ኦቲዝም ክፍል ፪-ሥውር ኦቲዝም

Share
ኦቲዝም ክፍል ፪-ሥውር  ኦቲዝም
Photo by Steve Smith / Unsplash

ኦቲዝም የሚለውን ቃል ስንሰማ ምናልባት በአዕምሯችን ውስጥ የሚቀረጸው በሕፃናትና በልጆች የተመሰለ ምስል ሊሆን ይችላል። ይሁንና በተለምዶ በልጆችና በጎልማሶች ዘንድ ከምናየው፤ ከተነገረን፤ ካነበብነው፤ ከምናውቀው በተለየ መልኩ ኦቲዝም በዓዋቂነት የዕድሜም ጭምር ለመጀመሪያ ጊዜ ሊገኝ እንደሚችል ማስተዋል ይገባል።

ኦቲዝም እ.አ.አ. ከ1911 ዓ.ም. ጀምሮ የሚታወቅ ሁኔታ ሲሆን ለበርካታ አሥርተ-ዓመታት የነበረን ግንዛቤ በሕፃናት ላይ ብቻ የሚታይ ሁኔታ ነው የሚል ነበር። ከዚህ ተያይዞም የኦቲዝም ምርመራ በሕፃንነት ዕድሜ ላይ ብቻ በማተኮሩ ኦቲዝም በአብዛኛው በልጅነት ዕድሜ እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል።

እ.አ.አ. ከ1980'ዎቹ ዓመታት ወዲህ ስለኦቲዝም ያለን ዕውቀትና ግንዛቤ እየዳበረ በመምጣቱ ከ30 ወራት ዕድሜ በታች ያሉትንና ከባድ የአዕምሮ ዝግመት የሚያሳዩትን ሕፃናት ብቻ ያቅፍ የነበረውን የቀድሞውን ጠባብ የኦቲዝም መስፈርት ወደኋላ በመተው የአዕምሮ ዝግመት የሌላቸው እንዲሁም ልዩ የተፈጥሮ ተሰጥዖ ያላቸው ልጆች ጭምር በመስፈርቱ እንዲጠቃለሉ ተደረገ።

ኦቲዝም መኖሩ ሳይታወቅ በርካታ ዓመታት ሊያልፉ ይችላሉ

  • ወላጆችና አሳዳጊዎች የኦቲዝምን ምልክቶች ሆን ብለውም ይሁን በቸልተኝነት አለበለዚያም ባለማወቅ ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ በሚቀሩበት ጊዜ
  • የጤና ባለሞያዎች በዕውቀትም ይሁን በብቃት ማነስ ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጡ ሲቀሩ
  • የኦቲዝም ምልክቶች ሥውር ወይም በግልጽ የማይታዩ ከሆኑ

በ80'ዎቹና በ90'ዎቹ (እ.አ.አ.) ኦቲዝም እንዳላቸው ሳይታወቅላቸው የቀሩ ልጆች በዓዋቂነት ዕድሜያቸው ሥውር ኦቲዝም እንዳላቸው ሊታወቅ እንደሚችል ተደረሰበት። የሚከተልሉት ምክንያቶች ለሥውር ኦቲዝም ትኩረት እንዲሰጥ አስተዋጽዎ አበርክተዋል፦

  • ስለ ኦቲዝም የነበረን ዕውቀት እያደገ ሲመጣ የሰዎች ንቃተ-ሕሊናም በዚያው መጠን ከፍ እያለ በመምጣቱና ኦቲዝም የዕድሜ-ልክ ሁኔታ መሆኑንና በዓዋቂ ዕድሜም ሊከሰት እንደሚችል በመታወቁ
  • ሥውር የኦቲዝም ምልክቶች በሚያስከትሏቸው የመንፈስ ውጥረቶችና ተያይዘውም በሚከሰቱት የባህርይና የእርስበእርስ ግንኙነቶች ችግሮች ሳብያ ሰዎች እራሳቸውን ለመረዳት ሲሉ በፈቃዳቸው ኦቲዝም ይኖራቸው እንደሆነ ለማወቅ በመፈለጋቸው
  • ኦቲዝም ያላቸው ልጆች ወላጆች በልጆቻቸው ላይ የሚያይዋቸው አንዳንድ ምልክቶች በእራሳቸውም ላይ እንደሚገኙ በማስተዋላቸውና ያልታወቀ ኦቲዝም ይኖራቸው እንደሆን በመጠርጠር ለማወቅ ፍላጎት ስላደረባቸው
  • በማኅበራዊ ሚዲያ ስለኦቲዝም የሚሰራጩ መልዕክቶች አመለካከታችን ሰፋ እንዲል እገዛ በማድረጋቸው
  • ቀደም ሲል ኦቲዝም በወንዶች ልጆች ላይ ብቻ የሚከሰት ሁኔታ ነው ተብሎ ይታመን ስለነበረ በብዙ የሚቆጠሩ ሴቶች ልጆች ኦቲዝም እንዳላቸው ሳይታወቅላቸው ቆይተው በዓዋቂ ዕድሜያቸው ማረጋገጥ ስለተቻላቸው
  • ጭንቀትና ድባቴ ኖሯቸው እርዳታ ሲሹ አንዳንድ ሰዎች በስህተት የአዕምሮ በሽታ (ለምሳሌ ባይፖላር ) አለባችሁ ተብለው ሕክምና ሲያገኙ የነበሩ ሰዎች ለሚያሳዩት የባህርይ ለውጥ መሠረቱ ኦቲዝም ሊሆን እንደሚችል ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊነቱ ስለታመነበት
  • ኦቲዝም ያላቸው ሰዎች ጥንካሬንና ልዩ ተሰጥዎን የሚያካትት የነርቭ ድሮች አወቃቀር ልዩነት ያላቸው (neurodivergent) ሰዎች እንጂ የአካል ጉዳተኞች አለመሆናቸው ተቀባይነት እያገኘ በመምጣቱና ትጉ ማስተዋልና ጥራት ያላቸው ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል ልዩ ብቃትና ችሎታ እንዳላቸው በመታወቁ
  • ኦቲዝም ዕድሜና ፆታ ሳይለይ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኝ ሁኔታ ከመሆኑም በላይ አገላለጹም ከሰው-ሰው ሊለያይ እንደሚችል በመታወቁ

የሥውርና ዘግይቶ የሚታወቅ ኦቲዝም ምልክቶች

በልጅነታቸው ኦቲዝም እንዳላቸው ሳይጠረጠር ቀርቶ ወይም ሳይታወቅላቸው ቆይቶ ከአደጉ በኋላ ኦቲዝም ስፔክትረም ዲዞርደር (ASD) እንዳላቸው የሚታወቅላቸው ሰዎች የሚከተሉትን ሥውር ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ፦

በማኅበራዊ ኑሮ ረገድ

  • የሌላን ሰው ሀሳብ ወይም አስተያየት ለመገንዘብ/ለመረዳት መቸገር - በንግግር ከሰው ጋር አለመግባባት
  • እራስን ማግለል (ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን ለማስወገድ ሲባል)
  • የስሜታዊነት ባህርይ ማሳየት (ተዕግስት ማጣት፣ ብስጭት፣ ወዘተ)
  • በአካል ክፍሎች (በዓይኖች፣ በትከሻ፣ በመልክ ወዘተ) የሚታገዙ የስሜት አገላለጾችንና ትርጉማቸውን/ መልዕክታቸውን ለመረዳት ወይም ፊትን ማምበብ አለመቻል

ለምሳሌ፦

  • በባህል ወይም በኅብረተሰብ ልማድ የማይባሉ አባባሎችን ማለት/መናገር
  • የውይይት አርዕስትን አለመከተል ወይም መስመር መሳት
  • ጥያቄ ሲመልሱ ትንታኔ ማብዛት ወይም በተቃራኒው እጅግ በጣም በአጭሩና በተወሰኑ ቃላት ብቻ መልስ መስጠት
  • የግል ሃሳባቸውን ለመግለጽ ሲያዳግታቸው መበሳጨት ወይም እራስን ማግለል
  • ስለ ነገሮችና ሁኔታዎች ከሚገባው በላይ ማብሰልሰል፣ መጨነቅና መጠበብ፣ ሲበዛባቸው ደግሞ መነጫነጭ ወይም እራሳቸውን ማግለል
  • ዘይቤያዊ አነጋገሮችን፣ ቀልዶችን፣ ተረቦችን አለመገንዘብና የተባለውን በቀጥታ ቃል-በቃል መውሰድ (አለመግባባትንና ግጭቶችን ያስከትላል)
  • ጓደኛን ማፍራት እንዲሁም ዘላቂነት እንዲኖረው ማድረግ ሊከብዳቸው ይችላል
  • ብዙ ጊዜ ብቸኝነትን መምረጥ

ድግግሞሽ

  • አንዳንድ ተግባሮችን እንደልማድ በተደጋጋሚ ማድረግ
  • ለዕለት-ተዕለት ዕቅዶቻቸውና ተግባሮቻቸው ግትርነትን ማሳየት - ለውጥን አለመፈለግ
  • በአካባቢያቸው ያሉ ቁሳቁሶች ቦታቸው፣ አደራደራቸውና አቀማመጣቸው የተወሰነ መልክ እንዲይዝ መፈለግ

ለምሳሌ፦

  • ጭኖቻቸውን በእጆቻቸው ማሻሸት፣ እጆቻቸውን ኪሶቻቸው ውስጥ ከትተው ጣቶቻቸውን ማፋተግ፣ የውስጥ እግሮቻቸውን እያራገቡ መሬትን ደጋግሞ መምታት (foot-tapping) ወይም እግርን ማወዛወዝ፣ አንድን ዘፈን ደጋግሞ ማዳመጥ፣ እጆችን ማርገብገብ፣ ወዘተ። እነዚህን የመሳሰሉ የድግግምሽ ተግባራት ስቲሚንግ (stimming) በመባል ይታወቃሉ።
  • ተመሳሳይ ነገሮችን/ሁኔታዎችን/ተግባራትን በየዕለቱ ማድረግ - ሁኔታዎቹን በተለመደው መንገድ እንዳያደርጉ የሚያግዳቸው ነገር ከኖረ መንፈሳቸውን ሊረብሽና ሊያስቆጣቸው/ሊያበሳጫቸው ይችላል
  • ሌሎችን ለመረዳትና ሁኔታዎችን ለመገንዘብ በመፈለግ የሰዎችን ፊት እንዲሁም የአካባቢን ሁኔታ ተግቶ መቃኘትና ማጥናት (hypervigilance & scanning)
  • የጨርቆች መለስለስ ወይም መሻከር፣ የልብሶች ማጥበቅ ወይም አለመመቸት፣ የምግብ ዓይነቶች ስሜት፣ ጣዕምና ሽታ ወዘተ ሊረብቿቸው ስለሚችሉ የተወሰኑ ልብሶችንና ምግቦችን ብቻ ሊያዘወትሩ ይችላሉ (sensory & processing differences)

(ከላይ የተዘረዘሩትና እዚህ ያልተጠቀሱ ሌሎችተደጋጋሚ ተግባራት የኦቲዝም ሰዎችን ጭንቀቶች በማለዘብና መንፈሳቸውን በማረጋጋት ረገድ ሰፊ ሚና ይጫወታሉ።)

የኦቲዝም ሰዎች ስለ ተወሰኑ ሁኔታዎች/ነገሮች ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል (special interests)። ስለሆነም በተወሰኑ አርዕስቶች ላይ (ለምሳሌ ስለ ወፎች፣ ስለ መኪናዎች፣ ስለ ፊልሞች፣ ወዘተ) ጥልቅ ዕውቀት ኖሯቸው ጥቃቅን መረጃዎችን የማስታወስ ልዩ ችሎታ ሊያሳዩ ይችላሉ።

የአዕምሮ አስፈጻሚ ክህሎቶችንና ስሜቶችን አስመልክቶ

ሥውር ኦቲዝም ያላቸው ሰዎች እንደ ዕቅድ ማውጣት፣ ሁኔታዎችን ማደራጀትና ማመቻቸት፣ ማስተዋልና ስሜትን መግዛት ያሉትን በአዕምሯችን የአስፈጻሚ ክህሎቶች (executive function) አማካኝነት የሚተገበሩ ኀላፊነቶችን ለመወጣት፣ ተግባራትን ለማከናወንና፣ ስሜታቸውን ለመቅቆጣጠር ሊቸገሩ ይችላሉ።

ለምሳሌ፡

  • የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን ለማውጣትና ለማቀናጀት ዕርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል - ክፍላቸውን/ቤታቸውን ማጽዳት፣ ቀን ጠብቀው የቢል ክፍያዎችን ማሟላት፣ ወዘተ
  • ቀጠሮዎችን መዘንጋት ወይም በተደጋጋሚ የማርፈድ ባህርይ ሊያሳዩ ይችላሉ
  • የሌሎችን ሰዎች አመለካከትና ሀሳብ ለመረዳት እንዲሁም ከሌሎች የሚጠበቅባቸውን ለማሟላት እገዛና ማበረታታት ሊያስፈልጋቸው ይችላል
  • ስሜታቸውን ለመረዳት፣ ለመቆጣጠር ወይም ለማስረዳት ሊያዳግታቸው ይችላል። ስለሆነም ከመጠን ያለፉ ወይም የገነኑ ስሜቶችን ሊያንጸባርቁ ይችላሉ።

በተጨማሪም

  • በድምጾችና በሚያዩአቸው ነገሮች ሃሳባቸው በቀላሉ ሊበተን ይችላል (distraction)
  • ለድምጾች እንዲሁም ለብርሐን ትብነትን (sensitivity) ሊያሳዩ ይችላሉ። ለምሳሌ፦
    • ጮክ ያለ ሙዚቃ ወይም ድምጽ ሲሰሙ ጆሮዎቻቸውን በመሸፈትን ወይም ከቦታው በመራቅ
    • የፍሎረሰንት መብራትንና ሌላም ዓይነት ኃይለኛ ብርሐንን አለመፈለግ/መከላከል/መሸሽ

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ኀፍረትን (shame) ሊያስከትሉና በእራስ መተማመንን (self-confidence) ሊያውኩ ይችላሉ።

ከኦቲዝም ጋር የተጎዳኘ የዐቅም መሟጠጥ

ሥውርም ይሁን በግልጽ የሚታይ ኦቲዝም ያላቸው ሰዎች እራሳቸውን ከአካባቢያቸው ለማስማማትና ኦቲዝም ከሌላቸው (allistic/ non-autistic people) ሰዎች ሁኔታ ጋር ለመመሳሰል ሲጥሩ የእራሳቸውን ስሜቶችና ፍላጎቶች ለመደበቅ (masking) ይገደዳሉ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ረጅም ጊዜ ለማሳለፍ በሚገደዱበት ወቅት የነርቨስ ሥርዓታቸው (nervous system) ከዐቅሙ በላይ ስለሚሆንበት - ልክ ባትሪ ለረጅም ጊዜ ሲሠራ ቆይቶ እንደሚደክምና እንደሚሞት - ኦቲዝም ያላቸው ሰዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ "ባትሪያቸው ይደክማል/ይሞታል"። ይህ ከኦቲዝም ጋር የተጎዳኘ የዐቅም መሟጠጥ ስሜት - ኦቲስቲክ በርናውት (autistic burnout) በመባል የሚታወቅ ሲሆን ሁኔታው በጸባይ ማጣት፣ በድባቴ አለዚያም እራስን በማግለል መልክ ሊገለጽ ይችላል። "የስሜት ባትሪን" መልሶ ለመሙላትም ረዘም ያለ የዕረፍት ጊዜ ሊያስፈልግ ይችላል።

ሥውር ኦቲዝም መኖሩ እንዴት ይታወቃል?

ከላይ የተዘረዘሩት ምልክቶች ሲያጋጥሙን በእርግጠኝነት ኦቲዝም ነው ብለን ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያዳግታል። ይሁንና ኤ.ዲ.ኤች.ኢዲ. (ADHD)፣ ጭንቀት (anxiety)፣ ድባቴ (depression) ፤ የአንጀትና የሰውነት መከላከያ ሥራዓት መታወክ (gastro-intestinal and immune function disorders)፣ እንዲሁም የሚጥል በሽታ (epilepsy) ከፍ ብለው ከተዘረዘሩት የሥውር ኦቲዝም ምልክቶች ጋር ተጣምረው በሚታዩበት ወቅት ኦቲዝም ሊኖር ይችል እንደሆነ መጠርጠርና ከግምት ውስጥ ማስገባት ብልህነት ነው።

በአሁኑ ጊዜ ኦቲዝምን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የላብራቶሪ ምርመራዎች በሥራ ላይ አልዋሉም። ነገር ግን ስለ ኦቲዝም ልዩ ስልጠና (specialization) ባላቸው ሰዎች በመታገዝ ወደ ኦቲዝም የሚያመላክቱ መስፈርቶችን በመሙላት (questionnaires) እንዲሁም ከፍ ብለው ከተዘረዘሩት ምልክቶች መሃል የትኛዎቹ እንዳሉ በማጣራት ኦቲዝም መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል።

ሥውር ኦቲዝም መኖሩን ማረጋገጥ ይጠቅማል?

ለማረጋገጥ የሚያበረታቱን ምክንያቶች፦

  • እራስን ለመረዳት - ከሰዎች ጋር በሚኖሩን ግንኙነቶች ያጋጠሙን ያለመግባባት ሁኔታዎች መሠረታቸው ኦቲዝም እንደሆነ ማወቅ እራስን በየምክንያቱ ከመኮነን (self-blame) ያድናል:: ልዩ ዝንባሌዎቻችንና ረቂቅ ችሎታዎቻችን ከኦቲዝም ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ማወቃችንም የኦቲዝምን በጎ ገጽታ ማየት እንድንችል መንገድ ይከፍታል፡፡
  • ዕርዳታን ለማግኘት -
    • ኦቲዝም እንዳለን ከተረዳን አብሮት ለሚከሰት ድባቴ፣ ጭንቀት፣ ወዘተ ተገቢውን ሕክምና ማግኘት ያስችለናል።
    • ኦቲዝምን አስመልክቶ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋሞች ካሉ ተስማሚ የትምህርትና የሥራ መስክ ላይ ለመሰማራት የሚያስችሉ ዕገዛዎችን ማግኘት እንችላለን።
  • ግንኙነቶችን ለማሻሻል -
    • ኦቲዝም እንዳለን ሲረጋገጥ የመንፈስ እፎይታና የሸክም መቅለል ስሜት እንዲሰማን በማድግ እራሳችንን ከመኮነንን ይልቅ (self-blame) በበጎ ዓይን እንድመለከትና ማንነታችንን እንድንቀበል (self-acceptance) ያበረታታናል።
    • ኦቲዝም እንዳለን ከተረጋገጠ ተመሳሳይ የሕይወት ተለምዶ ካላቸው ሰዎች ጋር የመሰባሰብና የመደጋገፍ እንዲሁም የመጎዳኘት ዕድል ስለሚኖረን የብቸኝነት ስሜታችንን ይቀንስልናል።
    • ሥውር ኦቲዝም እንዳለን የተረዱ ሰዎች በእነርሱና በእኛ መሀከል ያለው የአመለካከት ልዩነት ከኦቲዝም ጋር የተያያዘ እንደሆነ እንዲረዱና ስለእኛ ሊኖራቸው የሚችለው አሉታዊ አመለካከት እንዲወገድ፣ ከዚያም አልፎ ግንኙነታችን እንዲሻሻል መንገድ ይከፍታል።

ከማረጋገጥ ወደኋላ እንድንል የሚያደርጉን ምክንያቶች፦

  • በብዙ ሀገራት በዓዋቂ ዕድሜ የሚደረግ የኦቲዝም ምርመራ ብዙ ገንዘብ ያስወጣል (በካናዳ ውስጥ ምርመራው ከ$3000 በላይ ይፈጃል)።
  • በነጻ የመመርመር ዕድል ለማግኘት በጣም ረጅም (በዓመታት የሚቆጠር) የቀጠሮ ጊዜ ይፈልጋል።
  • ምርመራው ጊዜ ስለሚፈጅ ስሜትን ሊያውክ፣ ኦቲዝም ከተረጋገጠ ደግሞ መንፈስን ሊረብሽ ይችላል።
  • ሥውር ኦቲዝም እንዳለን ከታወቀ ሰዎች ስለኛ ያላቸው አመለካከት ሊለወጥ ይችላል፤ የመገለል፣ የመገፋትና የመበደል እንዲሁም ዕድሎችን የመነፈግ ሁኔታዎች ሊከሰቱብን ይችላሉ የሚል ስጋት ወይም ፍራቻ ሊያድርብን ይችላል።
  • በባለሞያ የተረጋገጠ ሥውር ኦቲዝም የትምህርትና የሥራ ዕድሎችን እንደሚከፍትልን እርግጠኛ ላንሆን እንችላለን።

ሥውር ኦቲዝም ሊኖረኝ ይችል ይሆናል ብለው የሚገምቱ ወይም የሚጠረጥሩ ሰዎች ሁሉ በባለሞያ በመታገዝ እርግጠኛውን ውጤት ለማወቅ ይፈልጋሉ ማለት አይቻልም። አንዳንድ ሰዎች ፈጽሞ አለማወቅን ይመርጣሉ። በአንጻሩ ደግሞ ብዙ ገንዘብ ከማውጣት ይልቅ እራሳቸውን በእራሳቸው ገምግመውና ተረድተው "ኦቲዝም እንዳለኝ እገምታለሁ" በማለት ስለእራሳቸው ያላቸውን ግንዛቤ በግልጽ የሚናገሩ ሰዎችም በመሃከላችን ይገኛሉ።

ኦቲዝም ተስፋፍቶ የሚገኝ የነርቮች አወቃቀር ልዩነት ወይም ሁኔታ እንጂ በሽታ ወይም ሕመም አለምሆኑን በማስታወስ ሥውር የኦቲዝም ምልክቶች በአንዳንድ ሰዎች ላይ የባህርይ ለውጥ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።

በትምህርት፣ በሥራና በማኅበራዊ-ኑሮ መስኮች የአንዳንድ ሰዎች ሁኔታ ወይም አስተሳሰብ ሳይገባን ሲቀር ቸኩለን ስለእነርሱ አሉታዊ አመለካከት ከሚኖረን ይልቅ አዕምሯችንን ከፈት በማድረግ "ሌላ ያልተገነዘብነው ነገር ሊኖር ይችል ይሆን?" ብለን እራሳችንን መጠየቅ ይጠቅማል። አለመግባባቶች በሚከሰቱበትም ወቅት ትዕግስትንና ትህትናን በማስቀደም ሰዎችን የተሻለ ለመረዳት ትጋት ማሳየታችን ተገቢና የሚመከር ነው።


References:

Signs of Autism in Adults: A Neurodivergent-Affirming Guide | Prosper Health
Wondering if you’re autistic? Explore common and overlooked signs of autism in adults, including masking and sensory issues, and learn about next steps.
The Lost Generation of Adults with Autism | Mental Health Academy
This article explores the diagnistic criteria for autism spectrum disorder and how to recognise undiagnosed autism in adults.
The Lost Generation of Autistic Adults
NDI Video | Autism Awareness Series
Autism Symptoms and Diagnosis in Adults
Wondering if you have autism? This can serve as a guide to help you start a conversation about adult autism symptoms with your doctor.

Read more

አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች

አራቱ የግንኙነቶች ዕንቅፋቶች

ተፈላልገውና ተመራርጠው አብረው ለመሆን ወይም ኑሮን አብረው ለመመሥረት የሚወስኑ ሁለት ሰዎች ወይም ጥንዶች (couples - ካፕልስ) ለግንኙነታቸው መሳካት ወይም አለመሳካት የየግላቸው የሕይወት ልምዶችና ተሞክሮዎች፣ እሤቶቻቸው እንዲሁም ሕልማቸውና ስለወደፊቱ ሕይወታቸው ያላቸው ተስፋ ወሳኝነት አላቸው። ጆን እና ጁሊ ጎትማን የተባሉ ሁለት ሳይኮሎጂስቶች (Drs. John & Julie Gottman) የጎትማን ሜተድ በመባል የሚታወቀውን የጥንዶች

By TW
የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና - አስተዳደግ ክፍል ፬

የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና - አስተዳደግ ክፍል ፬

የልጆችና የወጣቶች የአዕምሮ ጤና መዛባት ተስፋፍቶ የሚገኝ ክስተት ከመሆኑም በላይ እንደ የልጆች ጭንቀትና ድባቴ ያሉ ሁኔታዎች የዕድሜ-ልክ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ በመረጃ የተደገፉ ጥናቶች ያሳያሉ። (ከሲ.ዲ.ሲ. የተገኘ መረጃ ) የልጆች የአዕምሮ ጤንነት የልጆች የአዕምሮ ጤንነት የተጠበቀ ነው ብለን ስንል የአዕምሮ ጤና መዛባት እንደሌላቸው በማረጋገጥ መመስከርን ብቻ ሳይሆን ሙሉ ጤንነታቸው ተጠብቆ

By TW
አዎን! ወንዶችም ያርጣሉ!

አዎን! ወንዶችም ያርጣሉ!

የሴቶች እርጣት (menopause - ሜኖፖዝ) በእያንዳንዷ ሴት የሕይወት ሂደት ውስጥ በድንገት የሚከሰት ከኤስትሮጀንና ፕሮጀስትሮን የሴቶች ሆርሞኖች መጠን ማሽቆልቆል ሲሆን ከወር-አበባ ማብቃትና የሴቶች የመውለድ ችሎታ ፍጻሜ ጋር የተቆራኘ ሁኔታ ነው። በአንጻሩ ግን የወንዶች እርጣት (andropause - አንድሮፖዝ) በአንዳንድ ወንዶች ዘንድ ብቻ የሚከሰትና ከቴስቶስትሮን የወንዶች ሆርሞን መጠን መቀነስ ጋር የተጣመረ፣ አመጣጡ ደግሞ

By TW
ኦቲዝም - ክፍል ፩

ኦቲዝም - ክፍል ፩

የኦቲዝም ቁጥር መጨመር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም. መጀመሪያ ከአንድ መቶ ሃምሳ ልጆች መሀከል አንድ (150፡1) ኦቲስቲክ ልጅ ይገኝ እንደነበረና ከሃያ ዓመታት በኋላ ይህ ቁጥር በሶስት እጥፍ ያህል ጨምሮ በ2020 ዓ.ም. ከሰላሳ ስድስት ልጆች መሀል አንድ (36፡1) ኦቲስቲክ ልጅ መገኘቱን መረጃዎች ያሳያሉ። የኦቲዝም ቁጥር መጨመር ምክንያቱ

By TW