ለሥነ-ልቦናና ለሥነ-አዕምሮ ጤና ትርኩረት እንስጥ

Share
ለሥነ-ልቦናና  ለሥነ-አዕምሮ ጤና  ትርኩረት  እንስጥ
የአዕምሮ ጤናና የአካል ጤና አይነጣጠሉም

የሥነ-ልቦናና የሥነ-አዕምሮ ጤና አገልግሎት ሰጪዎች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ። ለምሳሌ፦ በግል ተቋማት፣ በሆስፒታሎች፣ በክሊኒኮች፣ በድጋፍ መስጫዎች፣ በማገገሚያ ተቋማት፣ በከፍተኛ ትመህርት ተቋማት እና በሌሎችም ሥፍራዎች አገልግሎት ይሰጣሉ።

ሳይኮተራፒ  (psychotherapy) የአስተሳሰብ፣  የባህርይ ፣  የተግባር፣  እንዲሁም  የማሕበራዊ  ኑሮ ግንኙነት  አዎንታዊ  ለውጦችን  ለማስገኘት የሚያገለግል የሥነ-ልቦና ዕርዳታ መስክ ሲሆን በመወያተትና  በመመካከር (talk therapy) ላይ የተመሠረተ የሞያ ዘርፍ ነው።

ግለሰቦች የሳይኮቴራፒ አገልግሎት የሚሹት  በተዛቡ አስተሳሰቦች፣ ስሜቶች፣ ሀድራዎች/ባህሪዎችና ተግባሮች ምክንያት በሕይወታቸው እንዲሁም ከሰዎች ጋር ባሏቸው ግንኙነቶች ውስጥ ችግሮች ገጥመዋቸው መፍትሔ ማግኘት ሲያዳግታቸውና የዕላት-ከዕለት ኑሮን ማሸነፍ/መግፋት ሲሳናቸው አለዚያም ሁኔታዎች ውስጣዊ ሰላም ሲነሷቸው ነው።

ሳይኮተራፒስቶች (psychotherapists) በመግባባት፣ በማዳመጥ፣ አስተያየታቸውን ከመስጠት በመቆጠብና ከተገልጋዮች ጋር የተወያዩባቸውን ጉዳዮች በምሥጢር  በመጠበቅ  ላይ የተመተመሠረተ የሥነ-ልቦና ዕርዳታ ይሰጣሉ። በተጨማሪም በባህርይም ይሁን በሕይወት ልምድ ሰው ከሰው እንደሚለያይ በመገንዘብ አዕምሯቸውን ክፍት አድርገው ያለ ምንም ትዝብት የተገልጋዩን ሃሳብና ስሜት ይከተላሉ። ስለሆነም ተገልጋዮች  የተናገሩት ወደ ሌላ ሰው ጆሮ እንደማይዛመት እንዲሁም በተናገሩት ነገር ሳይኮቴራፒስቱ እንደማይታዘቧቸው ዕምነት ኖሯቸው የልባቸውን ለማውራትና ስሜታቸውን ለመግለጽ ድፍረት ያገኛሉ።

የኑሮ ጫናና ዕክሎች እንዲሁም የተለያዩ የሕይወት ገጠመኞች የአዕምሮ ውጥረት (stress)፣ ጭንቀትና (anxiety) ድብርት (depression) ሊያስከትሉ ይችላሉ። እነዚህን ስሜቶች ለመቋቋምና የመንፈስ እርጋታን ለማግኘት ከሳይኮቴራፒስት ጋር የመወያየት(individual therapy) ጥቅሙ ከፍተኛ ነው ተብሎ ይታመናል ።

በትዳር ወይም በጾታዊ ወዳጅነት ውስጥ (couples therapy) እና በቤተሰብ አባላት መካከል በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እንዲሁም ልጆችን በማሳደግ ዙሪያ ስለሚከሰቱ ውጣ ውረዶች (family therapy) በአማካዩ በየሁለት ሳምንታት ለአንድ ሰዓት ያህል በመገናኘት መወያየትና መፍትሔዎችን ከተገልጋዮች ጋር አብሮ መፈለግ በሳይኮቴራፒ ከሚሰጡ አገልግሎቶች ውስጥ እንደምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው። ሌላ ውጤታማነቱ የታመነበት የሥነ-ልቦና ዕርዳታ አሰጣት ዘዴ ከአሥር የማይበልጡ ሰዎችን በማሰባሰብ በየጊዜው እየተገናኙ የሚደረግ የእርስ-በእርስ የመደጋገፍ ውይይት (group therapy) ነው።

ሳይኮቴራፒ (psychotherapy) ከካውንስሊንግና  (counselling) ከመንፈሳዊ  ካውስሊንግ (spiritual counselling) ጋር በአያሌ ገጽታዎቹ ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም በመካከላቸው ጥቂት ልዩነቶች እንዳሉ ይታወቃል። ካውንስሊንግ መረጃና  ምክር መለገስን እንዲሁም መመሪያ  መስጠትን  ያከለ ሲሆን መንፈሳዊ  ካውንስሊንግ  ደግሞ  መንፈሳዊና  ዕምነትን  ያዘሉ ምክሮችን  የሚያካትት የሥነ-ልቦና ዕርዳታ አሰጣጥ መንገድ ነው።

ሳይካያትሪ (psychiatry) ወይም የሥነ-አዕምሮ ሕክምና  ከፍ ብሎ ከተጠቀሱት የሚለየው ከሕክምና ልዩ ዘርፎች (specializations) አንዱ በመሆኑ ነው። ሳይካያትሪስቶች (psychiatrists) ወይም የሥነ-አዕምሮ ሐኪሞች በምርመርራ የአዕምሮ ሕመም መኖር ወይም አለመኖሩን የሚያረጋግጡ፣ እንደየአስፈላጊነቱ መድሐኒት የሚያዝዙ፣ በተጨማሪም የመድሐኒት ዓይነትም ይሁን የመጠን ለውጥ ቢያስፈልግ ለታካሚዎች በማስተማርና በማስረዳት ተገቢውን ክትትል የሚያደርጉ የጤና ባለሞያዎች ናቸው።

በግል  ሕይወትዎም  ይሁን  ከሌሎች ሰዎች  ጋር ባልዎት  ግንኙነቶች  ውስጥ ግራ የመጋባት፣ መላ ወይም  ደስታን የማጣት፣ እንዲሁም የጭንቀት፣  የኅዘን፣  የድብርትና ሌሎች  ሥነ-ልቦናን የሚረብሹ ጉዳዮች ወይም ሁኔታዎች ቢያጋጥምዎ በይሉኝታ ተገድበው ለብቻዎ ከማብሰልሰል ይልቅ ከሥነ-ልቦና ጤና ባለሞያ ዕርዳታ በመጠየቅ ለአዕምሮዎ ጤና እንክብካቤ ማድረግዎ ለአካልዎ ጤና ከሚያደርጉት እንክብካቤ ጎን-ለጎን ሊያካሄድ የሚገባና የሚበረታታ ነው ።

ለልብ ህመምና ለሌሎች በሽታዎች ከስፔሻሊስት ተጨማሪ አስተያየትና እንክብካቤ እንደሚጠይቁ ሁሉ የሥነ-አዕምሮ ህመም/በሽታ  ይኖረኝ ይሆን ብለው ከጠረጠሩ  ሐኪምዎ ወደ ሳይካያትሪስት  ይልክዎት ዘንድ (ሪፈራል - referral ) መጠየቅዎ ለአዕምሮዎ ጤና ተገቢውን እንክብካቤ መስጠትዎን፣ መንፈሰ ጠንካራነትዎንና ወኔ(courage) እንዳልዎት የሚገልጽ እንጂ ድክመትዎን የሚያመለክት አይሆንም።


ለድንገተኛና ለአጠቃላይ የአዕምሮ ውጥረት ዕርዳታ ካስፈለግዎ

Immediate & General Crisis Helplines

  • ሕይወትዎን ለማጥፋት የሚገፋፋ ስሜት ካደረብዎ ወይም የሚያውቁት ሰው እራሳቸውን ለማጥፋት ፍላጎት ካደረባቸው 9-8-8 ይደውሉ ወይም ቴክስት ያድርጉ Suicide Crisis Helpline: Call or text 9-8-8 for suicide and crisis hotline toll-free, anytime across Canada, for support if you or someone you know is thinking about suicide.
  • ከፖሊስ ነጻ የሆነና በማኅበረሰብ አባላት የሚመራ - ለማያስቸኩል የአዕምሮ ጤና ዕርዳታ ለማግኘት 211  ይደውሉ Toronto Community Crisis Service (TCCS): Call 211 to access this non-police, community-led service that dispatches trained crisis workers for non-emergency mental health crises and wellness checks in certain areas of Toronto.
  • የ24 ሰዓት የስልክ የአዕምሮ ውጥረት ዕርዳታ ለቶሮንቶና አካባቢዋ Distress Centres of Greater Toronto: Offers 24/7 crisis intervention and emotional support.
  • በአስተርጓሚ በመታገዝ አስቸኳይ የአዕምሮ ጤና የ24 ሰዓት ዕርዳታ ለማግኘት Gerstein Centre Crisis Line: Provides 24/7 community-based crisis support with language interpretation services available.
  • ለአዕምሮ ጤና፣ ለሱሰኝነት፣ እንዲሁም የቁማር ሱስ የ24 ሰዓት የስልክ ዕርዳታ ለማግኘት ConnexOntario: Provides 24/7 information and referral services for mental health, addiction, and problem gambling services across Ontario.
  • ለልጆች የ24 ሰዓት የስልክ ዕርዳታ Kids Help Phone: Offers 24/7 free, confidential, and anonymous professional counselling and support to young people across Canada.
  • ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የ24 ሰዓት የስልክ ዕርዳታ ለማግኘት Assaulted Women's Helpline: Provides 24/7 crisis counselling and safety planning for women in the GTA.
  • ለአረጋውያን የስልክ ዕርዳታ Toronto Seniors Helpline: A single point of access for seniors and caregivers to access community, home, and crisis services.

ለቶሮንቶ እና አካባቢው አጠቃላይ መረጃዎችን ለማግኘት 211 ይደውሉ Call 211 to find information on a comprehensive list of community and social services throughout the GTA. 


Read more

አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች

አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች

ተፈላልገውና ተመራርጠው አብረው ለመሆን ወይም ኑሮን አብረው ለመመሥረት የሚወስኑ ሁለት ሰዎች ወይም ጥንዶች (couples - ካፕልስ) ለግንኙነታቸው መሳካት ወይም አለመሳካት የየግላቸው የሕይወት ልምዶችና ተሞክሮዎች፣ እሤቶቻቸው እንዲሁም ሕልማቸውና ስለወደፊቱ ሕይወታቸው ያላቸው ተስፋ ወሳኝነት አላቸው። ጆን እና ጁሊ ጎትማን የተባሉ ሁለት ሳይኮሎጂስቶች (Drs. John & Julie Gottman) የጎትማን ሜተድ በመባል የሚታወቀውን የጥንዶች

By TW
ኦቲዝም ክፍል ፪-ሥውር  ኦቲዝም

ኦቲዝም ክፍል ፪-ሥውር ኦቲዝም

ኦቲዝም የሚለውን ቃል ስንሰማ ምናልባት በአዕምሯችን ውስጥ የሚቀረጸው በሕፃናትና በልጆች የተመሰለ ምስል ሊሆን ይችላል። ይሁንና በተለምዶ በልጆችና በጎልማሶች ዘንድ ከምናየው፤ ከተነገረን፤ ካነበብነው፤ ከምናውቀው በተለየ መልኩ ኦቲዝም በዓዋቂነት የዕድሜም ጭምር ለመጀመሪያ ጊዜ ሊገኝ እንደሚችል ማስተዋል ይገባል። ኦቲዝም እ.አ.አ. ከ1911 ዓ.ም. ጀምሮ የሚታወቅ ሁኔታ ሲሆን ለበርካታ አሥርተ-ዓመታት የነበረን ግንዛቤ

By TW
የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና - አስተዳደግ ክፍል ፬

የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና - አስተዳደግ ክፍል ፬

የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና መዛባት ተስፋፍቶ የሚገኝ ክስተት ከመሆኑም በላይ እንደ የልጆች ጭንቀትና ድባቴ ያሉ ሁኔታዎች የዕድሜ-ልክ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ በመረጃ የተደገፉ ጥናቶች ያሳያሉ። (ከሲ.ዲ.ሲ. የተገኘ መረጃ ) የልጆች የአዕምሮ ጤንነት የልጆች የአዕምሮ ጤንነት የተጠበቀ ነው ብለን ስንል የአዕምሮ ጤና መዛባት እንደሌላቸው በማረጋገጥ መመስከርን ብቻ ሳይሆን ሙሉ ጤንነታቸው ተጠብቆ

By TW
አዎን! ወንዶችም ያርጣሉ!

አዎን! ወንዶችም ያርጣሉ!

የሴቶች እርጣት (menopause - ሜኖፖዝ) በእያንዳንዷ ሴት የሕይወት ሂደት ውስጥ በድንገት የሚከሰት ከኤስትሮጀንና ፕሮጀስትሮን የሴቶች ሆርሞኖች መጠን ማሽቆልቆል ሲሆን ከወር-አበባ ማብቃትና የሴቶች የመውለድ ችሎታ ፍጻሜ ጋር የተቆራኘ ሁኔታ ነው። በአንጻሩ ግን የወንዶች እርጣት (andropause - አንድሮፖዝ) በአንዳንድ ወንዶች ዘንድ ብቻ የሚከሰትና ከቴስቶስትሮን የወንዶች ሆርሞን መጠን መቀነስ ጋር የተጣመረ፣ አመጣጡ ደግሞ

By TW