ሳይጠሩሽ አቤት፣ ሳይልኩስሽ ወዴት!

Share
ሳይጠሩሽ አቤት፣ ሳይልኩስሽ ወዴት!
Photo by Fr0ggy5 / Unsplash

ሰዎች ሳይጠየቁ ምክርን ለሰው የሚለግሱት መልካም በማሰብ ወይም ተመካሪውን ለመደገፍ ቢሆንም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን የሚችልባቸው አንዳንድ አጋጣሚዎች እንዳሉ ማስተዋል ይገባል።

የሚከተሉትን አባባሎች እንደ ምሳሌ እንመልከት፦

  • "ጸጉርህ ሳሳ - መመልጥ ጀመርክ እንዴ?!" "ታስሮ የተቀለበ በሬ አከልሽ አይደል እንዴ?!" ወዘተ በማለት መልክና አለባበስን እንዲሁም ሰውነትንና ገጽታን አስመልክቶ ተገቢ ያልሆኑ አስተያየቶችን መስጠት፤
  • "ተዉ እንጂ፣ ሀዘንን ማጥበቅ አያስፈልግም!" "ልጅ በልጅነት ነው - ቶሎ ልጅ ውለዱ እንጂ!" ወዘተ በማለት ከባለቤቱ በላይ ዓዋቂ ሆኖ መገኘት፤
  • የሰውን ፍላጎት ወይም ዝንባሌ ከመጠየቅ ይልቅ "ጠበቃ መሆን አለብህ!" "ነርስ ብትሆኚ ይሻላል!" እያሉ ለእራስ የሚመኙትን ለሌላ መምከር፤ ወዘተ

ሌላን ሰው በሚመለከት ጉዳይ ላይ የእራሳችን አመለካከትና አስተያየት ሊኖረን ይችላል። ያ ማለት ግን በማይመለከተን ጉዳይ ላይ ያሰብነውን መግለጽ ወይም ምክር መለገስ አለብን ማለት አይደለም። ይልቁንም ደግሞ ሳንጠየቅ። ምክንያቱም፦

፩ኛ/ ተመካሪው ሰው ጉዳዩን አስመልክቶ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ አይኖራቸውም፤ ስለሆነም በግላቸው ለሁኔታው መፍትሔ የማግኘት ብቃት ያጥራቸዋል የሚል ትችት በውስጡ እንዳዘለ ሆኖ ሊወሰድና ተመካሪውን ሊያስከፋ ስለሚችል፤

፪ኛ/ መካሪው ከተመካሪው የተሻለ አመለካከትና ሀሳብ እንደአላቸው ወይም "እኔ ከአንተ/ከአንቺ የተሻለ አውቃለሁ" በማለት ሌላውን ዝቅ በማድረግ የተሰነዘረ አስተያየት እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድና መካሪውን እብሪተኛ ሊያስመስል ስለሚችል፤

የሰብሰብነትና የግለሰባዊነት ኅብረተሰቦች

የቻይና፣ የጃፓን፣ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የደቡብ አሜሪካና የአፍሪቃ ሀገራት ሕዝቦች ኮሌክቲቪስት (collectivist society) ወይም የሰብሰብነት ኅብረተሰብ አወቃቀርን ይከተላሉ። በወገናዊነት ላይ በማተኮር ለእርስ-በእርስ መግባባትና ለግንኙነቶች ጥንካሬ ከፍተኛ ቦታ ይሰጣሉ። ስለሆነም መስማማትን አንድነትንና ማሕበራዊ ሀላፊነቶችን ተጋግዞ መወጣትን ያስቀድማሉ።

በአንጻሩ የኢንዲቪዷሊስቲክ (individualistic society) ወይም የግለሰባዊነት ኅብረተሰብ አወቃቀር ለግለሰብ ስሜቶች በማድላት ሰባዓዊ መብቶችን፣ እራስን የመግለጽ ነፃነትን፣ የግል ስሜቶች መጠበቅን፣ በእራስ መተማመንንና እራስን በእራስ መቻልን ከኅብረተሰብ ትስስርና ከወገናዊነት በፊት ያስቀድማል። በሰሜን አሜሪካ፣ ምዕራብ አውሮፓና አውስትሬሊያ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች በአብዛኛው የግለሰባዊነት ባህርዮችን ያንጸባርቃሉ።

በሰብሰብነት ኅብረተሰቦች ውስጥ ከቤተሰብና ከጎረቤቶች እንዲሁም ከሚኖሩበት ማሕበረሰብ አባላት ጋር ተመሳስሎ፣ ተቻችሎና ተጋገዞ መኖር ለግለሰቦች ህልውናና ደኅንነት መጠበቅ እጅጉን አስፈላጊ ሁኔታ ነው። ስለሆነም አካባቢውን መስሎ መኖር የማይችል ሰው ቢኖር ማሕበረሰቡ ስም ያወጣለታል፣ ይተቸዋል፣ ያገልለዋል ብሎም አንቅሮ ይተፋዋል። በማሕበረሰብ አለመታቀፍ ደግሞ ሰዎችን ለአደጋ ያጋልጣል። ይህንን ሁኔታ ለማገድና ማሕበራዊ ደንቦችን ለማስጠበቅ ሲባል አንዱ ሰው ሌላኛውን መካሪና ገሣጭ ይሆናል።

የምክር ለጋሾች እሳቤዎች

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ምክር የሚለግሱት በበጎ መንፈስ ተነሳስተው ነው። ተመካሪው የደረሰባቸው የሕይወት ገጠመኝ ቀለል እንዲላቸው እንዲሁም ጭንቀትና ሀሳብ እንዲቀንስላቸው በማሰብ ነው። እርስ-በእርስ ለመቀራረብ እንዲያስችላቸው በማሰብም ጭምር ሊሆን ይችላል። ደግሞም ለእኛ መልካም ውጤትን ያስገኘልን ሃሳብ/ተግባር ለሌሎች ሰዎችም እንደሚሠራ አድርገን ገምተን ያንን ለማካፈል ጉጉት አድሮብን ​ሊሆን ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ምናልባት ሌላ ሥውር ዓላማ ሊኖረንም ይችላል። ለምሳሌ፦ እራሳችንን ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ በእራሳችን እንደምንተማመን ወይም ልዩ ዕውቀት እንዳለን ሰው እንዲያውቅልን በመፈለግ፣ ወዘተ። በተለይ የናርሲሲዝም (narcissism) ባህርይ አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች ሳይጠየቁ መካሪ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ሌላን ሰው ለመቆጣጠር የመፈለግ እንዲሁም በእራሳቸው የመመጻደቅ እና የበላይነት ባህርዮችን በማንጸባረቃቸው፣ በተጨማሪም በግብዝነት እራሳቸውን ዐዋቂ አድርገው በማቅረብ አላስፈላጊ ዝርዝር ትንታኔ በማብዛታቸውና በአሰልቺነታቸው ይታወቃሉ።

እናማ...

ሰዎች የማንፈልገውን/ የማንቀበለውን ዓይነት ምክር ሲለግሱን ባይመቸን፣ ቢያስከፋን ወይም ቢያናድደን መልሳችን ከምክር ለጋሹ ጋር እንዳለን ቅርበት እንዲሁም የዕድሜና የስልጣን ልዩነት ሊለያይ ይችላል። የይሉኝታ ባህልም የተሰማንን ከመግለጽ እንድንቆጠብ ሊያደርገን ይችላል።

ለማንኛውም - እራሳችንን ካረጋጋን በኋላ ምክር ሰጪውን ስለሃሳባቸው አመስግነን "እስቲ አስብበታልሁ" ብለን ነገሩን መቋጨት እንችላለን። ሊቆጣጠሩን የፈለጉ ወይም ግፊት ሊያሳድሩብን እየሞከሩ ሆኖ ከተሰማን ደግሞ አሁንም ስለሃሳባቸው አመስግነን "ለገጠመኝ ጉዳይ መፍትሔ በግሌ አግኝቼለታለሁ። ምክርዎ ወደፊት ካስፈለገኝ እጠይቅዎታለሁ" በማለት ገደብ ማበጀት ይቻላል።

በአንጻሩ ምክር ለጋሾቹ እኛ ከሆንን ደግም ሀሳባችንን ከመናገራችን በፊት ለአንድ አፍታ ትንፋሽ ወስደን ...

  • "የአሰብኩትን ለማለት ያነሳሳኝ ምንድን ነው? መናገሬስ ምን ፋይዳ አለው?"
  • "ሀሳቤን እንዳካፍል ተጠይቄአለሁ ወይ?"
  • "ባጸጥታ አዳማጭ ብሆን ወይም የማብራሪያ ጥያቄ ብጠይቅ በቂ ይሆን?"
  • "አስተያየቴን ቢሰሙ ምን ሊሰማቸው ይችል ይሆን?"

...ብለን እራሳችንን እንድንጠይቅ ይመከራል። አያት ቅድም-አያቶቻችን በተረትና ምሳሌ መልክ የተዉልንን ቁም-ነገሮች ማስታወስም ይጠቅማል።

  • የአፍ ወለምታ በወጌሻ አይታሽም!
  • ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባበትም!
  • ሁሉ ቢናገር ማን ይሰማል!
  • ለመስማት የፈጠንክ ለመናገር የዘገየህ ሁን!
  • ለብልህ አይነግሩ ካልጠየቀ በስተቀር!
  • ለብልህ አይነግሩ ለንጉሥ አይመክሩ!
  • ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች!
  • ከባለቤቱ በላይ ያወቀ ቡዳ ነው!

Read more

የግል ገደቦች - Boundaries

የግል ገደቦች - Boundaries

ከሰዎች ጋር በሚኖሩን ግንኙነቶችና መስተጋብሮች ለእራሳችን ገደቦችን (boundaries - ባውንድሪዝ) ማበጀታችን ለህልውናችን መጠበቅና ለሰላማችን አስፈላጊ ሁኔታ ነው። እራስን መገደብ ከ- ለእራስ ገደብን ማበጀት ለየት ይላል።እራስን መገደብ ስሜትን ከመቆጣጠር ጋር የተዛመደ ነው። በአንጻሩ ግን ለእራስ ገደብን ማበጀት ደግሞ በእሤቶቻችን ላይ የተመሠረተ ሲሆን እራስን ከመገንዘብ ጋር የተሳሠረና ለእራሳችን ምን እንደምፈቅድ ወይም እንደማንፈቅድ

By TW
አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች

አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች

ተፈላልገውና ተመራርጠው አብረው ለመሆን ወይም ኑሮን አብረው ለመመሥረት የሚወስኑ ሁለት ሰዎች ወይም ጥንዶች (couples - ካፕልስ) ለግንኙነታቸው መሳካት ወይም አለመሳካት የየግላቸው የሕይወት ልምዶችና ተሞክሮዎች፣ እሤቶቻቸው እንዲሁም ሕልማቸውና ስለወደፊቱ ሕይወታቸው ያላቸው ተስፋ ወሳኝነት አላቸው። ጆን እና ጁሊ ጎትማን የተባሉ ሁለት ሳይኮሎጂስቶች (Drs. John & Julie Gottman) የጎትማን ሜተድ በመባል የሚታወቀውን የጥንዶች ሥነ-

By TW
ኦቲዝም ክፍል ፪-ሥውር  ኦቲዝም

ኦቲዝም ክፍል ፪-ሥውር ኦቲዝም

ኦቲዝም የሚለውን ቃል ስንሰማ ምናልባት በአዕምሯችን ውስጥ የሚቀረጸው በሕፃናትና በልጆች የተመሰለ ምስል ሊሆን ይችላል። ይሁንና በተለምዶ በልጆችና በጎልማሶች ዘንድ ከምናየው፤ ከተነገረን፤ ካነበብነው፤ ከምናውቀው በተለየ መልኩ ኦቲዝም በዓዋቂነት የዕድሜም ጭምር ለመጀመሪያ ጊዜ ሊገኝ እንደሚችል ማስተዋል ይገባል። ኦቲዝም እ.አ.አ. ከ1911 ዓ.ም. ጀምሮ የሚታወቅ ሁኔታ ሲሆን ለበርካታ አሥርተ-ዓመታት የነበረን

By TW
የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና - አስተዳደግ ክፍል ፬

የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና - አስተዳደግ ክፍል ፬

የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና መዛባት ተስፋፍቶ የሚገኝ ክስተት ከመሆኑም በላይ እንደ የልጆች ጭንቀትና ድባቴ ያሉ ሁኔታዎች የዕድሜ-ልክ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ በመረጃ የተደገፉ ጥናቶች ያሳያሉ። (ከሲ.ዲ.ሲ. የተገኘ መረጃ ) የልጆች የአዕምሮ ጤንነት የልጆች የአዕምሮ ጤንነት የተጠበቀ ነው ብለን ስንል የአዕምሮ ጤና መዛባት እንደሌላቸው በማረጋገጥ መመስከርን ብቻ ሳይሆን ሙሉ ጤንነታቸው

By TW