቸው ማስገደድ፣
- ዕውነት የሆነን ነገር ሲናገሩ ወላጆቻቸውን የሚያሳፍር ከሆነ ልጆቹ የዋሹ ወይም የተሳሳቱ አስመስሎ ማድበስበስና ልጆቹን መገሠጽና ማሳፈር፣ ወዘተ

አለመፈለጋቸውን በአንደበታቸው፣ በአካላቸው ወይም በሁኔታቸው ሲገልጹ "እየተሽኮረመሙ ነው!" ወይም "እየተግደረደሩ ነው!" በሚል ሽፋን የማይፈልጉትን እንዲያደርጉ ልጆችን ማስገድድ ልባቸው የሚላቸውን ማዳመጥ እንዲተዉ፣ ብሎም ለመብታቸው መቆምን ሳያውቁ እንዲያድጉ በማድረግ ለጉዳት እንዲጋለጡና ክፉ፣ አጉል ወይም መጥፎ/ጠያፍ አስተሳሰብ ባላቸው ሰዎች እንዲጠቁ ሊያደርጋቸው ይችላል።
በተመሳሳይ ሁኔታ "አልፈልግም!" ብለው በግልጽ እየተናገሩ ወይም "እምቢ! ተዉኝ!" እያሉ አለመፈለጋቸውን በሁኔታቸውም ጭምር እያሳወቁ እምቢታቸው እንደመግደርደር ተቆጥሮ ጾታዊ ትንኮሳና ወሲባዊ ጥቃት ወይም መደፈር የሚደርስባቸው ሴቶች ቁጥር እጅጉን በርካታ ነው።

መደምደሚያ፦
ልጆችን ከትንሽነታቸው ጀምረን በነፃነት ፍላጎታቸውንና ሀሳባቸውን እንዲገልጹ ዕድል እየሰጠን ልንገራቸው ይገባል። በተጨማሪም ማንም ይሁን ማን ያለፈቃዳቸው አከላታቸውን ሊነካ እንደማይገባ ልናሳውቃቸው ያስፈልጋል።
የሰውን ስሜት የሚነካ ንግግር ከመናገር እንዲቆጠቡ፣ የእራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ልጆች ስሜት ማዳመጥ እንዲሁም ፍላጎታቸውንና ግላዊ ድንበራቸውን ማክበር እንደሚያስፈልግና እንደሚጠበቅባቸው ልናስተምራቸው ይገባል።
ከልጅነታቸው ለስሜታቸው ትኩረት ተሰጥቶ የሚያድጉ ልጆች ውስጣቸውን የመስማት ልምዳቸውና በእራስ መተማመናቸው እያደገ ይመጣል። መብትና ግዴታቸውን አውቀው እራሳቸውን ከጥቃት የመከላከል ችሎታቸው የዳበረ ይሆናል። የሌሎችንም ሰዎች መብትና ግላዊ ገደቦች (boundaries - ባውንድሪዝ) የሚያከብሩ ይሆናሉ። ስለሆነም ሰው የማይፈልገውን አያደርጉም፣ "እምቢ፣ አይሆንም፣ አይቻልም፣ ወዘተ" ሲባሉ ግፊት አያሳድሩም።
ከላይ የተዘረዘሩትን ምክንያቶች መሠረት በማድረግ የመግደርደር ባህል ጊዜው ያለፈበትና ጥቅም-አልባ ልማድ መሆኑን አስተውለን፣ በተለይም ልጆችንና ሴቶችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ባህል መሆኑን አውቀን ጎጂነቱ ልናጎላና ልናስወግደው ይገባል።





