"ይቅር ተባባሉ!"
"ይቅርታ ምንድን ነው ካልተስተካከለ፣ እሾህ አሜከላ ሆድ እያበቀለ? ..." "ይቅርታ እለምናለሁ፣ ጥፋቴን አውቅያለሁ። ..." (ጥላሁን ገሠሠ)
"አንተም ተው! አንቺም ተይ! እናንተም ተዉ! ይቅር ተባባሉ" በማለት ሰዎች የተሰማቸውን ቅሬታ ወይም የደረሰባቸውን በደል ትተው ከበደላቸው ሰው ጋር ሰላም እንዲፈጥሩ መምከር በባህላችን የተለመደ ነገር ነው።
አንዳንዶቻችን ለግጭቶች መፍትሔ ሳይገኝላቸው ይቅርታ ስለጠየቅን ብቻ የበደልነው ወይም ቅር ያሰኘነው ሰው ይቅር እንዲለን እንጠብቃለን። ይቅር ካልተባልን ደግም ይቅርታችንን ባለመቀበላቸው ተበዳዩን እንደጥፋተኛ የምንቆጥርም አለን።
ሌሎቻችን ደግሞ ሰው አስከፍቶን በጉዳዩ ላይ ተነጋግረንና ተግባብተን መላ ሳንፈጥር በደፈናው ይቅርታ ስለተጠየቅን ብቻ "እሺ ይቅር ብያለሁ" ማለታችን በቂ ሊመስለን ይችል ይሆናል።
ይቅር መባባል ታድያ በእርግጥ ምን ይመስላል?
ይቅር ማለትና ለበዳይ ምሕረትን መለገስ (forgiveness)፣ ዕርቅን መፍጠር/ መታረቅ (reconciliation) እንዲሁም ሰውን መልሶ ማመን/ በሰው ላይ እንደገና ዕምነትን መጣል (rebuilding trust) በይቅርታ ሂደት ውስጥ የሚታቀፉና ትስስር ያላቸው ሁኔታዎች ቢሆኑም አንዳቸውን ከሌላኛቸው ነጥሎ ማየቱ ይቅርታ በእርግጥ ምን ማለት እንደሆነ ለመገንዘብ ይረዳናል።
ይቅር ማለት -
- አንድን ወገን ብቻ (ተበዳዩን) ይመለከታል
- ባለፈው ወይም ቀደም ሲል በተፈጠረው ሁኔታ ላይ (the past) የተመሠረተ ነው
- የደረሰብን በደል ያስከተለብንን ንዴት፣ ቁጣ እና ቂም በፈቃዳችን መተዋችንን ያሳያል
ዕርቅን መፍጠር -
- ሁለቱን ወገኖች (በዳይንና ተበዳይን) ያቅፋል
- የሁለቱንም ወገኖች ትብብር ይጠይቃል
- በዳዮች ጥፋታቸውን አምነው ስላስከተሉት ጉዳትና ቅሬታ ይቅርታ ከመጠየቃቸው በተጨማሪ በደሉን ላለመድገም ጥረት ሊያሳዩ እንዲሁም ላደረሱት ጉዳት ካሳ ሊከፍሉ ወይም በተግባር እርማት ሊያደርጉ ይገባል
- እርስ በእርስ መታመንን (መተማመንን፣ ዕምነትን) መልሶ መገንባት ይሻል
- ግንኙነታቸውን ወደነበረበት ለመመለስ ወይም በመሀከላቸው እንደገና መቀራረብ እንዲኖር የሁለቱንም ወገኖች ጥረት ይጠይቃል
መታመን / ዕምነትን መገንባት -
- የወደፊቱን (the future) ይመለከታል
- ይቅርታን ተከትሎ ወድያው የሚሆን ሳይሆን ረዘም ያለ ጊዜን ሊወስድ የሚችልና በሂደት የሚገነባ ሁኔታ ነው
- የበዳዩን የባህርይና የተግባር ለውጦች ማሳየት፣ ማለትም በደሉ ወይም ጥፋቱ ያስከተለውን ማረምንና እንደአስፈላጊነቱ ካሳ መክፈልን ጭምር ያጠቃልላል
ሰዎች ይቅርታን ለመጠየቅ ለምን ያመነታሉ?
- ስላደረጉት ጥፋት ዕፍረት ተሰምቷቸው
- የበላይነት ወይም የኩራት ስሜትና የምን-በወጣኝነት አቋም ኖሯቸው
- በደላቸውን ለመገንዘብ ተስኗቸው ወይም የበደሉን ክብደት በማቃለላቸው
- "ተበዳዩ ይቅር ባይሉኝስ?!" የሚል ፍራቻ ተቀርጾባቸው
- እራሳቸውን ከሚገባው በላይ ጥፋተኛ አድርገው ገምተው በመሸማቀቃቸው
- በተፈጠረው ሁኔታ ግራ በመጋባታቸው/ ሁኔታውን ባለመረዳታቸው
ይቅር ማለት በደልን መርሳት ማለት አይደለም
- ቅር ያሰኘን ነገር/ሁኔታ ሆኗል፣ ስለዚህ እንዳልተፈጠረ አድርገን ልናየው ወይም ፈጽመን ልንረሳው አንችልም
- ይቅር ማለት ጉዳት ወይም በደል አልደረሰም ማለትም አይደለም
- ይቅር ስላልን ከበዳዩ ጋር የሚኖረን ቅርበት ከቅያሜው በፊት ወደነበረበት ቦታ ወዲያው ይመለሳል ማለትም አይደለም። በዳይን መልሶ ሙሉ በሙሉ ማመንና ማቅረብ ጊዜ ሊወስድ ይችላል።
- ይቅርታ በግዴታ ወይም ሰውን በማስገደድ ሊሆን አይችልም።
- ይቅርታ አድርገንም ቢሆን ከበደለን ሰው ጋር የሚኖረን ቅርበት በገደብ እንዲሆን እንመርጥ ይሆናል። (ለምሳሌ፦ በተደጋጋሚ በደል ያደረሰብንን ሰው መልሶ መቅረብና ማመን አለመፈለግ።)
ይቅርታ ከልብ ሊሆን ይገባል
በማናቸውም ዓይነት የሰዎች ግንኙነቶች ውስጥ አለመግባባቶች ወይም ግጭቶች መከሰታቸው የግድ ነው። ጥፋትን አምኖ ይቅርታን መጠየቅ የተፈጠሩትን አለመግባባቶች ወይም ግጭቶች ተባብሮ ለመፍታትና ዕርቅን ለመፍጠር መንገድ ይከፍታል።
ይቅርታ የበዳይን እና የተበዳይን ሀቀኝነት ይጠይቃል። ስለሆነም ይቅርታን ስንጠይቅ ጥፋታችንን ወይም በደላችንን ሙሉ በሙሉ አምነን ሊሆን ይገባል።
"እንደዚህ/እንደዚያ ባታርጉ ኖሮ ይህ ሁኔታ አይፈጠርም ነበር፤..." እያሉ ምክንያት መስጠት የእራስን ጥፋት ማድበስበስ ከመሆኑም በላይ ተበዳዩን መልሶ ጥፋተኛ እንደማድረግ ስለሚሆን ከእንደዚህ ዓይነቱ አነጋገር መቆጠብ ያስፈልጋል።
ጥፋታችን ምን እንደሆነ በግልጽ ተናግረን በምን መንገድ እርማት እንደምናደርግ መግለጻችን ዕርቅን ለመፍጠር ወሳኝነት አለው። ለምሳሌ፦
- "ቅር አሰኝቼህ/ አስኝቼሽ/ አሰኝቼዎት ከሆነ በቃ ይቅርታ!"
ከማለት ይልቅ፦
- "በግሌ ያካፈሉኝን በሰው ፊት ማንሳቴ ትክክል አልነበረም። በአነጋገሬ ቅር መሰኘትዎ ተገቢ ነው። ይቅርታ ያድርጉልኝ። አይለመደኝም።..."
- 'ቃሌን ባለመጠበቄ ቅር አሰኝቼሻለሁ። ስለሆነም ለምን እንደከፋሽና በእኔ ላይ እምነት እንዳጣሽ እረዳለሁ፡፡ ይቅርታ አድርጊልኝ። ስህተቴን አርሜ የተስማማንበትን ለመፈጸም ቃል እገባለሁ። ተግባሬን አይተሽ እንደምታምኚኝም ተስፋ አደርጋለሁ።"
የመጀመሪያው አባባል ጥፋትን/በደልን አይገልጽም ወይም ላጠፋነው ጥፋት/ ላደረስነው በደል ሀላፊነት መውሰዳችንን አያሳይም። በአንጻሩ ግን ሌሎቹ አባባሎች፦
- ጥፋታችንን ማመናችንን፣
- ለተበዳዩ ስሜት ቦታ መስጠታችንን፣
- ለጥፋታችን እርማት በተግባራችን እንደምናሳይ ወይም ለማሳየት ጥረት እንደምናደርግና
- ተበዳዩ መልሰው በእኛ ላይ ዕምነት እንደሚኖራቸው ያለንን ተስፋ ያመለክታል።
ይቅር ማለት ዝግጁነትን ይጠይቃል
ይቅርታን መቀበል ወይም ይቅር ማለት ስሜትን በማስገደድ የሚሆን ነገር አይደለም። ምናልባት በሁኔታዎች ግራ ስለተጋባን ወይም የደረሰብን በደል ያስከተለብን ከባድ ስሜት አልፎ እስክንረጋጋ፣ አለዚያም ደግሞ መፍትሔው ምን ሊሆን እንደሚገባ ስናብሰለስል ጊዜ ሊወስድብንና ይቅርታ ለማድረግ ዝግጁ ሳንሆን ልንቆይ እንችላለን።
በሌላ በኩል ደግሞ በዳዩ የጥፋታቸውን ክብደት ያልተረዱ ከመሰለን ወይም ያደረሱብንን ጉዳት/በደል ሙሉ በሙሉ የተረዱ መስሎ ካልታየን ይቅር ለማለት እናመነታ ይሆናል። ምንልባትም ደግሞ በደሉ ከደረሰብን ረዘም ያለ ጊዜ በማለፉ - በዳዩ ለጥፋታቸው ኀላፊነትን ላለመውሰድ ብለው ነው፣ አድበስብሰው ለማለፍ አስበው ነው ዝም ብለው የቆዩት - ብለን ገምተን በዚያ ቅር ተሰኝተን ይቅርታ ከማድረግ ወደኋላ ልንልም እንችላለን።
ከይቅርታ በኋላሳ?
ይቅርታ ለውይይት በር ይከፍታል።በበዳዩ በኩል እንዲደረጉ የምንፈልጋቸው ለውጦች ካሉ እርስ በርስ መወቃቀስን ወደጎን ትተን በበደሉ ምክንያት የተሰማንን ስሜት በመግለጽና በመፍትሔዎች ላይ በማተኮር ተወያይተን ስምምነት ላይ መድረስ፣ እንዲሁም በመሀከላችን ቅርበትን መልሰን መገንባት እንችላለን።
ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው - ከግጭቱ በፊት ወደነበረን የቅርበት ደረጃ ለመመለስ ጊዜ ሊወስድብን ወይም ደግሞ ፈጽሞ ላይሳካልን ይችላል። ለምሳሌ በዳዩ ተደጋጋሚ ጥቃት ወይም እጅግ የሚጎዳ በደል ያደረሱብን መስሎ ከተሰማን በመሀከላችን የተፈጠረው መራራቅ እንዳለ መቀጠሉ ለእኛ የተሻለ መፍትሔ ሆኖ ሊሰማን ይችላል።
መደምደሚያ
ጥፋትን አምኖ ይቅርታን መጠየቅ ብዙዎቻችንን ሊከብደን ይችላል። ስለሆነም ውስጣዊ ጥንካሬያችንን ይፈትናል። በአንጻሩ ደግሞ ይቅርታን ለመቀበል ውስጥን ማዳመጥ ይሻል። ያጋጩን ሁኔታዎች እንደማይደገሙ/እንደሚለወጡ/እንደሚሻሻሉ ተስፋ ማድረግና በደል ያደረሱብንን ሰው መልሶ ማመን እራስን ለበደልና ለተደጋጋሚ ጉዳት ሊያጋልጥ ስለሚችል ማስተዋልንና ለእራስ ጥንቃቄ ማድረግን ይፈልጋል።
ይቅርታ ስኬታማ እንዲሆን የሁለቱን (የይቅርታ ጠያቂውንና የይቅር ባዩን) መከባበር፣ በጎ ፈቃድ፣ እርስ-በእርስ መተማመንንና ትብብር ይሻል።
