የቤተሰብ አባላት መጠማመርና መነጣጠል - ክፍል ፪

Share
የቤተሰብ አባላት መጠማመርና መነጣጠል - ክፍል ፪
Credit:RapidEye

የቤተሰብ መነጣጠል (Disconnection - ዲስኮኔክሽን)

በክፍል አንድ የቤተሰብ አባላት በመሀከላቸው በሚኖረው የእርስ በእርስ ጠንካራ መተሳሰር፣ መተባበርና መረዳዳት ላይ ብቻ በማተኮር ለየግል ስሜቶቻቸው ተገቢውን ቦታና ትኩረት ሳይሰጡ በሚቀሩበት ጊዜ፣ እንዲሁም አንዳቸው የሌላኛቸውን ስሜት እንደ የእራሳቸው አድርገው በሚወስዱበት ወቅት መጠማመር ወይም ኢንሜሽመንት ሊከሰት እንደሚችል ለመረዳት ችለናል።

አሁን ደግሞ የመነጣጠልን ባህርይ የሚያንጸባርቁ የቤተሰብ አባላት መሀከል ሊከሰቱ የሚችሉ ሁኔታዎችን እንመለከታለን።

የቤተሰብ መነጣጠል በአባላቱ መሀከል የሚከሰቱ አካላዊና ስሜታዊ መራራቅን እንዲሁም በንግግር አለመግባባትን ያጠቃልላል። ለምሳሌ፦

  • አብረው በአንድ ቤት ውስጥ እየኖሩ እርስ በእርሳቸው አይነጋገሩም
  • በአንድ ቤት ውስጥ እያሉ ሰፊውን ጊዜያቸውን ተነጣጥለው ወይም ለየብቻ ያሳልፋሉ
  • አንዳቸው የሌላኛቸውን ሁኔታ (መከፋት፣ መታመም፣ መጎዳት ወዘተ) ሳያስተውሉ ይቀራሉ
  • በቤተሰብ ውስጥ አስጊ ሁኔታ ወይም ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ መተጋገዝ ያዳግታቸዋል ወይም አብረው መፍትሔ ለማግኘት ይቸገራሉ

የቤተሰብ መነጣጠል በሚያድጉ ልጆች/ወጣቶች እና በአሳዳጊዎቻቸው መሀከል የመራራቅ ስሜት ከመፍጠሩ ሌላ በአሳዳጊዎቻቸው ላይ ቅሬታ (resentment - ሪዜንትመንት) እንዲያድርባቸውና ዕምነት እንዲያጡ ያደርጋል። ተያይዞም ፍላጎቶቻቸውንና ጭንቀታቸውን ከአሳዳጊዎቻቸው እንዲደብቁ/ ከመግለጽ እንዲቆጠቡ እንዲሁም ከአሳዳጊዎቻቸው ሠውረው ጎጂ ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ ወይም ለአጉል ልምዶች እንዲጋለጡ/ ለመሞከር እንዲገፋፋ መንገድ ይከፍታል።

  • የስሜት መራራቅ (emotional disconnection) - የቤተሰብ አባላትና ዘመዶቻቸው እርስ በእርሳቸው የሚነጋገሩ ቢሆኑም አንዳንዶቹ ግን የልባቸውን አይገልጹም ወይም አንዳቸው ስለሌላኛቸው ስሜት ለማወቅ ፍላጎትና ጉጉት አያሳዩም/ ግድ አይኖራቸውም። በሌላ አነጋገር ቀድሞ የነበራቸው ዓይነት ቅርበት አይታይባቸውም።
  • ውሱን የሆነ ግንኙነት (low contact) - አንዳንድ የቤተሰብ አባላትና ዘመዶቻቸው እንደ ሠርግና ኀዘን ላሉ ሁኔታዎች እንጂ ከዚያ ውጪ ሥራዬ ብለው አይፈላለጉም/ አይጠያየቁም፣ ዝምድናቸው በርቀት ይሆናል ማለት ነው።
  • መቆራረጥ (estrangement) - አንዳንድ የቤተሰብ አባላትና ዘመዶቻቸው ፈጽሞ አይነጋገሩም፣ ሊያገናኟቸው የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ ይሸሻሉ/ይርቃሉ።

የመነጣጠል መሠረታዊ ምክንያቶች

የቤተሰብ መነጣጠል በድንገት የሚከሰት ሁኔታ ሳይሆን በቤተሰብ አባላት ወይም በዘመዶቻቸው መሀከል ለረጅም ጊዜ ሰፍነው የቆዩ አለመግባባቶች ወይም መፍትሔ ያልተገኘላቸው ችግሮችና ግጭቶች በሚኖርሩበት ጊዜ የሚፈጠር ሁኔታ ነው። ለምሳሌ፦

  • ወላጆችና አሳዳጊዎች ለዓመታት በልጆቻቸው ላይ ያደረሱትን ስሜታዊና አካላዊ ጥቃት (emotional and physical abuse) እንዲሁም ልጆቻቸው ሲያድጉ የተሰማቸውን የአሳዳጊ ቸልተኝነት ወይም ግድየለሽነትን (emotional and physical neglect) መሠረት አድርጎ
  • በሀብትና ንብረት ዕጦት ላይ የተመሠረተ የቤተሰብ አባል ጉዳት ወይም ቸልተኝነትን (financial abuse and neglect) ተከትሎ
  • በቤተሰብ ውስጥ የአዕምሮ ጤና እክሎች በሚኖሩበት ጊዜ መፍትሔ ለማግኘት አባላቱ ሲያዳግታቸው ወይም ከዚያ ጋር የተሳሰሩ አለመግባባቶችና ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት
  • ጾታዊ ጥቃትን (sexual trauma) አስታኮ
  • የእሴቶች አለመመሳሰል ወይም ልዩነት (clash or difference in values)
  • የአኗኗር (lifestyle)፣ የጾታዊ ማንነትንና የግንኙነቶችን ልዩነቶች(gender identity and sexualiety) ተከትሎ
  • ሐይማኖትን ወይም ዕምነትን እንዲሁም የፖለቲካ አመለካከቶችን አስመልክቶ
  • ግላዊ ድንበሮችን ወላጆችና ዘመዶች በሚተላለፉበት ወይም በሚጥሱበት ጊዜ (personal boundary violations)
  • ከአማቶች፣ ከአማቾችና ከምራቶች ጋር ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን አስከትሎ
  • የትዳርን መፍረስ አስከትለው የሚከሰቱ የቤተሰብ ግንኙነቶች ቀውሶች - ለምሳሌ፦
    • ልጆቻቸው ለአባታቸው ወይም ለእናታቸው እንዲያደሉ ወላጅና ዘመዶቻቸው ግፊት ሲያሳድሩባቸው፣
    • የውርስ ግጭቶትን አስታኮ
  • በሕይወት ውስጥ ያልተጠበቁ ለውጦች ሲፈጠሩ - ለምሳሌ፦
    • ከሥራ፣ ከጤና፣ ከኑሮ ለውጦች ጋር ተያይዞ
    • ከመደብ፣ ከሀብትና ከመብት ጥያቄዎች፣ ልዩነቶችና ለውጦች ጋር ተጣምሮ

የመነጣጠል ምልክቶች

  • የቤተሰብ አባላት ፍቅራቸውን የሚያሳዩት ወይም የሚገልጹት እነርሱ የሚፈልጉትን/ የሚጠብቁትን ሁኔታ ሌሎች ሲያሟሉላቸው ብቻ ነው (conditional love)። ለምሳሌ፡-
    • ልጆቻቸው መልካም ባህርይ ሲያሳዩ ወይም ታዛዦች ሲሆኑ ብቻ፣
    • በትምህርት ወይም በሌላ መስክ ጥሩ ውጤት ሲያመጡ ብቻ፣
    • ሚስት ለባሏ ተገዢ በምትሆንበት ጊዜ ብቻ፣ ወዘተ
  • ሁኔታዎች አስከፍተዋቸው ሰዎች ስሜታቸውን በሚገልጹበት/ በሚያሳዩበት ጊዜ ወይም ድጋፍ በሚሹበት ጊዜ ቀበጥ/ሞልቃቃ (sensitive) ብለው የቤተሰብ አባላት ዘዎትር ሲተቿቸውና ሲያንቋሽሿቸው
  • ዕውነተኛውን ሁኔታ በመሸፈን ለውጪ ሰው ያልሆኑትን መስሎ ለመታየት መጣር ወይም ማስመሰል
  • በቤተሰብ ውስጥ ግጭቶች ሲፈጠሩ ወይም ችግር ሲኖር ተወያይቶ ከመፍታት ይልቅ በተደጋጋሚ አድበስብሶ ወይም ምንም እንዳልተፈጠረ አድርጎ ማለፍ

የቤተሰብ መቆራረጥ (Estrangement - ኢስትሬንጅመንት)

የኮንቲ እና ራየንን የጥናት ሥራ መሠረት በማድረግ (Conti, R.P., & Ryan, W.J., 2013). ጁርናል ኦፍ ሳይኮሎጂ ኤንድ ቢሄቪየራል ሳየንሰዝ መቆራረጥን እንደሚከተለው ያብራራል፦

  • ሁለት የቤተሰብ አባላት ወይም የሚዛመዱ ሰዎች በሚቆራረጡበት ጊዜ ፈጽሞ አይነጋገሩም (ምናልባት በተዘዋዋሪ መንገድ በጠበቃ ወይም በዘመድ አማካኝነት ካልሆነ በስተቀር)
  • ከሁለቱ አንዳቸው የበለጠ የማምረርና ሌላኛቸውን የማራቅ ባህርይ ሊያሳዩ ይችላሉ
  • አንዳቸው ሌላኛቸውን ማግኘት ቢፈልጉ እንዴትና የት ሊያገኟቸው እንደሚችሉ ቢያውቁም ሆን ብለው ርቀታቸውን ይጠብቃሉ።
  • ከሁለት አንዳቸው ወይም ሁለቱም እርስ በእርሳቸው ሌላኛቸውን በዳይና ጥፋተኛ አድርገው ይኮንናሉ (ያደረጉትን፣ ሳያደርጉ የቀሩትን፣ ወዘተ ምክንያት በማድረግ)
What Is Family Estrangement, Really?
Estrangement isn’t black and white. Explore the complexities, causes, and emotional layers behind family distance.

የመቆራረጥ መሠረታዊ ምክንያቶች

  • ከስብስብነት (collectivistic) አመለካከት ይልቅ የግላዊነት (individualistic) አመለካከት እየገነነ በመምጣቱ (Kitayama, et. al., 2010)። በበለጸጉ አገራት/ከተሞች እና በምዕራባዊው ዓለም ውስጥ የሚያድጉ ሰዎች የቤተሰብ አባላትን ወይም የወላጆቻቸውን ስሜት ለመጠበቅ ከሚተጉ ይልቅ የእራሳቸውን ማንነት ለመረዳት፣ ለኑሯቸው መሳካትና ለዕድገታቸው እንዲሁም ለአዕምሯቸው ጤና መጠበቅ ቅድሚያና ትኩረት ይሰጣሉ። (Cancien, 1988; Mounk, 2017; Pugh, 2015)
  • የአዕምሮ ጤና ዕክል የሚያጠቃቸው ሰዎች ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣቱ
  • በቤተሰብ አባላት መሀከል ያሉ የፖለቲካ አመለካከቶችና የእሴቶች ልዩነቶች በማየላቸው
  • ዘረኝነትና ሌሎች ሁኔታዎች በሚያስከትሏቸው የተለያዩ ሁኔታዎች ሳብያ (ሥራ የማጣት፣ የአዕምሮ ጤና መቃወስ፣ በወንጀል ተግባራት ላይ የመሠማራት፣ በሱስ የመያዝ፣ ወዘተ) በልጆች የአስተዳደግ ሂደት ውስጥ አባቶቻቸው ተገቢውን ተሳትፎ ሳያደርጉ በመቅረታቸው
  • የኤል.ጂ.ቢ.ቲ.ኪው+ ማህበረሰብ አባላት የሆኑትን ልጆቻቸውን ወላጆች መቀበል ባለመፈለጋቸው (Bosley-Smith & Reczek, 2022; Graham & Barnow, 2013; Lyons et al., 2013)
  • ምራት (የልጅ ሚስት) ወይም አማች (የልጅ ባል) ከአማቶቻቸው ጋር መግባባት ተስኗቸው በባላቸው/በሚስታቸው ላይ በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምክንያት መራራቅ ብሎም መቆራረጥ ሲከሰት
  • ወዘተ

በወላጆችና በአደጉ ልጆቻቸው መሀከል የሚፈጠር መቆራረጥ

የወላጆች አቋም ምን ይመስላል?

  • ያደጉ ልጆቻችን ስለአስተዳደጋቸው ትክክልነት ወይም መስተጓጎል አስተያየት ሊኖራቸው ይችላል። ነገር ግን እኛ ወላጆቻቸው ስናሳድጋቸው ስላደረግነው የሚኖራቸው አሉታዊ አመለካከት ሁሉ ትክክል ነው ማለት አይቻልም።
  • ያደጉ ልጆቻችን እኛን አሳዳጊዎቻቸውን የመንከባከብ ኀላፊነት ይጠበቅባቸዋል።
  • የልጅ ልጆቻችንን እንዳናይ ልጆቻችን ሲከለክሉን ልጆቹንም እኛንም መበደላቸው/ መጉዳታቸው እንደሆነ ሊያውቁ ይገባል።
  • አማቻችን/ምራታችን በእኛና በልጃችን መሀከል ገብተው ሊያራርቁን አይገባም።
  • እኛ ልጅ በምናሳድግበት ወቅት በጊዜው ትክክል የመሰለንን ሁሉ አድርገናል። በአሁኑ ወቅት ካለው የአስተዳደግ ዘዴ ጋር በማነጻጸር እኛን ጥፋተኛ፣ የአስተዳደግ ዘዴያችንንም ውድቅ በማድረግ ያደጉ ልጆቻችን እኛን መወንጀላቸው ተገቢ አይደለም።
  • በአስተዳደጋችሁ ቅር ተሰኝታችሁ ሊሆን ይችላል። ያ ማለት ግን እኛ ስናሳድጋችሁ ሆን ብለን በደል አድርሰንባችኋል ማለት አይደለም።

የአደጉ ልጆቻቸው አመለካከትስ?

  • በልጅነቴ የደረሰብኝን/ ያጋጠመኝን የማውቀው እኔ ነኝ። ወላጆቼ እኔ የተሰማኝን ሊያውቁልኝ ወይም ሊነግሩኝ አይችሉም።
  • እኔን ሲያሳድጉ የከፈሉትን መስዋዕትነት የእኔ ዕዳ በማስመሰል ልጃቸው ስለሆንኩ ወይም ስላሳደጉኝ ብቻ የፈለጉትን ነገር ሁሉ እንዳደርግላችው የመጠየቅ/የመጠበቅ ወይም እንደፈለጉት የማዘዝ መብት አይሰጣቸውም።
  • አሳዳጊዎቼ ከእኔ ጋር መልካም ግንኙነት ሳይኖራቸው፣ እኔ ሳልፈልግ/ሳልፈቅድ ከልጆቼ ጋር ጊዜ የማሳለፍ መብት እንዳላቸው አድርገው ማሰባቸው ስህተት ነው።
  • የእኔ አስተዳደግ የተሻለ ሊሆን ይገባ ነበር ብዬ በምልበት ጊዜ ለመረዳት ከመሞከራቸው ይልቅ አመለካከቴን ውድቅ ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም።
  • ውርስ እንከለክልሃለን/ሻለን ብለው ወላጆቼ እኔን ማስፈራራታቸው ለመራራቃችን መፍትሔ አይሆንም። ማለትም አያቀራርበንም።
  • ወላጆቼ ወላጆቻቸው ካሳደጓቸው በተሻለ ሁኔታ አሳድገውኛል። ቢሆንም ወላጆቼ ሲያሳድጉኝ (ዐውቀውም ይሁን ባለማወቅ) እኔ ላይ በደል አላደረሱም ማለት ግን አይደለም።

https://www.relationshipsnsw.org.au/blog/family-estrangement/

Going No-Contact With a Parent or Family Member: What You Need To Know
Deciding to go no-contact with members of your family can be extremely difficult. A psychologist explains possible pros and cons, and what to consider as you make your choice.

መቆራረጥን በማስወገድ ከአደጉ ልጆቻቸው ጋር እንደገና መቀራረብን የሚሹ ወላጆች ምን ሊገነዘቡ ይገባል?

  • ወላጆቻቸው ሲያሳድጓቸው ስለደረሰባቸው በደል በቁጭት፣ በንዴት፣ በብሶት፣ በምሬት ወዘተ ዐዋቂ ልጆቻቸው በሚናገሩበት ጊዜ ወላጆቻቸው ቅር ሊላቸው ይችላል። ይሁንና በትዕግስት በማዳመጥ የዐዋቂ ልጆቻቸውን ስሜት ለመረዳት መሞከራቸው በመሀከላቸው መቀራረብ እንዲኖር ብሎም እንዲዳብር መንገድ ይከፍታል ።
  • ወላጆች በዐዋቂ ልጆቻቸው አመለካከት ባይስማሙ ወይም እሴቶቻቸው ለየት ያሉ ቢሆኑ እንኳን በቀጥታ ከሚቃወሙ ወይም የልጆቻቸውን አመለካከት ውድቅ ከሚያደርጉ ይልቅ ልዩነታቸውን በእርጋታ ለመግለጽ ቢሞክሩ ይመረጣል።
  • ወላጆች ያደጉ ልጆቻቸው በፈለጉ ጊዜ ሲጠሯቸው እንዲገኙ ወይም አብረዋቸው ጊዜ እንዲያሳልፉ ሊጠብቁ አይገባም። ዐዋቂ ልጆቻቸው የእራሳቸው ኑሮ እንዳላቸው በማስታወስ ወድደው በፈቃዳቸው እንዲጠይቋቸው ዕድል መስጠታቸው ወይም ግዴታ እንዲሰማቸው አለማድረጋቸው ለግንኙነታቸው መሳካት እጅጉን አስፈላጊ ሁኔታ ነው።
  • ወላጆች የተሰማቸው ስሜት ወይም ቅሬታ ቢኖር ዐዋቂ ልጆቻቸውን ሳይኮንኑ፣ ሳያሳፍሩ ወይም ሳያማርሩ መግለጻቸው ይጠቅማል።
  • ወላጆች በእራሳቸው አስተዳደግ ወይም በኑሮ ገጠመኞቻቸው ደስተኛ አለመሆናቸው አሉታዊ ተጽዕኖ በልጆቻቸውና በግንኙነታቸው ላይ እንዳያሳድር ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል።
  • አሳዳጊዎች እራሳቸውን በመመልከትና በመገምገም በአስተሳሰባቸው፣ በአመለካከታቸው፣ በሁኔታቸውና በአነጋገራቸው ሌሎችን ሰዎች/ልጆቻቸውን እንዳያስከፉ ማስተካከልና ማሻሻል የሚችሉት ሁኔታ እንዳለ እራሳቸውን መጠየቃቸው ተገቢ ነው።

የአደጉ ልጆቻቸውስ?

  • በወላጆቻቸው አስተሳሰብ ስሜትና ፍላጎት መመራታቸው ግዴታቸው አለመሆኑን ተረድተው ለወላጆቻቸው ከመጠን ያለፈ ኀላፊነት እንዳይሰማቸው ዐዋቂ ልጆቻቸው ለእራሳቸው ገደብ ማበጀትና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።
  • ወላጆቻቸው ቂም የመያዝ ባሕርይ እንዳላቸው ዐውቀው ያደጉ ልጆቻቸው ስሜታቸውን ለወላጆቻቸው ለማካፈል ፍራቻ ቢያድርባቸውም እንኳን እራሳቸውን በማደፋፈር ዕውነተኛውን ስሜታቸውን አክብሮትን በአዘለ መልኩ መግለጻቸው ይጠቅማል።
  • ወላጆቻቸው ፍጹማን እንዳልሆኑ በማስታወስ የወላጆቻቸውን ችሎታና ብቃት ውሱንነት ከግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው።
  • ወላጆቻቸው ሲያሳድጓቸው ያጎደሉባቸው ነገር ቢኖር በዕውቀት ወይም በብቃት ማነስ እንጂ ሆን ብለው ልጆቻቸውን ለመበደል ወይም ለመጉዳት ያደረጉት እንዳልሆነ በማስተዋል ለወላጆቻቸው ይቅርታ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
  • እራስን መለስ ብሎ ማየትና መገምገም ብሎም በእራስ ላይ አዎንታዊ ለውጦችን ለማምጣትና ዕድገትን ለማየት ጥረት ማድረግ ለግንኙነቶች መሳካት ይጠቅማል።

ወላጆች "አቅማችን በፈቀደው መጠን ለልጆቻችን ተገቢውን እንክብካቤ ሰጥተን አሳድገናል!" ብለው ሊያምኑ ይችላሉ። ይሁንና ያደጉ ልጆቻቸው "ቅሬታ አለን፣ አስተዳደጋችን የተሻለ ሊሆን ይገባ ነበር!" ብለው ስሜታቸውንና ሀሳባቸውን በሚገልጹበት ጊዜ ወላጆች በጥሞና በማዳመጥ ለመረዳት መሞከራቸው ከልጆቻቸው ጋር ለሚኖራቸው ግንኙነት መሻሻል መሠረት ይሆናል። በመከባበር በመደማመጥና በመግባባት ወላጆችም ይሁኑ ያደጉ ልጆቻቸው (በዳዩም ይሁን ተበዳይ ነኝ ባዩ) አንዳቸው የሌላኛቸውን አመለካከት ለመረዳት መሞከራቸው ከቀሞው ለየት ያለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማገዝ ያለፉትን ሁኔታዎች ተቀብለው ከቀድሞው የተሻለ በመቀራረብ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲመሠርቱ ያደርጋል።


Read more

የቤተሰብ አባላት መጠማመርና መነጣጠል - ክፍል ፩

የቤተሰብ አባላት መጠማመርና መነጣጠል - ክፍል ፩

በ1960ዎቹ (እ.አ.አ.) የቤተሰብ አወቃቀርንና የአባላቱን ግንኙነቶች አስመልክተው ጥናታዊ ሥራዎችን ያበረከቱ ሰው (Salvador Minuchin) የቤተሰብ አባላትን ገደብየለሽ ስሜታዊ የእርስ በእርስ መጠማመር ኢንሜሽመንት (Enmeshment) ብለው ሰይመውታል። በሌላ አነጋገር በቤተሰብ አባላት መሀከል ያለው የቅርበት መጠንና እራስን በእራስ መግዛትና እራስን መቻል ሚዛኑን ካልጠበቅ መጠማመር ሊከሰት ይችላል ማለት ይቻላል። በቤተሰብ አባላት መሀከል ጤናማ

By TW
የግል ገደቦች - Boundaries

የግል ገደቦች - Boundaries

ከሰዎች ጋር በሚኖሩን ግንኙነቶችና መስተጋብሮች ለእራሳችን ገደቦችን (boundaries - ባውንድሪዝ) ማበጀታችን ለህልውናችን መጠበቅና ለሰላማችን አስፈላጊ ሁኔታ ነው። እራስን መገደብ ከ- ለእራስ ገደብን ማበጀት ለየት ይላል።እራስን መገደብ ስሜትን ከመቆጣጠር ጋር የተዛመደ ነው። በአንጻሩ ግን ለእራስ ገደብን ማበጀት ደግሞ በእሤቶቻችን ላይ የተመሠረተ ሲሆን እራስን ከመገንዘብ ጋር የተሳሠረና ለእራሳችን ምን እንደምፈቅድ ወይም እንደማንፈቅድ

By TW
ሳይጠሩሽ አቤት፣ ሳይልኩስሽ ወዴት!

ሳይጠሩሽ አቤት፣ ሳይልኩስሽ ወዴት!

ሰዎች ሳይጠየቁ ምክርን ለሰው የሚለግሱት መልካም በማሰብ ወይም ተመካሪውን ለመደገፍ ቢሆንም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን የሚችልባቸው አንዳንድ አጋጣሚዎች እንዳሉ ማስተዋል ይገባል። የሚከተሉትን አባባሎች እንደ ምሳሌ እንመልከት፦ * "ጸጉርህ ሳሳ - መመልጥ ጀመርክ እንዴ?!" "ታስሮ የተቀለበ በሬ አከልሽ አይደል እንዴ?!" ወዘተ በማለት መልክና አለባበስን እንዲሁም ሰውነትንና ገጽታን አስመልክቶ ተገቢ

By TW
አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች

አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች

ተፈላልገውና ተመራርጠው አብረው ለመሆን ወይም ኑሮን አብረው ለመመሥረት የሚወስኑ ሁለት ሰዎች ወይም ጥንዶች (couples - ካፕልስ) ለግንኙነታቸው መሳካት ወይም አለመሳካት የየግላቸው የሕይወት ልምዶችና ተሞክሮዎች፣ እሤቶቻቸው እንዲሁም ሕልማቸውና ስለወደፊቱ ሕይወታቸው ያላቸው ተስፋ ወሳኝነት አላቸው። ጆን እና ጁሊ ጎትማን የተባሉ ሁለት ሳይኮሎጂስቶች (Drs. John & Julie Gottman) የጎትማን ሜተድ በመባል የሚታወቀውን የጥንዶች ሥነ-

By TW