የግል ገደቦች - Boundaries
ከሰዎች ጋር በሚኖሩን ግንኙነቶችና መስተጋብሮች ለእራሳችን ገደቦችን (boundaries - ባውንድሪዝ) ማበጀታችን ለህልውናችን መጠበቅና ለሰላማችን አስፈላጊ ሁኔታ ነው።
እራስን መገደብ ከ- ለእራስ ገደብን ማበጀት ለየት ይላል።እራስን መገደብ ስሜትን ከመቆጣጠር ጋር የተዛመደ ነው። በአንጻሩ ግን ለእራስ ገደብን ማበጀት ደግሞ በእሤቶቻችን ላይ የተመሠረተ ሲሆን እራስን ከመገንዘብ ጋር የተሳሠረና ለእራሳችን ምን እንደምፈቅድ ወይም እንደማንፈቅድ የሚያመለክት ነው። በተጨማሪም እራሳችንን ለመንከባከብና የአዕምሮ ጤናችንን ለመጠበቅ እጅጉን ጠቃሚ ቅድመ ሁኔታም ነው።
እሤቶቻችንን መሠረት ያደረጉ የግል ገደቦቻችን ከሰዎች ጋር በሚኖሩን ግንኙነቶች ሁሉ ያንኑ ያንጸባርቃሉ። ለምሳሌ፦
- ለጊዜ ወይም ለሰዓት ቦታና ክብር የምንሰጥ ከሆነ ጊዜ እንዲባክን አንፈቅድም። የቀጠሮና የሥራ ሰዓት እናከብራለን፣ ለሚያረፍድ ሰው ትዕግሥት አይኖረንም።
- ከቤተሰባችንና ከልጆቻችን ጋር አብረን ለምናሳልፈው ጊዜ ዋጋ የምንሰጥ ከሆነ የሥራ ሰዓታችንን አናራዝምም፣ በተለያየ ምክንያት ከቤተሰብ ውጭ የምናሳልፈውንም ጊዜ የቤተሰብ ጊዜያችንን በማይሻማበት መልኩ እንመጥናለን።
- እራሳችንን መንከባከብና ጤናችንን መጠበቅ ከእሤቶቻችን አንዱ ከሆነ ሌላን ሰው እናስቀይማለን በሚል ሥጋት ለጤናችን የማይስማማንን ምግብ አንበላም። ለሰውነት ማጠንከሪያ እንቅስቃሴዎች ጊዜ እንመድብላቸዋለን። ሌሎች ሁኔታዎች የመኝታችንን ወይም የዕረፍታችንን ጊዜ እንዲጋፉ አንፈቅድም።
- ዕውነተኝነት የምንመራበት እሤት ከሆነ ከሰዎች ጋር በሚኖሩን ግንኙነትቶች ሁሉ ዕውነትን እንናገራለን፣ ስለዕውነት እንመሰክራለን። ለማስመሰል ስንል ወይም ሰውን ለመምሰል ስንል አንዋሽም። (ወዘተ)
የግል ገደቦቻችን እንደምንገኝባቸው ሁኔታዎች እንዲሁም ከሰዎች ጋር እንዳለን ቅርበት ሊለያዩ ይችላሉ። ከቤተሰብና ከጓደኞቻችን ጋር የሚኖሩን ገደቦች ከሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አዲስ ከተዋወቅነው ሰው ጋር ከሚኖሩን ገደቦች ለየት ይላሉ። ከአበሾች ጋር የሚኖሩን ገደቦች እንዲሁ ሌላ ባህል ካላቸው ሰዎች ጋር ከሚኖሩን የግል ገደቦች የሚለዩባቸው ባህርይዎች አሉ።
ህልውናችንን ለመጠበቅ የምንጠቀምባቸው ገደቦች ሦስት ገጽታዎቻችን ሊያንጸባርቁ ይችላሉ። በአንድ ወገን ያለን ሰዎች ግትር ገደቦች ሲኖሩን በሌላ ወገን ያለን ደግሞ የላሉና ሌሎች መስመሮቻችንን እንዲጥሱ መንገድ የሚከፍቱ ዘርዛራ/ልል ገደቦች ይኖሩን ይሆናል። በሁለቱ ተቃራኒ የዋልታ ጫፎች መሀከል የምንገኝ ደግሞ ሚዛናዊነትን ያዘሉና ጤናማ ገደቦችን እንተገብራለን።
ግትር ገደቦች
(Rigid boundaries - ሪጅድ ባውንድሪዝ) - ጥይት የማያስገባ በርና ግድግዳ እንደማለት
ግትር ገደቦች ያሉን ሰዎች እራሳችንን ከጉዳት ለመከላከል ስንል ሌሎችን ሰዎች አንቀርብም ወይም አናቀርብም። ይህ ባህርያችን ጽኑ አቋምና ጥንካሬ ያለን እንዲመስለንና እራሳችንን በእራሳችን የምንችል፣ የሌላ ሰው ዕርዳታ የማያስፈልገን ሆኖ እንዲሰማን ስለሚያደርግ ከሰዎች ጋር እንዳንቀራረብና እንዳንዛመድ በማድረግ ለብቸኝነት ይዳርገናል፣ ብሎም የአዕምሮ ጤናችን ለጉዳት እንዲጋለጥ መንገድ ይከፍታል። ተያይዞም ጠቃሚ ልምዶችንንና ተሞክሮዎችን የማግኘት ዕድሎችን እንድንነፈግ ያደርጋል።
ዘርዛራ/ልል ገደቦች
(Porous boundaries - ፖረስ ባውንድሪዝ) - በር የሌለው ቤት ውስት እንደመኖር
ዘርዛራ ወይም ልል ገደቦችን የምንተገብር ሰዎች ስለግል ሕይወታች አላስፈላጊ ወይም ከመጠን ያለፈ ግልጽነትን እናበዛለን። የሌሎችን ሰዎች ጉዳይ የእራሳችን በማድረግ እራሳችንን ለአላስፈላጊ ጭንቀት እንዳርጋለን። በተጨማሪም የማንፈልገው ነገር ቢኖር ለመግለጽ ስለሚከብደን ወይም ደግሞ ይሉኝታ ስለሚሰማን ከፍላጎታችን ውጪ ፈቃደኞች ሆነን እንገኛለን።
ይህ ጸባያችን ለሌሎች ሰዎች ምቹ አድርጎን በቀላሉ የሚያቀራርበን ቢሆንም ስሜታችንን እና ፍላጎቶቻችንን ተከትለን ሳይሆን ለመወደድ ወይም ላለማስቀየም ብለን ስለምናስመስል ሰዎች እውነተኛ ማንነታችንን የማወቅ ዕድል አይኖራቸውም፣ ስለሆነም ቅርበታችን ጥልቀት አይኖረውም። ይህ የማስመሰል ወይም የመምሰል ባህርያችን በውስጣችን ጥሩ ስሜት እንዳይሰማን ስለሚያደርግ ለመንፈስ ጭንቀትና ለአዕምሮ ጤና ቀውሶች ያጋልጠናል።
ጤናማ ገደቦች
(Healthy boundaries - ሄልትዚ ባውንድሪዝ) - ሚዛናዊነት ያለው፣ እንደየሁኔታውና እንደፈቃዳችን የምንከፍተውና የምንዘጋው በር ያለው ቤት ውስጥ እንደመኖር
ለእራሳቸው ጤናማ ገደቦችን የሚያበጁ ሰዎች ግትር ወይም ልል ገደቦችን ከመተግበር ይልቅ ሁኔታዎችን በመገምገም ከሰዎች ጋር በጎ ቅርበትን ይሻሉ። ስለየግል ሕይወታቸው ለሌሎች የሚያካፍሉትን እንደቅርበታቸው ይመጥናሉ። እንዲሁም ጤናቸውንና ሕልውናቸውን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ሲሉ በሁኔታዎች ካልተስማሙ አይሆንም በማለት ገደቦችን ያበጃሉ፣ ለይሉኝታ አይገዙም።
ከቤተሰባችን አባላት ጋር፣ ከሥራ ባልደረቦቻችን፣ ከጓደኞቻችን፣ ዕምነታችን ከሚያስተሳስረን ሰዎች ጋርም ይሁን በሌሎች አጋጣሚዎች ሁሉ ጤናማ ገደቦች እንዲኖሩን ማድረጋችን እርስ-በእርስ መከባበርን እና መተማመንን (trust - ትራስት) ስለሚያጎለብት ከሰዎች ጋር ለሚኖሩን ግንኙነቶች መሳካት እጅጉን ወሳኝነት አለው።
ጤናማ ገደቦች ካሉን ዕውነተኛ ስሜቶቻችንን እና ፍላጎቶቻችንን በመግታትና በመጫን የአዕምሮ ጤናችንን ለጭንቀትና ለውጥረት አንዳርግም። የሚያስፈልገን ዕርዳታ ወይም የሁኔታ ለውጥ ቢኖር ከመጠየቅ ወደኋላ አንልም።
የግል ገደቦችን መተግበር
- ገደቦቻችንን ለመለየት - አንዳንድ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች በውስጣችን የሚፈጥሯቸውን ስሜቶች በማስተዋል "ምንድን ነው እንዲሆን የምፈልገው?" ብሎ እራስን መጠየቅ ያስፈልጋል። ለምሳሌ፦
- የመጠራጠር ወይም ያለመመቸት ስሜት ከተሰማኝ ሰላምና ምቾት እንዲሰማኝ ምን ማድረግ ያስፈልገኛል? ምን ቢሆን ይሻለኛል?
- ለደህንነቴ ያሠጋኛል የሚል ስሜት ካደረብኝ ሥጋቴን ለማስወገድ ምን ዓይነት ገደብ ለእራሴ ባበጅ ይጠቅመኛል?
- የመንፈስ መረበሽ ስሜትን የሚያስከትሉብኝ ሁኔታዎች የትኛዎቹ ናቸው? እነዚህን ሁኔታዎች ለመከላከልና እራሴን ለመንከባከብ የሚረዱኝ የግል ገደቦች ምን ይመስላሉ? (ወዘተ)
- ገደቦቻችንን ለመግለጽና ለመተግበር - አንተ ወይም አንቺ እንዲህ ስላደረጋችሁ/ ስላላችሁ ብለን ከመወንጀል ይልቅ "እኔ የዚህ ዓይነት ስሜት ስለተሰማኝ እንደዚህ አደርጋለሁ ወይም እንዲያ ቢሆን እመርጣለሁ" በማለት ስሜታችንን እና ፍላጎታችንን ወይም የማንፈልገውን ነገር/ሁኔታ መግለጽ ይመከራል። ይህ አባባል I-statement (አይ ስቴይትመንት) በመባል ይታወቃል። ለምሳሌ፦
- (እኔ) አደጋ ያስከትልብኛል ብዬ ስለምሠጋ ይህንን ሰው/አካባቢ እርቃለሁ።
- (እኔ) በዚህ ሁኔታ/አባባል ስለማልስማማ በጉዳዩ ላይ ላለመሳተፍ ወስኛለሁ።
- (እኔ) ስላልገባኝና ሁኔታው ግራ ስለገባኝ ውሳኔዬን ከመግለጼ በፊት የማሰቢያ ጊዜ እፈልጋለሁ።
- የማይስማማን ነገር ሲኖር ይቅርብኝ/አይሆንም በማለት አንድን ሁኔታ አለመፈለጋችንን መናገራችን በቂ ሊሆን ይገባል። ማለትም ለምን የሚል ጥያቄ ቢያስከትል እንኳን ካልመሰለን/ካልፈለግን በስተቀር ምክንያት ወይም ማብራሪያ የመስጠት ግዴታ የለብንም ማለት ነው።
- የግል ገደቦቻችን እንዲከበሩልን ስንጠብቅ የሌሎችን ሰዎች የግል ገደቦችም ልናከብር እንደሚገባ በማስታወስ የሚከተሉትን ምልክቶች ወይም ፍንጮች ልናስተውል ይገባል፦
- ስናናግራቸው ዓይኖቻቸውን ወይም ፊታቸውን ከእኛ ዞር ካደረጉ እንድንተዋቸው ፈልገው ሊሆን ይችላል ብለን ማሰባችን የሌሎችን ሰዎች የግል ገደቦች ከግምት ውስጥ ማስገባታችንን ያመለክታል።
- አነጋገራቸው ጥድፍ ጥድፍ እንዳለ ሆኖ ከተሰማን "አሁን ሰውን ማናገር አልፈለጉ ወይም አይችሉ ይሆን ወይ?" ብለን እራሳችንን መጠየቃችን ለሌሎች ሰዎች ስሜቶች ቦታ እንደምንሰጥና የግል ገደቦቻቸውን ለማክበር ያለንን ትጋት ያሳያል።
- ለምንናገረው የአንድ ቃል ወይም አጫጭር መልሶችን ከሰጡን አሁንም "ምናልባት እንድንተዋቸው ፈልገው ይሆን ወይ?" ብለን ልናስብ ይገባል። (ወዘተ)
ዓይነቶቻቸውስ?
ስለ ግንኙነቶችና የግል ገደቦች በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ Nedra Glover Tawwab ስድስት የገደብ ዓይነቶች እንዳሉ በመግለጽ እንደሚከተለው ይተነትኗቸዋል፦
አካላዊ ገደቦች
(Physical boundaries - ፊዚካል ባውንድሪዝ) = የአካላችንን ጤና እና የእረፍት ፍላጎታችንን ለማስጠበቅ የምንገልገልባቸው ገደቦች ናቸው።
- አጠገቤ ከሚገኝ ሰው ወይም ሰው ከተሰበሰበበት ቦታ ምን ያህል ራቅ ብዬ ብቆም ምቾት ይሰማኛል?
- ሰው እንዲያቅፈን፣ እንዲነካን፣ እንዲጨብጠን (ወዘተ) ፈቃዳችን ነው ወይ?
ለምሳሌ አንዳንድ ልጆች ሰዎች እንዲያቅፏቸው ወይም እንዲስሟቸው አይፈልጉም። የልጆቻቸውን አካላዊ ገደቦች የሚያከብሩ ወላጆች ከልጆቻቸው ፍላጎት ውጪ ሰዎችን በማቀፍ ወይም በመሳም ሰላም እንዲሉ አያስገድዱም። ልጆቻቸውን አይመቱም፣ አይኮረኩሙም፣ አይቆነጥጡም።
ስሜታዊ ገደቦች
(Emotional boundaries - ኢሞሽናል ባውንድሪዝ) = ስሜቶቻችንን እንዲሁም ስሜታዊ ጤናችንን እና አቅማችንን (emotional energy - ኢሞሽናል ኤነርጂ) ለመንከባከብ እንገለገልባቸዋለን።
- ስሜቶቻችንን ለመንከባከብም ይሁን ለመግለጽ ሀላፊነቱ የእያንዳንዳችን ወይም የእኛ የእራሳችን ነው። ብንናደድ እራሳችንን ማረጋጋት፣ ብናዝን ስሜታችንን ማባበል፣ ቢደክመን ዕረፍት ማድረግ ወዘተ የሚጠበቀው ከእኛ ከእራሳችን ነው።
- የሌሎችን ሰዎች(የቤተሰባችንን አባላት ጭምር) ስሜትና ጭንቀታቸውን የመሸከም ሀላፊነት ሊጠበቅብን አይገባም።
ለምሳሌ፦ ጭንቀታቸውንና የሕይወት ውጣውረድ ያስከተለባቸውን ስሜታዊ ውጥረትና ጫና ወላጆች ለልጆቻቸው ማካፈላቸው/ ማውራታቸው የልጆቻቸውን ስሜታዊ ገደቦች ስለሚተላለፍ አሳዳጊዎችና ወላጆች ይህንን ሊገነዘቡና ከእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ሊቆጠቡ ይገባል። በተመሳሳይ ሁኔታ ስለደከመን፣ ስለራበን፣ ስላመመን ወይም ስለተናደድን (ወዘተ) የሌላን ሰው ስሜት በሚነካ መልኩ ልንናገር አይገባም፣ ስሜታዊ ገደባቸውን ማክበር ይጠበቅብናል።
ወሲባዊ ገደቦች
(Sexual boundaries - ሴክሹዋል ባውንድሪዝ) = አከላታችን፣ ጾታዊ ማንነታችን እና መብታችን እንዳይደፈር ለማገድ እንገለገልባቸዋለን።
ጾታዊና ወሲባዊ ግንኙነትን አስመልክቶ ለሚኖሩን ስሜቶችና ፍላጎቶች እንዲሁም ተሳትፎ እያንዳንዳችን የግላችን የሆኑ ገደቦች አሉን። ስለሆነም ለመሳተፍ መፈለጋችንን እና ፈቃደኝነታችንን (consent - ኮንሴንት) ሰዎች ሊጠይቁን ይገባል።
ወሲባዊ ገደቦቻችን እራሳችንን ከጾታዊና ወሲባዊ ጥቃት ለመከላከልና ሕልውናችንን ለመጠበቅ/ለማስጠበቅ ይጠቅሙናል። ለምሳሌ፦
- ጾታችንን አስመልክቶ ጸያፍ አባባሎችንና ሁኔታዎችን ለማገድ
- በመዳበስ/በመንካት እንዲሁም ለወሲባዊ ግንኙነት ከፍላጎታችን ውጭ በማስገደድ ሌሎች ሰዎች መብታችንን እንዳይይጋፉ ለማገድ
የጊዜ ገደቦች
(Time boundaries - ታይም ባውንድሪዝ) = ለሥራ ወይም ለትምህርት፣ ለእረፍት፣ እንዲሁም ለተለያዩ የግል ጉዳዮቻችን የምናውለውን ጊዜያችንን ለመንከባከብ እንገለገልባቸዋለን።
- ሰዓታችንን በምን ዓይነት መንገድና ሁኔታ ልናሳልፍ እንደምንፈልግ በመወሰን ለእራሳችን የጊዜ ገደቦችን መስጠታችን ሀላፊነቶቻችንን ለመወጣትም ይሁን ከሰዎች ጋር በመሆን ለምናሳልፈው ጊዜና ለምናወጣው ጉልበት ያለንን አክብሮት ያሳያል።
- ለጊዜያችን ገደቦችን ማበጀታችን በጊዜ ውጥረት ሳብያ ሊደርስብን የሚችላውን የመንፈስና የአዕምሮ ዝለትን (burnout - በርናውት) ለመከላከል ይረዳናል።
ለምሳሌ፦ ሥራ የመግቢያና የመውጫ ሰዓታችንን በማክበር፣ ጉዳይ እያለን ሰዎች በወሬ እንዳይይዙን ገደብ በማበጀት፣ ከጊዜያችንን እና ከአቅማችን በላይ የሆኑ ሀላፊነቶችን ከመውሰድ በመቆጠብ፣ ወዘተ።
ቁሳዊ ገደቦች
(Material boundaries - ማቲሪያል ባውንድሪዝ) = ንብረታችንን፣ ሀብታችንን እንዲሁም ገንዘባችንን ለመንከባከብና ጉዳቶችን ለመከላከል የምንገለገልባቸው ናቸው።
ቁሳዊ ገደቦቻችን ከሀብት ንብረታችንና ከገንዘባችን የትኛውን ወይም ምን ያህሉን ለማካፈል፣ ለማዋስ፣ ለማበደር፣ ለመስጠት አለዚያም ለመሸጥ እንደምንፈልግ ወይም አለመፈለጋችንን ለመወሰን ያስችሉናል።
ለምሳሌ፦ ሰዎች ገንዘብ እንድናበድራቸው ቢጠይቁን ምን መልስ እንደምንሰጥ ለመወሰን፣ በቤተ-መጻሕፍትና በመዝናኛ ቦታዎች (ወዘተ) የሚገኙ በጋራ የምንገለገልባቸውን ንብረቶችና ሥፍራዎች ደንብና ሥርዓትን በተከተለ መልኩ ለመጠቀም፣ ወዘተ።
የአስተሳሰብና የአመለካከት መብት ገደቦች
(Intellectual boundaries - ኢንቴሌክቿል ባውንድሪዝ) = አስተሳሰባችንን፣ አመለካከታችንን፣ እሤቶቻችንን እንዲሁም እምነቶቻችንን ለማስከበር የምንጠቀምባቸው ናቸው፡፡
እያንዳንዳችን የግላችን የሆኑ ምናልባትም ከሌሎች ሰዎች ለየት ያሉ አመለካከቶች አስተሳሰቦች፣ እሤቶችና እምነቶች ሊኖርሩን ይችላል። እነዚህ ልዩነቶቻችን አንዳችንን ከሌላኛችን ዝቅ ወይም ከፍ አያደርጉንም። ስለሆነም ውይይቶችና ክርክሮች ላይ ስንሳተፍ ልዩነቶቻችንን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ለተለያዩ አመለካከቶች አክብሮትን በመስጠት ሊሆን ይገባል። የሚያጋጩን ሁኔታዎች ከተፈጠሩ/ የሚፈጠሩ ከመሰለን ደግሞ የግል ገደቦቻችንን በመጠቀም ውይይቱ/ክርክሩ ላይ መሳተፍ አለመፈለጋችንን መግለጽ እንችላለን፡፡
ለምንኖርበት ሥፍራ የግቢ አጥር ወይም በር ስናበጅ በግቢው ወይም በቤቱ ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች ደህንነትና ሰላም ለመጠበቅ ነው። ሰው በር ቢያንኳኳ እንኳን ከፍተን ማንነቱን ዓይተን እኛ ካልፈቀድን በስተቀር ማንም ሰው ወደ ግቢያችንና ቤታችን ሰተት ብሎ ሊገባ አይገባም። በተመሳሳይ ሁኔታ ህልውናችንን፣ሰላማችንን እና የአዕምሯችንን ጤና ለመጠበቅ እንዲሁም እኛን ሊጎዱ ይችላሉ ብለን የምንገምታቸውን ሁኔታዎች ለማገድ ለእራሳችን ገደቦችን ማበጀታችን ይጠቅመናል።