የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና - አስተዳደግ ክፍል ፬
የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና መዛባት ተስፋፍቶ የሚገኝ ክስተት ከመሆኑም በላይ እንደ የልጆች ጭንቀትና ድባቴ ያሉ ሁኔታዎች የዕድሜ-ልክ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ በመረጃ የተደገፉ ጥናቶች ያሳያሉ። (ከሲ.ዲ.ሲ. የተገኘ መረጃ )
የልጆች የአዕምሮ ጤንነት
የልጆች የአዕምሮ ጤንነት የተጠበቀ ነው ብለን ስንል የአዕምሮ ጤና መዛባት እንደሌላቸው በማረጋገጥ መመስከርን ብቻ ሳይሆን ሙሉ ጤንነታቸው ተጠብቆ ዕድገትና ብስለታቸው እንዲዳብሩ (ability to thrive) ሁኔታዎች የተመቻቹላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥንም ያካትታል። (ከሲ.ዲ.ሲ.- CDC ሴንተር ፎር ዲዚዝ ኮንትሮል ኤንድ ፕሪቬንሽን የተወሰደ)
ከጆርጅ ኻል የልጆችና የቤተሰብ ማዕከል (George Hull Centre for Children and Families) የተገኘ መረጃ ፦
- በዐዋቂ ዕድሜ የሚታዩ የአዕምሮ ጤና ዕክሎች 70 በመቶ የሚሆኑት የሚጀምሩት በልጅነት ዕድሜ ነው።
- በካናዳ ውስጥ ከ15 እስከ 24 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚነኙ ወጣቶት ዘንድ ለሞት ከሚያበቋቸው ዋና ምክንያቶች አንዱ የእራስን ሕይወት ማጥፋት ነው።
- ትኩረት ተሰጥቷቸው በጊዜ የሕክምና እርዳታ ከተሰጣቸው ከ60 እስክ 70 በመቶ የሚሆኑት የደረሰባቸው የአዕምሮ ጤና ዕክል ተወግዶ የተሻለ ጤንነት ይሰማቸዋል።
ከአምስት ልጆች አንዱን/አንዷን የአዕምሮ ጤና ችግር ሊያጋጥመው/ማት እንደሚችልና የቀን-ተቀን ሕይወቱን/ቷን፣ እንዲሁም የትምህርትና የማሕበራዊ ኑሮ ብቃቱን/ቷን ሊያውክ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ።
እንደ ጭንቀት (anxiety)፣ ድባቴ (depression)፣ ኤ.ዲ.ኤች.ዲ (ADHD - የትኩረት ማጣትና የዕረፍት-አልባነት ሁኔታ)፣ አመጋገብን ከማስተጓጎል ጋር የተቆራኙ ዕክሎች (eating disorders - ኢቲንግ ዲስኦርደርስ) እና ኦ.ሲ.ዲ. (OCD - ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር) ያሉ ሁኔታዎች በአብዛኛው ከ18 ዓመት ዕድሜ በፊት መታየት እንደሚጀሩ፣ በአንጻሩ ደግሞ ትኩረት ተሰጥቷቸው በወቅቱ መፍትሔ ሲገኝላቸው ሁኔታዎቹ ሊያስከትሏቸው የሚችሏቸው የዕድሜ-ልክ ጉዳቶች እንደሚወገዱ የዓለም-አቀፍ የጤና ድርጅት (WHO) ያስረዳል።
የልጅነትና የወጣትነት ዕድሜ ፈጣን የአካልና የአዕምሮ ዕድገት የሚታይባቸው ከመሆናቸው ባሻገር ልጆችና ወጣቶች ለአዕምሮ ጤና ቀውሶች የሚጋለጡባቸው ዘመናትም ናቸው።
ለልጆችና ወጣቶች ጠቅላላ ጤና እንዲሁም ለዕድገታቸውና ለደኅንነታቸው መጠበቅ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያሏቸው ግንኙነቶች ጥንካሬና የሚያድጉባቸው ወይም የአካባቢያቸው ሁኔታዎች መመቻቸት ወይም አለመመቻቸት ወሳኝነት አላቸው።
ሰላም፣ ደኅንነት፣ እርጋታና እንክብካቤ የተሞላባቸው ግንኙነቶችና የአካባቢ ሁኔታዎች ለልጆች አካላዊና አዕሞሯዊ ጤንነትና ዕድገት ጠንካራ መሠረት ናቸው።
በአንጻሩ ደግሞ በቤት ውስጥና ከቤት ውጪ - በትምህርት እንዲሁም በዲጂታል መስኮች - የሚከሰቱ አሉታዊ ተሞክሮዎች ልጆችን ለአዕምሮ ጤና ቀውሶች ያጋልጣሉ። ለምሳሌ፦
- ልጆች አካላዊ/አዕምሯዊ/መንፈሳዊ ጉዳትና ጭቆና ሲደርስባቸው ወይም ለሌላ ሰው ጉዳትና ጭቆና ሲጋለጡ
- ሱስ (የአደንዛዥ ዕፆች፣ የመጠጥ፣ ወዘተ) ወይም የአዕምሮ ጤና እክል ካለባቸው ወላጅ/አሳዳጊ ጋር አብረው ለመኖር ሲገደዱ
- ለኑሮ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ሁኔታዎች (መጠለያ፣ ምግብ፣ ወዘተ) ሳይሟሉላቸው ሲቀሩ
በልጅነት ዕድሜ የሚከሰቱ ጭንቀት፣ ፍርሃትና ድባቴ
ልጆች እንደማንኛውም ሰው አልፎ አልፎ ፍርሃት እና ጭንቀት እንዲሁም የማዘንና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል። ይሁንና ከመጠን ያለፉና ዕረፍት የሚነሱ የፍርሃት ወይም የጭንቀት እንዲሁም የማዘን ስሜቶች መሠረታቸው ከአዕምሮ ጤና መዛባት ጋር የተገናኘ ሊሆን እንደሚችል ማስተዋል ተገቢ ነው። በተጨማሪም ጭንቀትና ድባቴ አብዛኛውን ጊዜ በጣምራነት የሚከሰቱ መሆናችውን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል ።
የልጅነት የገነነ ጭንቀትና ፍርሃት
የልጅነት ከመጠን ያለፈ ጭንቀት ፍርሃትና መረበሽ ወይም አንግዛየቲ (anxiety) አንዳንድ ልጆችን ሲያነጫንጭ ወይም ሲያስቆጣቸው፣ ሌሎችን ደግሞ ዕንቅልፍ በመንሳት ድካም እንዲጫናቸው ያደርጋል፣ የሆድ ወይም የራስ ሕመምም ሊያስከትልባቸው ይችላል።
የልጅነት ጭንቀትና ፍርሃት የተለያዩ ሁኔታዎች ጋር ሊከሰቱ ይችላሉ:: ለምሳሌ፦
- መለያየትን አስከትሎ የሚከሰት የጭንቀትና የመረበሽ ሁኔታ (separation anxiety disorder) - ልጆች ከወላጆቻቸው መለየት ብርቱ ፍርሃትና ጭንቀት ሲያስከትልባቸው
- ጥላቻ ወይም ፎብያ (phobia) አንዳንድ ነገሮችን ወይም ሁኔታዎችን ከመጠን በላይ መፍራትና መሸሽ - ለምሳሌ ሸረሪትን፣ ውሻን፣ ሐኪምን ወዘተ
- ማሕበራዊነትን በመፍራት የመጨነቅና የመሸሽ ሁኔታ (social anxiety disorder) ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያገናኙ አጋጣሚዎችን እጅጉን መፍራትና መሸሽ - ለምሳሌ ትምህርት ቤት ከመሄድ ጋር የተያያዘ ጭንቀትና ፍራቻ
- የተስፋፋ የጭንቀትና የመረበሽ ሁኔታ (generalized anxiety disorder) ሁኔታዎችንና ቦታን ሳይለይ የሚከሰት ሲሆን የዕለት-ተዕለት ኑሮን ሊያውክ የሚችል የተጋነነ የመጨነቅ የመጠበብና የፍርሃት ስሜት ነው
- ድንገተኛ ድንጋጤና መሸበር (panic disorder) በድንገት የሚከሰት የተጋነነ ፍርኀትን ያዘለ የመሸበር ስሜት - የልብ ምት ፍጥነቱን ይጨምራል፣ መተንፈስ ያቅታል፣ የማዞር ስሜትንና ማላብን ያካትታል
የልጅነት ድባቴ
ምንም እንኳን ልጆች ሁሉ አልፎ አልፎ የማዘንና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሊያድርባቸው የሚችል ቢሆንም አንድዳንድ ልጆች ግን ቀላል ሁኔታዎችን መቋቋም አዳግቷቸው የከበደ የማዘንና ተስፋ የመቁረጥ ስሜቶች ሊጫጫኗቸው ይችላሉ። ተያይዞም ወትሮ ያስደስቷቸው ለነበሩ ነገሮችና ሁኔታዎች ፍላጎት የማጣት ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል ። እነዚህ ምልክቶች ረዘም ላለ ጊዜ (ከአንድ ወር በላይ) በልጆች ባህርይ ላይ በሚታዩበት ወቅት ድባቴ ተጭኗቸው ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።
ድባቴ የተጫናቸው ልጆች የሚከተሉት ሁኔታዎች ይታዩባቸዋል፦
- አዘውትሮ የሚከሰት የማዘንና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እንዲሁም ነጭናጫነት
- ደስታን በሚሰጡ ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ላይ መሳተፍን አለመፈለግ
- የአመጋገብ ለውጦችን ማሳየት - ከወትሮው እጅጉን የበለጠ ወይም በጣም ያነሰ የምግብ ፎላጎት ማሳየት
- የዕንቅልፍ መዛባት - ዕንቅልፍ ማብዛት ወይም ማጣት
- የጉልበት ማነስ፣ የድካምና የመሳነፍ ወይም የመቁነጥነጥ ባህርይ ማሳየት
- የማስተዋል ችሎታ ማነስ
- በእራስ የመተማመን ስሜት መቀነስ፣ እራስን መኮነን ወይም መንቀፍ
- እራስን ሆን ብሎ መጉዳት (self-harm)
- የተባባሰ ድባቴ የእራስን ሕይወት ለማጥፋት ማሰብንና ዘዴዎችን መፈለግን ሊያስከትል ይችላል
ድባቴ ያለባቸው ልጆች ስሜታቸውን ላይገልጹ ወይም ሊደብቁ፣ ማዘናቸውንም ላያሳውቁ ይችላሉ። የማይጠበቅ ባህርይ ሊታይባቸውም ይችላል። ስለሆነም ምን እንደሚሰማቸው ጠይቀን ለመረዳት ከመጣር ይልቅ አስቸጋሪ ልጆች ናቸው ብለን ልንገመግም እንችላለን።
የልጅነት ጭንቀትንና ድባቴን መከላከል
ልጆች ለምን የተጋነነ ጭንቀት ፍርሃትና ድባቴ እንደሚያድርባቸው ወይም መነሻው ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ከዘር የሚወረሱ ተፈጥሯዊና የባህርይ ልዩነቶችን ጨምሮ በተለያዩ ተነባባሪ ሁኔታዎች ሳብያ ሊከሰቱ ይችላሉ ተብሎ ይታመናል።
የተጋነነ ጭንቀት ፍርሃትና ድባቴ እንዳይደርስባቸው የልጆችን መሠረታዊ ፍላጎቶች ከማሟላት በተጨማሪ ስሜቶቻቸውን በመከታተል የሚሰማቸውን ማካፈል እንዲችሉ ወይም እንዲደፍሩ አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠርና ማበረታት ይገባል።
የአካልና የመንፈስ እንዲሁም የስሜት ጉዳቶችና ጭቆናዎች፣ በሌሎች ልጆች መገለልንና መገባጠርን (bullying) የሚጋብዙ ሁኔታዎች፣ የወላጆችና የአሳዳጊዎች ጭንቀትና ድባቴ፣ እነዚህንና ሌሎች በልጆች ላይ የመንፈስ ውጥረትን (stress) ሊያስከትሉ የሚችሉ አጋጣሚዎችን በማስወገድ እፎይታንና ሰላምን የሚያስከብሩ የአካባቢ ሁኔታዎን ማመቻቸት ያስፈልጋል።
የልጅዎ ባህርይ የሚያሳስብዎ ከሆነና በጭንቀት ወይም በድባቴ ምክንያት የተከሰተ ለውጥ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ ካደረብዎ ከአዕምሮ ጤና ወይም ከሥነ-ልቦና ባለሞያ ጋር በመማከር ግምገማና እርዳታ መሻትዎ ለልጅዎ የአዕምሮ ጤንነት መጠበቅ ትኩረት መስጠትዎንና በይሉኝታ አለመገደብዎን ያሳያል።
ልጆችና ወጣቶች ለቤተሰባቸው ስሜታቸውን መግለጽ ከተሳናቸው ስለ አዕምሮ ጤና ዕውቀትና ብቃት ካላቸው የእርዳታ ሰጪዎች ጋር ምስጢራቸው ተጠብቆ መወያተት እንደሚችሉ በማሳወቅ ከዚህ በታች ባሉት ቁጥሮች እንዲደውሉ ወይም ቴክስት እንዲያደርጉ አለዚያም ድኅረ-ገጾቻቸውን በመጎብኘት እርዳታ እንዲጠይቁ ማበረታት ይመከራል፦
Suicide Crisis Helpline - Call or Text: 9-8-8 website: 988.ca
Helpline for Children and Youth - Call: 1-800-668-6868 - Text: 686868 website:kidshelpphone.ca
Good2Talk - For post-secondary students - 1-866-925-5454 website:good2talk.ca
Distress Centres of Greater Toronto - Call: 416-408-4357 website: dcogt.com
Toronto Community Crisis Service - Non-police mobile crisis response — call and request a mobile crisis team - Dial: 2-1-1
Distress Centre Halton - Halton Hills / Milton: 905-877-1211; Burlington: 905-681-1488; Hamilton: 905-561-5800; Oakville: 905-849-4541 website: dchalton.ca
Trans Lifeline - 1-877-330-6366 website: translifeline.org




