ሐዘን ሲተነተን

Share
ሐዘን ሲተነተን
Photo by Thomas Bormans / Unsplash

ሐዘን (grief) የምናውቀው፣ የምንቀርበው ወይም የምንወደው ሰው በሞት ሲለየን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ከሕይወት ጋር የተገናኙ ከባድ የማጣት ጉዳቶችን (loss) አስከትሎ የሚከሰት ስሜት ነው።

ለምሳሌ፦

  • ጤናችን ሲታወክና መፍትሔ የማይገኝለት ሁኔታ ሆኖ የአካላችን ክፍል ወይም አዕምሯችን ሙሉ በሙሉ መዳን ሲሳነው
  • የትዳር ወይም የፍቅር ወዳጅነት መፍረስ፣
  • ከሰዎች ጋር የነበረን ቅርበት በተለያየ ምክንያት ሲታወክና መራራቅ/መለያየት ሲፈጠር፣
  • ጽንስ ሲጨናገፍ ወይም ዕርግዝና ሲቋረጥ፣
  • በድንገት ከሥራ መባረር፣ በጡረታ መገለል፣
  • ንብረትን ወይም ሀብትን ማጣት/መነጠቅ ፣
  • ከኖሩበት አካባቢ መፈናቀል ወዘተ

ማጣት በሦስት ፈርጆች ይከፈላል፦

  • ንብረትና ሀብትን ማጣት፤ ሥራን ማጣት/ከሥራ መባረር፣ ወዘተ (External loss)
  • በራሳችን/ በግላችን/ በውስጣችን ማጣት ሲደርስብን/ ሲያጋጥመን (የአካል/የአዕምሮ ጤና ማጣት፣ ያለምነውን ወይም ተስፋ ያደረግነውን ማጣት ፣ ወዘተ (Intra-psychic loss)
  • ከሌላ ሰው ጋር ያለንን ግንኙነት አስታኮ የሚከሰት ማጣት፦ ከሰው ጋር ያለን ግንኙነት በሞት ወይም በሌላ ምክንያት ሲስተጓጎል/ ሲሰናከል/ ሲቋረጥ፣ ወዘተ (Inter-psychic loss)

ሰውን በሞት ማጣትን አስከትሎ የሚከሰት ሐዘን ከሁሉ በላይ የከበደና ቅስምን የሚሰብር ነው። የቅርባችን የሆነ ሰው በሞት ሲለየን የሚሰማን ሐዘን ያ ሰው ስለተለየን ብቻ ሳይሆን ከሟች ጋር የተያያዙ ትውስታዎችን ስለምናጣ፣ ሟች በሕይወት ሳለ/ሳለች/ሳሉ እና አብረን በኖርንባቸው ጊዜያት ለቅርበታችን ሰጥተነው የነበረው ልዩ ቦታ ባዶውን ቀርቶ በቀን ተቀን ሕይወታችን ውስጥ ክፍተት ስለሚፈጠር፣ ከዚያም አልፎ ስለወደፊቱ አብረን አልመነው እና ተስፋ አድርገነው የነበረውን ሁሉ ስለምናጣም ጭምር ነው።

በሞትም ይሁን ከፍ ብልው በተዘረዘሩት የማጣት ሁኔታዎች ምክንያት የሚደርስብን ሐዘን በሰውነታችንና በአዕምሯችን ውስጥ ከዚህ በታች የተጠቀሱትንና ሌሎች ለውጦችን ያስከትላል

አካላዊ ለውጦች ፦

  • የድካም ስሜት
  • የዕንቅልፍ መዛባት እንዲሁም የቅዠት ዕንቅልፍ
  • የምግብ ፍላቶት መለወጥ፣ የማቅለሽልሽ ወይም የጨጓራ መቆጣት ስሜት፣ ተቅማጥ ወይም የሆድ ድርቀት
  • የራስ ምታት፣ የጡንቻዎች ህመም፣ የደረት ውጥረት ወይም የጉሮሮ ጥበት ስሜት
  • ሰውነታችን በሽታዎችን የመከላከል ኅይሉን በማጣቱ ምክንያት ለበሽታዎች መጋለጥ
  • የልብ ምትና የደም ግፊት ከፍ ማለት፣ "የልብ መሰበር" ወይም የባዶነት ስሜት
  • የማጥወልወል ስሜት፣ የአፍ መድረቅ፣ ወዘተ

ስሜታዊ ለውጦች፦

  • የስሜት መደንዘዝ (shock, numbness)፣ ሞትን ወይም ማጣትን አለመቀበል ወይም አለማመን (denial & disbelief)
  • የስሜት መተረማመስ (disorganization)፣ ግራ መጋባት (confusion)፣ ለጥያቄ መልስ ማጣት (searching)፣ መናፈቅ/ መንሰፍሰፍ/ መጓጓት (yearning)
  • መጨነቅና መጠበብ (anxiety)፣ መደናገጥ (panic) ፣ መፍራት (fear) ፣ መሸበር (terror)
  • መናደድ፣ መበሳጨት፣ መማረር
  • ራስን ወይም ሌላን መውቀስ/ መኮነን
  • መቅናት፣ መቆጨትና የጥፋተኝነት ስሜት መሰማት
  • ማዘን - መከፋት፣ መደበር፣ የቅስም መሰበር፣ ተስፋ መቁረጥ፣
  • ዕምነትን መፈተን/መጠየቅ/ መጠራጠር
  • ራስን ለመጉዳት ወይም ለማጥፋት የመፈለግ ስሜት
  • የብቸኝነት ስሜት
  • የእፎይታ ስሜት (ሟችን ለረጅም ጊዜ ስናስታምም ቆይተን ስቃያቸውን አስተውለን "አሁንስ ስቃዩ በዛባቸው - በቃ ይበላቸው" ብለን በምንመኝበት ጊዜ የሚሰማን የመቀበልና የመረጋጋት ስሜት)፣ ወዘተ

አንዳንድ ሰዎች ጮክ ብለው በማልቀስ ሐዘናቸውን የሚገልጹ ሲሆን ሌሎች ዝምታና ለብቻቸው የማብሰለሰል ባህርይ ሊያሳዩ ይችላሉ። እንደገና ሌሎች ደግም ስለሟች ትውስታቸውን ማውራትንና በሟች ስም አንዳንድ በጎ ተግባራትን ማድረግ ይመርጡ ይሆናል። ታድያ ይህ ሰዎች በተለያየ መንገድ የሐዘን ስሜታቸውን እንደሚገልጹ/ እንደሚወጡ የሚያሳይ እንጂ የሐዘናቸውን ጥልቀት/ክብደት ወይም መጠኑን የሚያመለክት አይደለም።

ሐዘን የራሱ የሆነ ሂደት ስላለው ማፋጠን ወይም ከላይ የተዘረዘሩት የማጣት ስሜታዊ ለውጦች እንዳይኖሩን ማድረግ አይቻልም። በትዕግስት ስሜቶቻችንን እያዳመጥን ለእራሳችን ጊዜንና እንክብካቤ መስጠታችን እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ሐዘንን ካፈንነው ጤናችንን በማወክ የተለያዩ የአካል ህመሞችና በሽታዎች እንዲሁም እንደ የገነነ ቁጭት/ ራስን መኮነን፣ ድብርት እና ራሳችንን ለማጥፋት የመፈለግ ስሜት ያሉ የሥነ-አዕምሮ ውጥረቶችን ሊያስከትል ይችላል።

ብዙውን ጊዜ ሰዎች በአንድ ዓመት ውስጥ ሊጽናኑና ሐዘናቸው ሊቀልላቸው ይገባል የሚል አመለካከት አለ። ይሁንና ሐዘን እንደ ቋሚው ባህርይና የሕይወት ልምድ፣ ከሟች ጋር እንደነበረን ቅርበት፣ እንደ ሟች ዕድሜና አሟሟት ወዘተ ይለያያል።

አንዳንዶቻችን ዛሬ ሐዘን በርትቶብን ውሎ ነገ ደግሞ ቀለል ሲለን፣ እንደገናም ወሎ አድሮ ሲከብደን፣ ወራት ወይም ዓመታት ተቆጥረው ሐዘኑ እንደገና ሲያገረሽብን ግራ ገብቶን "ምን ሆኛለሁ?" ብለን እራሳችንን እንጠይቅ ይሆናል። ሰው ይታዘበናል ብለንም ስሜታችንን እናፍን ይሆናል። በተለይም በልጅነታችን ወላጃችንን አጥተን ከሆነ በዕድገታችን ጉዞ ውስጥ በሚከሰቱት ለውጦች እና አዳዲስ ምዕራፎች ወላጃችን በሕይወት ኖሮ/ኖራ ይህንን ለማየት በቻለ/በቻለች ነበር ብለን በመቆጨት በየምዕራፉ የሐዘን ስሜቶች እንደገና ጎብኝተውን ይሆናል። እዚህ የተጠቀሱትና እነዚህን የመሳሰሉ ስሜቶች በሐዘን ጉዞ ውስጥ ሊደርሱ እንደሚችሉ አውቀን በተከሰቱ ጊዜ ለእራሳችን ተገቢውን እንክብካቤ እንድንሰጥ ይመከራል።

ስለደረሰብን ሐዘን ጥሩ የማዳመጥ ችሎታ ካለው ሰው ጋር ብናወራና በግልጽ የሐዘን ስሜታችንን ብናካፍል፣ የዕለት ከዕለት ተግባራትን ማከናወን ከተሳነን ደግሞ ከሐዘን አማካሪ (grief counsellor) ዕርዳታ ብንጠይቅ እራሳችንን እየተንከባከብን ሐዘናችንን ጤናማ በሆነ ሁኔታ እንድንወጣ ይረዳናል።

ሰው ሲሞት መሰባሰብና መተጋገዝ እንዲሁም የየማሕበረሰቡን ባህል፣ ደንብና ሥርዓት በተከተለ መንገድ ሐዘነተኛን ማስተዛዘንና ማጽናናት የሚጠበቅ ነገር ነው። ይሁንና ከላይ እንደተገለጸው ሐዘንን የምናስተናግድበትና የምንገልጽበት መንገድ ከሰው ሰው ሊለያይ እንደሚችል ተገንዝበን ሀሳባችንን/ምክራችንን ለሐዘነተኞች ከመለገሳችን በፊት ለማጽናናት ተብሎ በተለምዶ የሚባል አነጋገር በሐዘነተኞች ስሜት ላይ ምን ሊያስከትል ይችላል ብለን እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል ።

ለምሳሌ፦

  • “ላይችል አይሰጥም።”
  • “ሁሉም ለበጎ ነው።”
  • “ገና ወጣት ነሽ፣ ሌላ ልጅ ትወልጃለሽ።”
  • “አይዞህ - ዕድሜህ ለጋ ነው ሌላ ሚስት እንደገና ታገባለህ።”
  • “ተዉ፤ ማልቀስ ከእንግዲህ አያስፈልግም።”
  • "ሟች ረጅም ዕድሜ ኖረዋልና ማዘን አይገባም።" ወዘተ

እንደዚህ ዓይነት አባባሎች ሐዘነተኞችን ከማጽናናት ይልቅ ሐዘናቸው ተገቢ እንዳልሆነ ሆኖ እንዲሰማቸው፣ እራሳቸውን የበለጠ እንዲኮንኑና ሐዘናቸውን እንዲያፍኑ ያደርጋል። ከፍ ተብሎ እንደተገለጸው ሐዘንን ማፈን በጤናችን ላይ በርካታ አሉታዊ ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል።

ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች “እንዲህ አድርጉ” ወይም “እንዲያ አታድርጉ” ብለን ሳንጠየቅ ምክር መካሪዎች ሆነን ከመገኘት ይልቅ በትዕግስት ከልባችን አዳማጮች በመሆን ሐዘነተኞች ስሜታቸውን በፈቃዳቸው እንዲያካፍሉን ዕድል ብንሰጣቸው ይመረጣል። አንዳንዴ በዝምታ ከጎናቸው ብንቀመጥ በቂ ሊሆን እንደሚችል እናስተውል። ምን ብናደርግላቸው ወይም ምን ዓይነት ዕርዳታ ከእኛ እንደሚፈልጉ ብንጠይቃቸው (በባህላችን መግደርደር ያለ ነገር ቢሆንም) ፍላጎታቸውን እንዲገልጹና ለእነርሱ በሚመች መንገድ ድጋፍ እንድንሆናቸው ዕድል ይሰጠናል።

ማጣት፣ ሞትና ሐዘን ማናችንንም የማያበላልጡ በሁላችንም ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ክስተቶች ናቸው። ስለሆነም ስለሕይወት ገጠመኞቻችን/ልምዳችን በነጻነት እንደምንወያየው ሁሉ ስለማጣት፣ ስለሞትና ሐዘንም በግልጽ ማውራትንና በሐዘናችን ጊዜ አስተዛዛኞች በምን መንገድ እንዲደግፉን እንደምንፈልግ ያለይሉኝታ መናገርን እንልመድ።

ሐዘነተኞችን የሐዘን ስሜቶቻቸው ቀለል እንዲሉላቸው ወይም መጽናናታቸው እንዲፋጠን የሚያስችለን ኅይል ወይም ችሎታ ማናችንም እንደሌለን በመገንዘብ በትዕግስት ከሐዘን ጋር አብረን መቆየትን ለእራሳችንም ይሁን ለሌሎች እንፍቅድ። መካሪዎች ከምንሆን ይልቅ ጥሩ አዳማጮች በመሆን ሐዘነተኞች ስሜቶቻቸውን በእራሳቸው መንገድና ጊዜ እንዲያስተናግዱ ተገቢውን ቦታና አክብሮት እንስጣቸው።


Read more

አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች

አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች

ተፈላልገውና ተመራርጠው አብረው ለመሆን ወይም ኑሮን አብረው ለመመሥረት የሚወስኑ ሁለት ሰዎች ወይም ጥንዶች (couples - ካፕልስ) ለግንኙነታቸው መሳካት ወይም አለመሳካት የየግላቸው የሕይወት ልምዶችና ተሞክሮዎች፣ እሤቶቻቸው እንዲሁም ሕልማቸውና ስለወደፊቱ ሕይወታቸው ያላቸው ተስፋ ወሳኝነት አላቸው። ጆን እና ጁሊ ጎትማን የተባሉ ሁለት ሳይኮሎጂስቶች (Drs. John & Julie Gottman) የጎትማን ሜተድ በመባል የሚታወቀውን የጥንዶች

By TW
ኦቲዝም ክፍል ፪-ሥውር  ኦቲዝም

ኦቲዝም ክፍል ፪-ሥውር ኦቲዝም

ኦቲዝም የሚለውን ቃል ስንሰማ ምናልባት በአዕምሯችን ውስጥ የሚቀረጸው በሕፃናትና በልጆች የተመሰለ ምስል ሊሆን ይችላል። ይሁንና በተለምዶ በልጆችና በጎልማሶች ዘንድ ከምናየው፤ ከተነገረን፤ ካነበብነው፤ ከምናውቀው በተለየ መልኩ ኦቲዝም በዓዋቂነት የዕድሜም ጭምር ለመጀመሪያ ጊዜ ሊገኝ እንደሚችል ማስተዋል ይገባል። ኦቲዝም እ.አ.አ. ከ1911 ዓ.ም. ጀምሮ የሚታወቅ ሁኔታ ሲሆን ለበርካታ አሥርተ-ዓመታት የነበረን ግንዛቤ

By TW
የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና - አስተዳደግ ክፍል ፬

የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና - አስተዳደግ ክፍል ፬

የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና መዛባት ተስፋፍቶ የሚገኝ ክስተት ከመሆኑም በላይ እንደ የልጆች ጭንቀትና ድባቴ ያሉ ሁኔታዎች የዕድሜ-ልክ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ በመረጃ የተደገፉ ጥናቶች ያሳያሉ። (ከሲ.ዲ.ሲ. የተገኘ መረጃ ) የልጆች የአዕምሮ ጤንነት የልጆች የአዕምሮ ጤንነት የተጠበቀ ነው ብለን ስንል የአዕምሮ ጤና መዛባት እንደሌላቸው በማረጋገጥ መመስከርን ብቻ ሳይሆን ሙሉ ጤንነታቸው ተጠብቆ

By TW
አዎን! ወንዶችም ያርጣሉ!

አዎን! ወንዶችም ያርጣሉ!

የሴቶች እርጣት (menopause - ሜኖፖዝ) በእያንዳንዷ ሴት የሕይወት ሂደት ውስጥ በድንገት የሚከሰት ከኤስትሮጀንና ፕሮጀስትሮን የሴቶች ሆርሞኖች መጠን ማሽቆልቆል ሲሆን ከወር-አበባ ማብቃትና የሴቶች የመውለድ ችሎታ ፍጻሜ ጋር የተቆራኘ ሁኔታ ነው። በአንጻሩ ግን የወንዶች እርጣት (andropause - አንድሮፖዝ) በአንዳንድ ወንዶች ዘንድ ብቻ የሚከሰትና ከቴስቶስትሮን የወንዶች ሆርሞን መጠን መቀነስ ጋር የተጣመረ፣ አመጣጡ ደግሞ

By TW