የቤተሰብ አባላት መጠማመርና መነጣጠል - ክፍል ፩
በ1960ዎቹ (እ.አ.አ.) የቤተሰብ አወቃቀርንና የአባላቱን ግንኙነቶች አስመልክተው ጥናታዊ ሥራዎችን ያበረከቱ ሰው (Salvador Minuchin) የቤተሰብ አባላትን ገደብየለሽ ስሜታዊ የእርስ በእርስ መጠማመር ኢንሜሽመንት (Enmeshment) ብለው ሰይመውታል። በሌላ አነጋገር በቤተሰብ አባላት መሀከል ያለው የቅርበት መጠንና እራስን በእራስ መግዛትና እራስን መቻል ሚዛኑን ካልጠበቅ መጠማመር ሊከሰት ይችላል ማለት ይቻላል።
በቤተሰብ አባላት መሀከል ጤናማ ስሜታዊ ገደቦች ካልተከበሩ የሰዎችን አዕምሯዊና ስሜታዊ ዕድገቶች በመግታት ቤተሰባዊ ሰላምንና ደህንነትን ሊያውኩ እንደሚችሉም አክለው ገልጸዋል።
በአንጻሩ ደግሞ በቤተሰብ አባላት መሀከል መቀራረብ ሳይኖር ሲቀር፣ ወይም ደግሞ በመሀከላቸው ሊከሰት የሚችለውን መራራቅ መነጣጠል (disconnection - ዲስኮኔክሽን) ወይም መለያየት (disengagement - ዲስኢንጌይጅመንት) ብለውታል። በእንደዚህ ዓይነት የቤተሰብ አወቃቀር ውስጥ የሚያድጉ ልጆችና ታዳጊ ወጣቶች አንዳንዶቹ ሕጎችን በመጣስ፣ ከቤት ሸሽቶ በመጥፋት፣ ወዘተ አጉል ጸባዮችን ሲያሳዩ ሌሎች ደግሞ የአዕምሮና የአካላዊ ጤና መታወክ ሊደርስባቸው ይችላል።
ቤተሰባዊ የእርስ በእርስ ግንኙነትን እንደ ረጅም አግዳሚ ዋልታ ወይም መስመር አድርገን ብናስበውና በአንዱ የዋልታ/የመስመር ጫፍ ላይ የመጠማመር ወይም የኢንሜሽመንት ግንኙነት አለ ብለን ብንል በሌላኛው ጫፍ ደግሞ የቤተሰብ አባላት መለያየትን፣ መራራቅን ወይም መነጣጠልን (disconnection - ዲስኮኔክሽን) እናገኛለን።
በሁለቱ የዋልታ ጫፎች መሀከል ደግሞ የግል ገደቦችን ያዘለውን ጤናማ ግንኙነት እናገኛለን። (ባለፈው ጦማር ላይ በዝርዝር የተነጋገርንበት አርዕስት ነውና ይህንን በመጫን ትንታኔውን ይመልከቱ።)
በቅድሚያ የቤተሰብ መጠማመር በምን ምክንያት እንደሚከሰትና ምንን ሊያስከትል እንደሚችል እንመለከታለን። በተከታዩ ጦማር በክፍል ፪ ደግሞ በቤተሰብ መነጣጠል ላይ እናተኩራለን፡፡
መጠማመር (Enmeshment - ኢንሜሽመንት)
እርስ በእርሱ ተጠላልፎ የተወታተበን የሱፍ ክር እንደምሳሌ አድርገን ብንወስድ ክሮቹን ለመፍታት ሲሞከር አንዱ ክር ሌላውን ክር ሊጎትት እንደሚችለው ሁሉ በተጠማመሩ ቤተሰቦች ውስጥም (enmeshed families - ኢንሜሽድ ፋምሊዝ) የቤተሰቡ አባላት ስሜቶቻቸው እርስ በእርሳቸው የተጠላለፉ ይመስል የአንዱ የቤተሰብ አባል የሚሰማው ስሜት፣ የሚፈልገው ነገር፣ የአለበት ሁኔታ፣ ተግባሩ ወዘተ የሌሎቹን የቤተሰብ አባላት - በይበልጥም የልጆችን - ስሜት ሊነካ ብሎም ሊያውክ ይችላል።
ለምሳሌ፦ "ለከፍተኛ ትምህርት ከቤት ርቄ ብሄድ ወላጆቼ ሰው አይሆኑም/ ይጨነቃሉ/ ይጎዳሉ። የእነርሱ መጨነቅ ደግሞ እኔንም ያስጨንቀኛል። ስለዚህ የምፈልገውና ምርጫዬ ባይሆንም ቀረብ ያለ ቦታ እመዘገባለሁ። ዕውነተኛውን ፍላጎቴን ብናገር ሴልፊሽ (selfish) የሆንኩ ይመስላል ብዬ እሰጋለሁ፣ በተጨማሪም እነርሱን ማስከፋት አልፈልግም።"
ወጣቷ ለሕይወቷ ወሳኝ በሆነ ጉዳይ ላይ ለእርሷ ትክክል የሆነውን መንገድ መከተል ትታ ወላጆቿን ላለማስከፋት ስትል ከፍላጎቷ ውጪ አቅጣጫዋን ለመቀየር መወሰኗ እነርሱ ቅር እንይላቸው ብላ ብቻ ሳይሆን እነርሱ ከከፋቸው እርሷም ደስ እንደማትሰኝ ስለገመገመች ነው። ይህ ምሳሌ የሚያሳየን የወጣቷ ስሜት ከወላጆቿ ስሜት ጋር መጠማመሩን ነው።
ወላጆቿ የእራሳቸውን ስሜት መግራት የሚችሉና ከልጆቻቸው ጋርም ጤናማ ስሜታዊ ገደቦች ያሏቸው ሰዎች ቢሆኑ ኖሮ ወጣቷን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ "አንቺ ምን ታስቢያለሽ? ምን ቢሆን ትክክል ይመስልሻል? " እያሉ አስተያየቷን እየጠየቋት ታድግ ነበር። በውሳኔዎችዋና በምትወስዳቸው እርምጃዎች ልምዶችን እያካበተች በሄደች ቁጥር ደግሞ በእራስ-መተማመንዋን ያጎለብተው ነበር። በተጨማሪም የወላጆቿ ዋና ኀላፊነት አርሷን መደገፍ እንደሆነ ስለምትገነዘብ ለከፍተኛ ትምህርት ርቃ ስትሄድ ቢያዝኑ ወይም ቢከፋቸው ስለሚወዷት እንጂ ራቅ ወዳለ ተቋም መሄዷን ጠልተው እንዳልሆነ ገብቷት ትረጋጋም ነበር። ስለዚህም የትምህርት ምርጫዋ የወላጆቿን ሳይሆን የእራሷን ስሜትና ፍላጎት የተከተለ ይሆን ነበር።
ይህ ምሳሌ የሚያሳየን የሚያድጉ ልጆችና ወጣቶች ከአሳዳጊዎቻቸው ጋር የሚኖርራቸው ግንኙነት ጤናማነትም ይሁን ውስብስብነት ወደፊት በትምህርት፣ በሥራ፣ እንዲሁም በማኅበራዊና በትዳር ሕይወታቸው ውስጥ ለሚኖሯቸው ግንኙነቶች ወሳኝነት እንዳላቸው ነው።
በፍራቻ የአሳዳጊዎቻቸውን ስሜት እያዳመጡ እነርሱን ለማስደሰት ሲሉ የእራሳቸውን ስሜት ገትተው ያደጉ ሰዎች ዘዎትር የሌሎችን ሰዎች ስሜት የማስቀደም ባህርይና በእራሳቸው የመተማመን ጉድለት ሊታይባቸው ይችላል። ስለሆነም ጤናማ ግንኙነቶችንና ጠንካራ ወዳጅነትን ለመገንባት ሊቸገሩ ይችላሉ። ወላጆች በሚሆኑበትም ጊዜ (- እራሳቸውን ተመልክተው አንዳንድ ባህርያቸውን ለማሻሻል ካልተጉ በስተቀር -) ለልጆቻቸው ይህንኑ ጎጂ ልምድ ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
በአንጻሩ ደግሞ በመወያየት፣ በመደማመጥ፣ በመተሳሰብና በመግባባት ግጭቶችን መፍታት ለምደው፣ ለስሜቶቻቸው ትኩረት ተሰጥቶ፣ ጤናማ በሆኑ ገደቦች ተደግፈውና በፍቅር ያደጉ ሰዎች የመጠማመር ባህርይ አይታይባቸውም። ስለሆነም ከሌሎች ሰዎች ጋር በመግባባት ጤናማና ዘላቂ ግንኙነቶችን መመስረት አያዳገግታቸውም። የወላጅነት ኅላፊነታቸውንና ግዴታቸውን ለይተው በማወቅ ለልጆቻቸው ስሜት ተገቢውን ቦታ ይሰጣሉ ፣ ጤናማ ገደቦችን በተግባራቸው ለልጆቻቸው ያስተምራሉ።
መጠማመርን ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች
ሀ/ ስሜታዊ ገደቦች (boundaries - ባውንድሪዝ) ግልጽ ካልሆኑና አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን እንደጓደኛቸው ዓይተው ስሜቶቻቸውን ያለገደብ ሲያካፍሉ -
ለምሳሌ፦ "አባትህ እንደገና አመሸ ደግሞ፤ ለዚያውም ክፉ ነገር ይደርስበታል ብዬ እንደምሰጋ እያወቀ። ጠዋት ትምህርት ቤት ሲወስድህ ምን ያህል እንደተጨነቅሁ ንገረው፤ አንተን ይሰማህ ይሆናል።"
የዚህ ዓይነቱ አባባል ልጆችን በወላጆቻቸው መሀከል በማይገባ መልኩ ወሬ አመላላሽ ከማድረጉም በላይ ለአባታቸው ማምሸት እንዲሁም ለእናታቸው ጭንቀት መላ የመፍጠር ኀላፊነት እንዲሰማቸው ሊያደርግና ሊያሳስባቸው ይችላል። ከዚያም አልፎ ወላጆቻቸው ይፋታሉ የሚል ሥጋት ሊያሳድርባቸውም ይችላል። በተጨማሪም ልጆች እራሳቸው በግላቸው የተሰማቸውንና ለወላጆቻቸው ማካፈል የሚያስፈልጋቸው/የሚገባቸው ጉዳይ ቢኖር እንኳን ወላጆቻችንን እናስጨንቃለን ብለው በመሳቀቅ ከመንገር እንዲቆጠቡና ችግራቸውን በውስጣቸው ደብቀው በምስጢር እንዲይዙ ይገደዳሉ። ስሜታቸውን ጤናማ በሆነ መንገድ ከመግለጽ ይልቅ ዘዎትር ወደውስጥ ማፈናቸው ደግሞ ለጭንቀትና ድባቴ ሊዳርጋቸው ይችላል።
ለ/ ልጆችና ታዳጊ ወጣቶች አሳዳጊዎቻቸውንና ሌሎች የቤተሰብ አባላትን የመንከባከብ ኀላፊነት ሲጣልባቸው -
ለምሳሌ፦
- ልጆች ለወላጆቻቸው የቋንቋ አስተርጓሚ ሆነው ማወቅ ለማይገባቸው ሁኔታዎች በሚጋለጡበት ጊዜ (በመስማትና በማንበብ) -
- ወላጆች ታማሚዎች ከሆኑ ወይም ሁለት ሶስት ሥራዎችን ከቤት ውጪ መሥራት ከኖረባቸውና ልጆች (ይልቁንም ታላቅ/የመጀመሪያ ልጆች) የቤት ውስጥ ሥራዎችን የማከናወንና ታናሽ እኅት ወንድሞቻቸውን የመንከባከብ ኀላፊነት ሲጣልባቸው -
እነዚህ ሁኔታዎች የቤተሰብ አባላትን ለመጠማመር በማጋለጥ ልጆችን ከወላጆቻቸው እኩል የቤተሰባቸውን የዕለት-ተዕለት ኑሮ በተመለከተ ለችግሮች መፍትሔ የማግኘትና ቤተሰቡን የመምራት ኀላፊነት እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል (= role reversal - ሮውል ሪቨርዛል/ parentification - ፓረንቲፊኬሽን)። በተጨማሪም ለእራሳቸው ፍላጎቶች ቅድሚያ መስጠት ቢገባቸው እንኳን (ለምሳሌ ደክሟቸው ማረፍ ቢያስፈልጋቸው) የጥፋተኝነት (guilt - ጊልት) ስሜት ሊያሳድርባቸውና የአዕምሮ ሰላም ሊነሳቸው ይችላል።
ተያይዞም ለሚከተሉት ዘላቂ የመጠማመር ጉዳቶች እንዲጋለጡ ይሆናል፦
- ጭንቀትና ጥበት (anxiety - አንግዛየቲ)፣ ድባቴ (depression - ዲፕሬሽን)
- የገነነ ሰውን ለማስደሰት የመፈለግና የመጣር አጉል ባህርይ (people pleasing - ፒፕልፕሊዚንግ)
- ለእራስ ተገቢውን ገደብ ማበጀት አለመቻል (lack of personal boundaries - ላክ ኦፍ ፐርሰናል ባውንድሪዝ) እና እራስን ለጥቃትና ለጉዳት ማጋለጥ
ሐ/ አሳዳጊዎች እራሳቸውን የማረጋጋት ልምድ ሳይኖራቸው ቀርቶ እንደ ንዴት፣ ፍርኀት፣ ሥጋትና ጭንቀት ያሉ ስሜቶች ሲሰሟቸው ልጆቻቸውን በየምክንያቱ ጥፋተኛ በማድረግ በሚወነጅሉበት ጊዜ
- ከዘር ወደዘር በተዋረድ የወረሱትን የወላጅ አምባገነንነት የአስተዳደግ ልምዶችን በግትርነት በመከተል
- ልጅን የማሳደግ ዕውቀትና ብቃት ሳይኖራቸው ሲቀር (ባለማወቅና በስህተት)
ለምሳሌ፦
"ከእኅትሽ ጋር ስትጨቃጨቁ የደም ብዛቴን አባሳችሁብኝ፣ በግፊቱ ምክንያት አንድ ነገር ብሆን ይቆጫችኋል!"
"ትወዱታላችሁ ብዬ ለእናንተ የሠራሁላችሁን ምግብ ለምን አልበላ ትላላችሁ? እኔ ቅር ሲለኝ ግድ የላችሁም መሰለኝ።"
"አናንተ አስረፍዳችሁኝ ባታናድዱኝ ኖሮ ቁልፉን ያስቀመጥኩበትን ቦታ ማስታወስ አያቅተኝም ነበረ።"
በተጠማመረ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ሰዎች እራሳቸው ፈቅደው/ ወድደው ላደረጉት ነገር ወይም በእራሳቸው ጥፋት ልጆቻቸው የማይገባ ኀላፊነት እንዲሰማቸውና እንዲሳቀቁ ያደርጋሉ። "እንዲህ አድርጌልህ..." "እንዲህ ደክሜልሽ..." እንዲያ ተጎድቼላችሁ ..." በማለትና ለልጆቻቸው ውለታ የዋሉ በማስመሰል ለስሜታቸው እንዲሁም ለጤንነታቸውና ለደህንነታቸው ልጆቻቸው እንዲጨነቁና ባለዕዳነት እንዲሰማቸው ያደርጋሉ።
መ/ የባህል ተጽዕኖ - በሰብሰብነት ማህበረሰብ (collectivist society) እና በግለሰባዊነት ማህበረሰብ (individualistic society) መሀከል በሚፈጠሩ ልዩነቶች።
ለምሳሌ፦
- ይሉኝታን በመፍራትና ለየት ብሎ ላለመታየት ሲባል ማስመሰል -
- ሰውን ላለማስከፋት ወይም ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን/ግጭቶችን ለማገድ በማሰብ ከፍላጎት ውጪ ሌሎች ሰዎች የሚፈልጉትን ማለት/ ማድረግ -
በውጪው ዓለም ልጆች የሚያሳድጉ ሰዎች ከሀገራቸው ይዘው በመጡት ባህል "ሰው ምን ይላል" እያሉ በመጨነቅ በሚያሳድጓቸው ልጆችላይ ተገቢ ያልሆኑ ግፊቶችን ሊያሳድሩ ይችላሉ። ልጆቻቸው የእራሳቸውን ስሜት ችላ ብለው ለአሳዳጊዎቻቸው ጭንቀት ትኩረትና ቅድሚያ በሚሰጡበት ጊዜ የመጠማመር ግንኙነት ሊከሰት ይችላል ።
መጠማመር የሚያስከትላቸው ጉዳቶች
- የእራስን ማንነት፣ ፍላጎቶችን፣ እሴቶችንና (values - ቫልዩዝ) ግቦችን (goals - ጎውልዝ) ለይቶ ማወቅ አለመቻል
- ለጭንቀትና ለድባቴ መጋለጥ
- በእራስ አለመተማመን ፣ በነገሮችና በሁኔታዎች ላይ ውሳኔ መስጠት አለመቻልና ዘዎትር የሌሎችን አስተያየት በመጠየቅ ማሰልቸት
- የእራስን ፍላጎቶች በመጫንና የሌላን ሰው ስሜት ከማስቀደም ጋር ተያይዞ ለሚከሰት የቅሬታ ስሜት (resentment - ሪዜንትመንት) እራስን ማጋለጥ
- ስለሌሎች ሰዎች ስሜቶች እራስን ጥፋተኛ አድርጎ መወንጀል (guilt - ጊልት)
- በጾታዊ ወዳጅነትና በግንኙነቶች ውስጥ ለአላስፈላጊ ግጭቶች መጋለጥ