ኮንሴንት Consent ምንድን ነው?
ኮንሴንት = ፈቀደ፣ ተስማማ፣ እሺ አለ - ማለት ነው። (አቢሲኒካ መዝገበ ቃላት)
https://dictionary.abyssinica.com/consent
ኮንሴንት (Consent) በዓለም-አቀፍ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ደንቦችና ሕግጋት ላይ የተመሠረት ደንብና ልማድ ሲሆን ማንም ሰው አካሉን/ አከላቱን አስመልክቶ በሕይወቱ፣ በጤናው፣ በወሲባዊ ግንኙነቱና ሌሎችም ከአካል ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች ዙሪያ ራሱ በራሱ የመወሰን ሙሉ ነጻነት እንዳለው ያመለክታል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ 'ፈቃደኝነት' ተብሎ ተተርጉሟል።
ኮንሴንት ሲተነተን (FRIES በሚሉት ፊዳሎች እንደሚጀምር ያስተውሉ)
F- Freely Given = በፈቃደኝነት የሚሰጥ - ማለትም ያለ ምንም ግፊት፣ ማስፈራራትና ማስገደድ (no pressure, threats or manipulation)
R - Reversible = በማንኛውም ጊዜ ሃሳብን መቀየር የሚያስችል (anyone can change their mind at any time)
I – Informed = ስለ ምን እንደሆነ የሚገልጽ - ማለትም የተስማማንባቸው ነጥቦች/ሀሳቦች/ሁኔታዎች/ተግባሮች የትኛዎቹ እንደሆኑ በመረዳት ላይ የተመሠረተ (you know what you’re agreeing to)
E - Enthusiastic = ግልጽ ስሜትንና ጉጉትን ወይም ፍላጎትን ያዘለ አዎንታን ያከለ (clear and enthusiastic – not silence, not “I guess” or “maybe”)
S – Specific = በአንድ ነጥብ ወይም በአንድ ጉድይ ላይ ብቻ ያተኮረ - ማለትም ለአንድ ሁኔታ እሺ ማለት ለሁሉም ነገር ፈቃደኝነት እንደተሰጠ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም (saying yes to one thing doesn’t mean yes to everything)
በአብዛኛዎቹ እንደ ካናዳ ያሉ ሀገራት ሕጎች መሠረት በኮንሴንት ወይም በፈቃደኝነት ላይ ያልተመሠረተ ወሲባዊ ግንኙነት ሕገወጥ ተግባር ወይም ወንጀል ነው። በትዳር ውስጥም ይሁን ከትዳር ውጪ ሕጉ ማናቸውም ዓይነት ሁኔታዎች ያጠቃልላል። አንድ ሰው “አልፈልግም ትዉኝ” ካለ እንዲሁም በግልጽ “እሺ እፈልጋለሁ” ብሎ ካልተስማማ ወሲባዊ ግንኙነትን መጀመርም ሆነ ከተጀመረም በኋላ መቀጠል በሕግ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው።
በካናዳ ውስጥ ኮንሴንት/'ፈቃደኝነት' በሰፊው የሚተገበር መልካም ባሕል ከመሆኑም በላይ ሰብዓዊ ክብርንና ደህንነትን ማስጠበቂያ ሕግና ልማድም ነው።
በአንዳንድ ባሕሎች እንቢታ እንደ ነውር ሊቆጠር ስለሚችል አንዳንዶቻችን በአንደበታችን “እሺ” ብለን እየተናገርን በሁኔታችንና በአካላችን የመራቅ/የመሸሽ ወይም በድን የመሆን ባሕርይ በማሳየት አለዚያም አንገታችንን እና ዓይኖቻችንን ዞር በማድረግ እንቢተኝነታችንን እንገልጻለን። የዚህ ዓይነቱ ስውርና አለመፈልግን የሚያሳይ አገላለጽ በቂ ሆኖ ሊወሰድ ይገባል። አንድ ሰው የማመንታት ወይም እንዳልፈለገ የሚገልጽ/የሚያመለክት ሁኔታን ካሳየ ኮንሴንት አልሰጠም ወይም አልፈቀደም ማለት ነው።
ሰዎች ማንኛውም ዓይነት ነገር/ሁኔታ እንዲያደርጉ ጠይቀናቸው አለመፈለጋቸውን ሲገልጹልን "እየተግደረደሩ ነው" ብለን በመገመት እኛ የፈለግነውን ወይም የጠየቅነውን እንዲያደርጉ ለማሳመንና ሀሳባቸውን ለማስቀየር የመሞከር ባህል ልንመረምረውና ልንጥለው የሚገባ ጎጂ ልማድ ነው።
ይልቁንም የወንድ ጾታ ሰው ከሆኑ፣ በዕድሜዎ ልቀው ከተገኙ/ከበለጡ፣ በሀብት፣ በሃላፊነት ደረጃና በስልጣን ከፍ ያሉ ከሆኑ የሌሎችን ኮንሴንት ወይም ፈቃደኝነት በግልጽ እንዲሹና እንዲጠይቁ አጥብቆ ይመከራል።
ለምሳሌ፦
- "አንዴ ጉንጭህን/ ጉንጭሽን መንካት ትፈቅድልኛለህ/ትፈቅጂልኛለሽ ወይ?"
- "እዚህ ጋ ብስምህ/ ብስምሽ ፈቃደኛ ነህ/ነሽ ወይ?"
- "ተስማምተን የምናደርገው ቢሆንም በመሃል ሀሳብህን ከቀየርክ ንገረኝ/ ሀሳብሽን ከቀየርሽ ንገሪኝ፤ ያለምንም ጥያቄ እናቆማለን።
- "_____ ትፈልጋለህ/ ትፈልጊያለሽ ወይ?"
- ወዘተ
ዝምታ እሺታ አይደለም። በግልጽ በመጠየቅ እዎንታንና ፈቃደኝነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ሰዎችን በአለባበሳቸው፣ በአነጋገራቸው ወይም በሁኔታቸው ፈቃደኞች የሆኑ አድርገን ብንገምት እንኳን ኮንሴንታቸውን በመጠየቅ አዎንታቸውን ልናረጋግጥ ይገባል።
በማስፈራራት፣ በማባበል፣ ወይም በማስገደድ የሚደረግ ነገር ፈቃደኝነትን ወይም ኮንሴንትን የተከተለ አይሆንም።
ይልቁንም ሰዎች በአልኮሆል መጠጥ፣ በአደንዛዥ ዕጾች፣ በጤና ጉድለት፣ በዕድሜ ለጋነት፣ በአዕምሮ ብስለት ማነስ ወይም በሌላ ምክንያት ከታወኩ ፈቃደኝነታቸውን ወይም ኮንሴንት ሊሰጡ ፈጽሞ እንደማይቻላቸው መገንዘብና ከማንኛውም ዓይነት አሉታዊ ተግባርና ወሲባዊ ግንኙነት እራስን ማገድ ያስፈልጋል።